Friday 28 June 2013

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ትህትና

   የእግዚአብሔርን ሠሪነትና ሃለዎትን ለመንፈሳችን ከምናስረግጥበት አንዱና ዋናው ትልቅ ሥራ ጸሎት ነው፡፡ ደስታችንንና ሐዘናችንን፣ ምሬታችንናና ጣዕማችንን፣ ከፍታችንንና ውርደታችንን … በሁኔታና በችግር ታጥረን እንኳ የምንናዘዝበት የማይረሳ ርዕስ ጸሎት ነው፡፡ ጸሎት ለመጸለይ ደጅ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉ ነገራችንን በሩን ዘግተንበት፥ የልባችንን እልፍኝ ከፍተን ከእግዚአብሔር ጋር የምናወራበት ቃል ጸሎት ነው፡፡ ልብን አዋርዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመጸለይ እንደውኃ የሚፈስስ የተሰጠ ሕይወት ይጠይቃል፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ለመሰጠትና ለመፍሰስ ደግሞ የመጀመርያው በር ትህትና ነው፡፡ ትህትና መቅለስለስና መሬት መሬት እያዩ “መሽኮርመም” አይደለም፡፡ ትህትና ራስን ንቆ ባዶነትን መርጦ መንፈስን በጌታ እግዚአብሔር ፊት ማዋረድ ነው፡፡   
     
     ቅድስት ድንግል በጸሎቷ ሕያው እግዚአብሔር በሥራው ተገልጦ ትሁታንን ከፍ ከፍ ሲያደርግ፤ ትዕቢተኞችን ሲያዋርድ፤ የተራቡትን ሲያጠግብ፤ የጠገቡትን ሲያስርብ፤ ባዶዎችን ሲመላ፤ የአብርሃምን ኪዳን ሲያስብ … ዛሬም እየሠራ በሐለዎቱ አለ ትለናለች፡፡ ጸሎታችን የእግዚአብሔርን መኖር ማስረገጥ ካልቻለ ግብዛዊ ማነብነብ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በሥራው እንዳለ ካሰብን ግን ባይመለስልን እንኳ ደስተኞች ነን፡፡
     ሕልውናውን ስላመነች ራስዋን ፍጹም በማዋረድ በፊቱ ቀረበች፤ “የባርያይቱን ውርደት ተመልክቷልና” ብላ፡፡ አዎ! እንደክቡር ባርያ ሳይሆን ከባርያም እንደተዋረደ ባርያ ራስዋን ቆጠረችው፡፡ ትህትና ያለንን የምንቆጥርበት የሂሳብ ስሌት ሳይሆን፥ ሁሉን ለክብሩ ጥለን እኛ በክብሩ የምንጋረድበት ምስጢር ነው፡፡ አስተዋይ ባርያ የእርሱን ማነስ ሳይሆን፥ የጌታውን መግነንና መክበር እያየ በነፍስ በመንፈሱ ይደሰታል፡፡ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” አይደል ያለችው ቅድስቲቱስ?
   የአሥራ አምስት ዓመት ብላቴና ናት፤ የምትኖረው ከአገልጋዮች ተርታ ከቤተ መቅደሱ ሳይሆን፥ የተናቁ ሰዎች ከሚኖሩባት ከናዝሬት ከተማ ነው፡፡ ጌታ የመረጣት “ታላቅ ሥራን በእርሷ ሊያደርግ” እንደሆነ ከመልአኩ ገብርኤል ቃል ሰምታለች፤ ነገር ግን በልብዋ አንዳች አልተመካችም፡፡ ይህንንም አሰምታ ተናገረችው፤ “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና”፡፡
    ፍሬ የበዛበት ዛፍ ያጐነብሳል፥ የጌታ ጸጋ የበዛለትም በልቡ አይመካም፡፡ ባለውና በተሰጠው ጸጋ አካፍሎ በመስጠቱ ይረካል እንጂ፡፡ አገልግሎ፣ የተሰጠውን ሁሉ አካፍሎ፣ ወጥቶ ደክሞ … ራሱን ግን እንደማይጠቅም ባርያ አድርጐ ይቆጥራል፡፡ እውነተኛ ትህትና እያገለገሉ ክብርን ሳይሆን ብዙ እየደከሙ ለክብር እንደማይገባ ራስን መቁጠር ነው፡፡
     ቅድስት ድንግል የኢየሱስ እናት ናት፡፡ ይህንንም መልአኩ አጽንቶ ነግሯታል፤ እርሷ ግን ራሷን በትህትና እንደባርያ ትቆጥራለች፤ ከእርሷ የሚወለደው አለሙን ከኃጢአቱ የሚያነጻ፣ መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ የእግዚአብሔር በግ፣ የያዕቆብን ቤት የሚገዛ ጌታ፣ ጠላትን የሚሰብር የይሁዳ አንበሳ ነው፤ … እርሷ ግን በዚህ ጌታ ፊት ራስዋን እንደባርያ፥ መዋረዷንም የሚመለከት አምላክ እንደሆነ በጸሎቷ ተናገረች፡፡
    ድንግል ማርያም የኢየሱስ እናት ሆና ዓይኖቿን በራሷ ላይ ስትጥለው ግን[የጠቢብ ዓይኖቹ በራሱ ላይ ናቸውና] ባርያ መሆንዋን ተመለከተችው፤ ስለዚህም የባርያይቱን ውርደት ተመልክቷልና አለች፡፡ እኛ ራሳችንን ካልጣልን እግዚአብሔር አያነሳንም፤ እኛ ራሳችንን ባከበርነው መጠን እናጣዋለን፡፡ ትህትና በጌታ ፊት ራስን መጣልም ነው፡፡ ትህትናዋ ልባችሁን የነካ፥ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤” ወዳለው ጌታ ልባችሁን አቅኑ፡፡
              “እለትቀውሙ አትህቱ ርዕስክሙ”
      የትህትና ባለቤት ጌታ እግዚአብሔር ልባችንን ይግዛው፡፡ አሜን


2 comments:

  1. denke new tebareke

    ReplyDelete
  2. AMLAKE KIDUSAN KALE HIWOT YASEMAH. DIGIL BEMILJAWA ATILEYEH EWUNET NEW YE TSAFKEW.

    ReplyDelete