Wednesday 10 July 2013

በክንዱ ያዳነኝ

ለኃጢአት ከተሰጠ ሰውነት
ሞት ሞት ከሚሸት ማንነት
አልጋ ሲሉት ከሚል ቀጋ
ሁሌ ከሚቃትት ሁሌ ከሚሰጋ

ጥላን ከሚከተል ንፋስ ከሚጎስም
ሕማም ደዌ ሀሳር ከበዛበት ዓለም
ማን ነው የሚያድነኝ? ኃይሉን ክንዱን ሰብሮ 
ከንቱ ከተባለ ከአለማመን ኑሮ …
የሞት ዕልልታ ከነገሰበት
ሰይጣን በክፋት ከአጊያጌጠበት
ኃጢአት ድር ቤቷን ከሠራችበት
ሥር መሠረቷን ካፀናችበት
ማን ያድነኛል? ከመቃተቴ
ማን ይሰማኛል? ይህን ጩኸቴ፡፡
ጽድቅ ከሚሠለች ከድካም መንፈስ
ማለዳ ቀድሶ አመሻሽ ከሚረክስ …
የመርገም ዕጭ አብቅሎ
የጽድቅ ጫጩት ገድሎ …
ከድንግዝግዝ ጉዞ ካልጠራ ዕይታ
ከሰካራም ጠባይ ከዚያ ክፉ ጌታ
ማነው የሚያድነኝ? ብዬ አልታወክም
ልቤን አላደክምም አቅሌን አልበትንም
አለልኝ መከታ የተዘረጋ ክንድ
ቀራንዮ ጎልጎታ ውዴ እኔን በወውደድ …
ሸክሜን ተሸክሞ ርስቴን ያሰፋልኝ
ወዶ በፈቃዱ ሞቴን የሞተልኝ

ጌታ ኢየሱስ ነው በክንዱ ያዳነኝ፡፡

No comments:

Post a Comment