Wednesday 24 July 2013

ልከኛው ጳውሎስ - 1





 Please read in PDF:- Likegnaw Pawlos                   
http://3.bp.blogspot.com/-v6MBFvXs0og/Ue-C6SMGNAI/AAAAAAAAAFQ/IyavgKd7Db0/s1600/_St_Paul_Preaching_in_Athens.jpg
      
       እንደኰከብ ፈርጥ ለአሕዛብ በማለዳ የፈካ ፣ በነፍስ ተወራርዶ ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የሰበከ ፣ በከሳሾች ፊት ለቅንጣት እንኳ አንገቱን ሳይደፋ የኢየሱስንበስም የገለጠ ፣ ቃሉና ሕይወቱ ነገሥታትንና ፈላስፎችን ለክርስቶስ የሚማርክ ፣ በሥጋ ባለው ባዕለጠግነት ሳይመካ ፤ ላገለገለበትም የሚገባውን አንዳች ሳይጠይቅ እየተራበና እየተጠማ ለክብሩ ወንጌል ያደላ ፣ በክርስቶስ ፊት እንጂ በሰው ፊት መከበርን የጠላ ፣ በአገልግሎቱና በጉዞው ሁሉ ላይከብድ የተጠነቀቀ ፣ ሲታይ ሞኝ በሕይወቱ ግን ለክርስቶስ ብልኅ የሆነ ፣ በድካምና በመገረፍ ያበዛ ፣ በድብደባ ብዙ ጊዜ በመታሰርም ያተረፈ ፣ ለሞት እስኪቀርብ በድንጋይ ለወንጌሉና ኢየሱስ ለሚለው ስሙ የተወገረ …

    በብዙ ፍርሃትና እንቅልፍ በማጣት ፣ በመጨነቅና ብዙ ጊዜ በጥማና በጦም በብርድና በራብ በእርዛትም ያልተማረረ ፣ በስሙ መጋዝን ፊቱ እየበራ የተቀበለ ፣ በቁም እስራት ለዓመታት ቢንገላታም ያልተሳቀቀ ፣ ሲያገለግል ከልቡ ተሰጥቶበጸጋ ያገለገለ ፣ እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ለማስደሰት ለቅጽበት ያልኖረ ፣ ምድራዊውን መከራ በክርስቶስ ተጠቅልሎ የናቀና የተጠየፈ ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በማሳደዱ ንስሐን ብግልጥ በአደባባይ የተናዘዘ …
  በሰው ዘንድ አዕማድና ዋና መስለው ከሚታዩ አንዱ ጴጥሮስን በሠራው ስህተትና እንደወንጌል እውነት በቅንነት ስላልሄደ በአንጾኪያ ፊት ለፊት በተግሰጽ የተቃወመ ፣ ብቻውን ከመሮጥ ተቆጥቦ ቤተ ክርስቲያንን በብዜት እየተከለየጌታውን ሩጫ እንዲሮጡ ምርጥ አብያተ ክርስቲያናትን ያፈራ ፣ መዳናችን እንዲሁ በእግዚአብሔር ጸጋና ብቃት እንጂ በእኛ ንቃት እንዳልሆነአስረግጦ ያስጨበጠ ፣ ለመጽሐፍ ቅዱሷ ቤተ ክርስቲያን ማደግና መለምለም ሁለንተናውን የሰጠ … የመሲሑ ኢየሱስ ጻድቅ ባርያ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፡፡
      ይህን ሁሉ በማድረጉ ግን ምስጋና የጐረፈለት ፣ አድናቆት የበዛለት ፣ ያማሩ ውድ ሽልማቶች የተትረፈረፈለት ፣ በሄደበትም ሁሉ መድረክ የተለቀቀለት አገልጋይ ሳይሆን ተቃራኒውን እንደእጅ መንሻ የተበረከተለት ምርጥ የጌታ የክብር ዕቃ ነው፡፡
      ቅዱስ ጳውሎስ በፊስጦስ ፊት “አብደሃል እኮ ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደእብደት ያዞርሃል” የተባለ ፣ በስብከቱ የተመሰጠው ንጉሥ አግሪጳም “በጥቂቱ ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህን?” በማለት ያሾፈበት ፣ በኢየሩሳሌም ያሉ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ታላላቆች ሊገድሉት በብዙ የፈለጉት ፣ ከአርባ የሚበዙት አይሁድ ሊገድሉት ተማምለው ከመብልና ከመጠጥ የተከለከሉበት ፣ ጠርጠሉስ “ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በአለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሳ ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና ፤ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው ፥ …” ብለው የወነጀሉት …  
      በሁሉም ሰው ዘንድ ያልተወደደ ፣ በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን አወዛጋቢ ማንነት የነበረው ፣ አብረውት የሚያመልኩት እንኳ ብዙ ጊዜ የሚተቹት ፤ ውሸት የሚናገሩበትና የሚያደርገውን የማይገነዘቡለት “መልእክቶቹስ ከባድ ና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ሲታይ ግን ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና፡፡” ብሎ ታላቁ መጽሐፍ እንዳለው ለብዙዎች የልዩነት ሐዋርያ ነበር፡፡
     ወዳጄ ውዱ የክርስቶስ የዛሬው አገልጋይ ሆይ! ወንጌልን ተሰጥተህ የምታገለግል ከሆነ ሁለቱም ቀስቶች ያገኙሃል፡፡ ወንጌል እያገለገሉ ከሰው ሽልማት መጠበቅ በሚገባ የወንጌሉን ጠባይ አለማወቅ ነው፡፡የቀስተኛውን የዲያብሎስን ቀስትና የሞትን መውጊያ መስበር በራሱ ሕመም አለበት፡፡ የዲያብሎስን ራስ የምንቀጠቅጥ ከሆነ የሰኰና መነከስ ሊያገኘን ግድ ነው፡፡ ከሰማዩ ስፍራ ከኢየሱስ ጋር ለመቀመጥ መነሻው በረት መድረሻው መስቀል መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
      ጳውሎስ እንደጌታው የራሱን መስቀል የተሸከመና ሩጫውን በመታገስ ሲሮጥ ያገኘውን ተቃውሞና የደረሰበትን መከራ ሁሉ በደስታ የተቀበለ ነው፡፡ በብዙ ወደኋላ የሚስቡ ነገሮች እየገጠሙት በመቶ እጥፍ ወደፊት ተጉዞ የክብሩን ወንጌል የገለጠ ጻድቅ ነው፡፡
      በብዙ የስቃይ ሕመም ውስጥ እንኳ ሆኖ ድንቅ ዘማሪም ነበር፡፡ ከበዛው ከጠላቱ ተግዳሮት ይልቅ የሚጋርደውን የመድኃኒት ኢየሱስን እጅ እያየ ፣ ለቁጥር ከሚታክቱት ከሳሾቹና አሳዳጆቹ ነቃፊና ተቺዎቹ ይልቅ ለታመኑት ጥቂት የወንጌል ልብ ላላቸው እየተጋ ለእናት ወንጌል በመሰጠት ያገለገለ ወንድም ነው፡፡ አገልጋይ ሆይ! ከገዛ ወገኖችህ እንኳ ትዕልፊት መከራ እንዳለብህ አትዘንጋ፡፡ጳውሎስ ያገለገላትን ወንጌል የምታገለግል ከሆነ እውነትን እያገለገልክ መናፍቅ ተብለህ እንደምትወገዝ አትጠራጠር፡፡ በክብሩ ዙፋን ፊት የጽድቅን አክሊል ልትቀበል የምትተጋ ብርቱው ሆይ! ጸጋው ይበቃሃል፡፡ ኃይሉ በድካምህ ይፈጸማልና በርታ!!!
     የጌታ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ አገልጋዮቻችንን ታግኝ፡፡ አሜን፡፡ 




1 comment:

  1. 10 Q! it is blessing to hear about st. Paul!

    ReplyDelete