Sunday, 16 July 2023

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳፬)

 Please read in PDF

ለባለፉት ጥቂት ወራት ያረጋል አበጋዝ የተባለ ሰው በጻፈውና “መድሎተ ጽድቅ” በተባለው መጽሐፉ ላይ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሾችን እየሰጠን መኾናችን ይታወሳል፤ ዛሬም የዚያን ተከታዩን ክፍል እናቀርባለን። በባለፉት ጊዜያት፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በተደጋጋሚ የሚቃወምበትንና የሚጥስበትን መንገድ እያሳየን መቆየታችን ይታወሳል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀባይ ቢመስልም፣ ነገር ግን በሌላ ትምህርት ደግሞ ያንኑ የተቀበለውን እውነት መልሶ ሲክድና በሌላ ትምህርት ሲቃወም እንመለከተዋለን፤ ለምሳሌም፦



1.3.    መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት “እያመነ” ይክዳል፦ ስለ መጽደቅ ሲናገር፦ “ሰው ያለ እምነት፣ ያለ ምስጢራት፣ … ስለ ጾመ፣ ስለ መጸወተ … ብቻ ይጸድቃል አንልም።[1] “መዳን በእምነት ብቻ” የሚለው ኑፋቄ ነው” ይላል።[2]  በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ “ለመዳን ወሳኝ ነገሮች ማወቅና ማመን” እንደ ኾነ ይናገራል።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ በተደጋጋሚ በጻፈው መጽሐፉ ውስጥ የሚጠላው ወይም የማይፈልገው ወይም በግልጥ ሲክድ የምንመለከተው ነገር ቢኖር፣ “መዳን በክርስቶስ ብቻ ነው ወይም ማዳን የእግዚአብሔር ብቻ ነው” ብሎ ሙሉ ለሙሉ መቀበል አይፈልግም። ከክርስቶስ የመስቀል ሥራ በተጨማሪ ምስጢራትም የክርስቶስ የመስቀል ሥራ ያህል ተቀባይነት እንዲኖራቸው ብርቱ ጥረት ይጥራል።

አንድ ጊዜ፣

“ሰውን ሊያድነው የሚችለው እውነተኛና ዘለዓለማዊ መድኃኒት ራሱ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን እንዲሁም ይኽ ሰውን የማዳን ጉዳይ ከራሱ ከእግዚአብሔር በቀር በሌላ በማንም የማይፈጸምና ለማንም የማይቻል … ነው”[3]

እንዲሁም፣

“የወደቀውንና የሞተውን የሰውን ልጅ ያዳነው የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ የሰው የራሱ ሥራ አይደለም። ሰው በሥራው ብቻ የሚጸድቅ ቢሆን ኖሮ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ደጋግ አባቶች ለመዳን ክርስቶስ ባላስፈለጋቸው ነበር። … እኛን ያዳነን የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ ሥራችን አይደለም።”[4]

ይልና፣ መልሶ ደግሞ፣

“ለድኅነት ወሳኝና አስፈላጊ የኾኑ ምሥጢራትን መፈጸም ይገባል።”[5]

በማለት ያለ ምስጢራት ክርስቶስ ብቻውን በቂ አይደለም በማለት ይወላውላል። እንዲያውም በክርስቶስ ማመን መሠረት እንጂ መጨረሻ እንዳልኾነ ደፍሮ ሲናገር እንሰማዋለን። ምስጢራት የክርስቶስን ማዳን ረጂ ወይም ደጋፊ ነገሮች እንደ ኾኑ የሚያስረዳበት መንገድ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ፈጽሞ የማይታዘዝ መኾኑን በትክክል ያሳያል። ይኸንኑ ለማጽናትም፣ የጥምቀትን ውኃ “የድኅነት ውኃ” በማለት እስከ መጥራት ይደርሳል።[6]

ለዚህም ዋቢ ሲጠቅስ፣ ቆርኔሌዎስ ለመዳን ቅዱስ ጴጥሮስና ቆርነሌዎስ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድና በቤተ ክርስቲያንም ተገኝተው ምስጢራት መፈጸም እንደ ተጠበቀባቸው አስቂ በኾነ መንገድ ያቀርባል። በዚህ ዋቢው “የመድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ግልጥ ውሸት ይዋሻል፤ ጴጥሮስም ኾነ ቆርነሌዎስ ወደ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ምስጢራት መፈጸማቸውን የሚያመለክት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።

ይልቁን፣ ቆርነሌዎስ እንደ አሕዛብ-አይሁዳዊ ይፀልይ፣ ምጽዋት ያደርግ፣ እግዚአብሔርን ይፈራ፣ በብዙ ሰዎችም ዘንድ በመልካምነቱ የተመሰከረለት ሰው ነበር እንጂ የመዳንን ወንጌል ሰምቶ፣ በክርስቶስ አምኖ፣ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት አልተጠመቀም ነበር፤ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሰበከውና በክርስቶስ ኢየሱስ ባመነ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀት ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅነትን አገኘ፤ ከመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ ሰዎች ኹሉ እያዩት በውኃ ተጠመቀ፤ (ሐ.ሥ. 10፥28-42)።

በቅዱስ ቆርነሌዎስ የመዳን ሕይወት ውስጥ፣ ቀዳሚው ነገር እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት ማመኑ ነው፤ እንዳመነ ወዲያውኑ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ተጠመቀ፤ ከዚያም በኋላ በውኃ ተጠመቀ፤ ቅዱስ ቃሉ “… በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።” (ሐ.ሥ. 10፥43) ብሎ እንደ ተናገረው፣ ቆርነሌዎስ የዳነውና መዳንን የተቀበለው ይህን የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል በማመን ክርስቶስን በመቀበሉ በስሙም የኃጢአትን ስርየት በማግኘቱ ብቻ ነው።

ከዚህ ባሻገር እኒህን እውነቶች እያመነ መልሶ ይክዳል፣ ይህ ብቻ ሳይኾን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት በምልዓት ሳይኖረው በድፍረት የሚናገራቸው ብዙ ነገሮች አሉት፤ እኒህም፦

·        አስቀድሜ እንደ ተናገርኹት፣ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አንዳች ዕውቀት ስለሌለው፣ ስለ ውኃ ጥምቀት ብቻ ይናገራል፣

·        ክርስቶስን በማመን የሚገኘውን የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀትና ሙላት፣ እርሱ ግን በቅብዐ ሜሮን አማካይነት እንደሚገኝ ወይም እንደምንታተም በድፍረት ይናገራል። የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የሚያትመው መንፈስ ቅዱስ እንደ ኾነ ቢያምንም ምልሶ ግን ይክዳል።[7]

እንግዲህ ይህንና ሌሎችንም እውነቶች በግልጥ በመካድ፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣንና እውነት የማይታመን መኾኑን እናስተውላለን። ጌታ መንፈስ ቅዱስ ልቡን እንዲያቀናለት እንማልዳለን!

ይቀጥላል …



[1] ገጽ 185

[2] ገጽ 183-184

[3] ገጽ 92 እና 93 (አጽንዖት የእኔ)፤

[4] ገጽ 121

[5] ገጽ 126

[6] ገጽ 137

[7] ገጽ 146

3 comments:

  1. I am not writing to argue but to know the truth. The word Trinity is not in the Bible. God strictly said that He is the only one and there is no one beside Him. God is a Spirit and manifested in flesh but that doesn't mean He is Trinity. The father the Son and the Holy Spirit is one God not Trinity.

    ReplyDelete
  2. pls Can you show me one verse in the Bible That says God is Trinity?

    ReplyDelete
  3. Glory to God!
    And thank God about you

    ReplyDelete