Friday 12 July 2013

የምድረ በዳው ዋርካ

   Please read in PDF
  የበረሃ ጉዞ ከዋዕዩና ከንዳዱ ጽኑዕነት የተነሳ እንዲህ እንደዋዛ የሚታሰብ ጉዞ አይደለም፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ከወጡ በኋላ ዳግመኛ ወደኋላ መመለስ እንዳይችሉ የኤርትራን ባሕር በደረቅ ተሻግረው የባሕሩ ደጅ ሲዘጋ ከፊት ለፊታቸው የገጠማቸው ታላቁ የሲን ምድረ በዳ ነው፡፡

http://1.bp.blogspot.com/-smIC3HtGJTM/UeDxWHcnMfI/AAAAAAAAAE8/fnF7TnNFhuA/s320/desert-tree07.jpg


       ምድረ በዳ አድካሚ፣ አታካች  ብቻ አይደለም፤ ጽኑ አዙሪት ያለው፣ በአውሎ የታገዘ፣ አሸዋውም ድንገት ደፍቆ የሚቀብር ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ይህንን እያወቀ ነው ሕዝቡን ወደዚህ ሥፍራ የመራው፡፡ ምንም በሌለበት ሁሉ ነገራቸው ሊሆን፡፡ እርሱ ሁሉ በሁሉ ነውና፡፡ ሕይወት ጉዞ ናት፥ በተለይ ከጌታ ጋር አንድ ጊዜ ጉዞ ከጀመርን በኋላ ፈርዖንንና ሠራዊቱን የዋጠውን ያን የኤርትራ ባሕር ለመሻገር ወደኋላ ለመመለስ ማሰብ ሞት ነው፡፡ የተጠራነው “ … ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሮጥ …” ዘንድ ነው፡፡
    የኃጢአት ደጅ ዘግተን ከመጣን በኋለ ተመለሰን እንደሎጥ ሚስት ወደኋላ መመለስ የሚያምረን፣ ወደኋላ መመልከት የሚያስጐመዠን ከሆነ የኖርንበት ሕልውና እስኪረሳ የጨው ሓውልትነት ይጠብቀናል፡፡ ወደኋላም ከመመልከት ያንን የምድረ በዳ ጉዞ ከአሻጋሪው ጌታ፤ ከአሳላፊው ወዳጅ ጋር አብሮ መሻገርን የሚመስል አሸናፊነት የለም፡፡
     ይህች አለምና በውስጧ ያሉ ብዙ ነገሮቿ ምድረ በዳ ናቸው፡፡ ታመነው ባልንጀርነት በመከዳዳት ሲዘጋ ፣ የጣፈጠው ፍቅር ምሬቱ ልክን ሲያልፍ፣ ያጐረሰን ሲነክስ፣ የባረከን ሲያማ … እንደመስማት፤ እንደማየት የሚያቃጥል ምድረ በዳ የለም፡፡ ትልልቅ ወዳጅነቶች፣ ትልልቅ ትዳሮች፣ ትልልቅ የፍቅር ሕብረቶች … ምድረ በዳ በሚሆን አመጽ፣ አድመኝነት፣ ጠብና ክርክር … ተቃጥለው ብናኝ አሻራቸው እንኳ እስከማይታይበት ጠፍቷል፡፡
     በዚህች ምድረ በዳ አለም ላይ ስትጓዙም ጠላት ያቆሰላችሁ፣ ወዳጅ ያከሰላችሁ፣ ያመናችሁት ሰው በክህደቱ ያጠቆራችሁ፣ ከግብጽ ከምትከፋ አለም ወጥታችሁ ባሕረ ኤርትራ ኃጢአትን ጠልታችሁ ወደጌታ የክብር ወንጌል መጥታችሁ አብያተ ክርስቲያናት የገፏችሁ፣ ያለስማችሁ ስም ሰጥተው፣ ታርጋ ለጥፈው ያሳደዷችሁ፣ አይገፉም አይበድሉም በተባሉት አብርሃምና ሳራ የተገፋችሁ ንጹሐን ብዙ አጋሮች የጌታ ቤተሰቦች ሆይ! አይዟችሁ  ትልቅ የሕይወት የእረፍት ዋርካ ኢየሱስ አለላችሁ፡፡ ጥላው ያሳርፋል፤ እረፍቱ በቀን ከሌ’ት ያዘምራል … ሩጫውን ታግሳችሁ ሩጡ … መስቀላችሁን ተሸክማችሁ በምድረ በዳዋ አለም ጨክናችሁ በሞገሱ ተራመዱ … እርሱ አማኑኤል የሕይወት ጥላ ዋርካችሁ አለላችሁና …
   ወንጌልን በወንጌል ልብ፣ ያንን ሁሉን አድራጊ የመጽሐፍ ቅዱስን እግዚአብሔር እየሰበካችሁ እያገለገላችሁ ብዙ “ወዳጅ” የከዳችሁ፣ ዘመድ ወገን የጠላችሁ፣ ጌታን ስትቀርቡ አለሙ ምድረ በዳ የሆነባችሁ ደስ ይበላችሁ … እርሱ በፈረሰው በኩል ፣ በዋዕዩ ምትክ ሆኖ ዋርካ ሆኖላችኋል … እያለቀሳችሁ ዝሩ፥ ነዶ ታቅፋችሁ በእርሱ ደስታ ትመለሳላችሁ … በአዳኝነቱ የምታምኑ ሆይ! ኑ ከዚያ ዋርካ ሥር ሁላችን እንጠለል፡፡
ያረፍኩብህ ዋርካዬ መድኃኒቴ ኢየሱስ ሆይ! ተባረክልኝ፡፡ አሜን፡፡



No comments:

Post a Comment