Monday 11 September 2023

“ንስሐ ግቡ” (ማቴ. 3፥2)

 

መጥምቁ ዮሐንስንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሚያመሳስላቸው የስብከት ርዕሶች ቀዳሚው፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚለው መንግሥተ ሰማያዊ አዋጅ ነው። ቅዱስ ማቴዎስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ሲናገር፣ “በዚያም ወራት … በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ። የስብከቱም ማዕከል የእግዚአብሔር መንግሥትና ንስሐ ነበር። “ንስሐ” ድርጊታዊ ትርጒሙን ስንመለከት፣ “መመለስ” ማለት ነው። ይህም ከክፉ ድርጊቶች ኹሉ መመለስ፣ ክፉ ድርጊትን ኹሉ መተው፣ ከክፉ መንገድ ኹሉ ዘወር ማለትና ወደ ክርስቶስ መመለስ የሚል ትርጒምን የያዘ ነው።

ንስሐ ሰዎች በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱበት ነው፤ “ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤” (ሐ.ሥ. 8፥22) በሚለው ቃልና፣ “ … የኃጢአትንም ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ትከፍት ዘንድ፥ ከሕዝቡና ወደ እነርሱ ከምልክህ ከአሕዛብ አድንሃለሁ።” (ሐ.ሥ. 26፥18) ተብሎ በተነገረው ቃል መካከል የንስሐን ትርጒም ብንመለከት፣ ንስሐ ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን መመለስ፣ ክፋን ኹሉ መተው፣ ከሰይጣን ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር ማለትና ወደ እውነተኛ የነፍስ እረኛ መመለስ የሚለውን ዐሳብ ይይዛል፤ (1ጴጥ. 2፥25)።

አንድ አማኝ በኢየሱስ ጌትነት አምኖአል ከተባለ፣

1.   ከኀጢአት ፍጹም ዘወር በማለት ፊቱን በትክክል ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለበት ማለት ነው። ክርስቶስ ከኀጢአት ያዳነን ጌታ ብቻ ሳይኾን፣ በሕይወታችንም ላይ ጌታና ገዥ አድርገን ልንሾመው ይገባናል። በትክክል ከጨለማ ሥልጣን ከተላቀቅን፣ በብርሃናት ጌታ በክርስቶስ ጥላ ሥር መጠለላችንን በትክክለኛ ሕይወት መግለጥና ማሳየት ይገባናል።

2.   ንስሐ፣ አንድ ኃጢአተኛ በወንጌል ሲያምንና ደካማውን በሚረዳው በእግዚአብሔር ጸጋ ታግዞ የሚወስነው ታላቅና ቅዱስ ውሳኔ ነው። “የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።” (ሐ.ሥ. 11፥21)፤ ያለ እግዚአብሔር ጸጋ የትኛውም ኀጢአተኛ ወደ እግዚአብሔር ሊመለስና ወስኖ ከኀጢአት ኃይል ሊላቀቅ አይችልም።

3.   ንስሐ ከመዳናችን ጋር የተሳሰረ እንጂ ሊነጣጠል አይችልም። ብዙዎች ከዳንን ወዲያ ንስሐ መግባትና መጸለይ ለሽልማት እንጂ አይቅምም ይላሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ፣ “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።” (ሐ.ሥ. 3፥19-20) እንዲል፣ ንስሐ መግባ ያለበት እነት ዘወትር ወደ እውነተኛ መዳን የሚያደርስ ነው።

እናም የንስሐ ስብከት ዘወትር ከወንጌልና ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር በአንድነት ተሰናስሎ ወይም ተሳስሮ የሚቀርብ ነው። መዳንን፣ የኀጢአት ሥርየትን፣ እውነተኛ ቅድስናን፣ ከኀጢአት ጋ መጋደልን ወይም መታገልን ያለ ንስሐ ማሰብ አንችልም። የአገር ፈውስ፣ የትውልድ ዕረፍት፣ የክፉዎች ሰላም፣ የኀጢአተኞች መቀደስ … ያለው በክርስቶስ ወደ እግዚብሔር በሚደረግ መመለስ ውስጥ ነው።

በርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በስሙም[በኢየሱስ] ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአል።” (ሉቃ. 24፥47) ብሎ እንደ ተናገረው፣ ባዳነን ጌታ ስም ዘወትር ከኀጢአታችን ንስሐ እንግባ! እንመለስም!

1 comment: