Tuesday, 25 July 2023

ከእሳት የሚያድን፤ በእሳት የሚጠብቅም አምላክ አለን!

 Please read in PDf

እሳት በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ዓይነት መንገድ ተገልጦአል። ለኹላችንም ግልጥ የኾነው እሳት፣ ሰዎች ለመሥዋዕት አገልግሎት (ዘሌ. 6፥13፤ 1ነገ. 18፥38፤ 2ዜና. 7፥1-3)፣ ለምግብ ማብሰያ (ዮሐ. 21፥9)፣ ለብረት ማቅለጫና (ዘጸ. 32፥24) ለሌሎችም አገልግሎት የሚውል ነው። ይህን እሳት ዓላውያን ነገሥታት አንዳንድ ጊዜ በእነርሱ ላይ ለተነሣሱባቸው ሰዎች፣ የፍርድ መቀጣጫ አድርገው ይጠቀማሉ። ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ ለእርሱ ምስል ወይም ጣዖት አልሰግድም ያሉትን ሦስቱን ወጣቶች፣ “… ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ። (ዳን. 3፥20)።

ነገር ግን ሦስቱን ወጣቶች የእስራኤል አምላክ ያህዌ ኤሎሂም ታደጋቸው፤ አዳናቸውም፤ ከእስራኤል አምላክ ከቅዱሱ እግዚአብሔርም በቀር ሌላ የሚያድን አምላክ እንደሌለ፣ ያ ዓላዊ ንጉሥ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለም (ዳን. 3፥29)፤ በእርግጥም ከእሳት የሚያድን ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ እንደሌለና በእሳትም ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ቅዱሳት መጻሕፍት በምልአት ይመሰክራሉ፤



እግዚአብሔር ከእሳት ያድናል፣

በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፥ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።” (መዝ. 66፥12)

እግዚአብሔር በእሳት ልዑላዊ መግቦቱን ይፈጽማል፣

“ደመናን ለመሸፈኛ ዘረጋባቸው፥ እሳትንም በሌሊት ያበራላቸው ዘንድ ዘረጋ።” (መዝ. 105፥39)

እግዚአብሔር ራሱን በእሳት ይገልጥ ነበር፤

የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ።” (ዘጸ. 3፥2)

በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ።” (ዘጸ. 13፥21)

እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥” (ሐ.ሥ. 3፥3-4)

እግዚአብሔር በእሳት ሕዝቡን ይጠብቃል፤

በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።” (2ነገ. 6፥17)



እንግዲህ በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስንመለከት፣ እግዚአብሔር እንዴት ባለ አስደናቂ መንገድ በእሳት እንደ ተገለጠና ሕዝቡን ከእሳት እንዳዳነ፤ በእሳት እንደሚጠብቅም እንመለከታለን። ይህ ሊስተባበል የማይችል የአምላካችን ቃል ነው።

ነገር ግን ሰዎች ከዚህ በተቃራኒ ፍጡራን፣ ከእሳት እንደሚያድኑና እንደሚታደጉ ሲታመኑና ሲያስተምሩ ይስተዋላል። የመጽሐፍ ቅዱስን ቃሎች ለሚያጠና ለእውነተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ግን ከእሳት የሚያድንና የሚታደግ ያህዌ ኤሎሂም ብቻ ነው! በእርግጥም በአዲስ ኪዳንም፣ በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።” (1ጴጥ. 1፥6-7) ተብሎ እንደ ተነገረ፣ እሳት ከኾነው ከማናቸውም ከሚገጥመን መከራ የሚያድነን ደግሞም መውጫውን የሚያዘጋጅልን (1ቆሮ. 10፥13) እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ አሜን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

1 comment: