Monday 19 June 2023

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ” (ማቴ. 5፥43-48)

 Please read in PDF

ጌታችን ኢየሱስ የሚመሠርታት መንግሥት፣ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት አይደለችም፤ መንግሥቱ ለፍጹማንና እርሱን ለሚከተሉ ብቻ የምትገባና የምትሰጥ ናት። ጌታችን ኢየሱስ ስለ መንግሥቱና በመንግሥቱ ውስጥ ተከታዮቹ እንዴትና በምን መልኩ መመላለስ እንዳለባቸው ሊያስተምራቸው ወደደ፤ ትምህርቱ ባዶ ቃላት አይደሉም፤ ውብና የሕይወት ተስፋዎችን ጭምር የያዙና በምትመጣውም መንግሥቱ እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው በንጉሣዊ ወርቃማ ቃሉ አስተምሮአል።

ማቴ. 5 ጠቅላላውን የብጽዕና አንቀጾችን ብንጨምቅ፣ “በነገር ኹሉ በእግዚአብሔር ላይ የሚደገፉና በመከራ ጊዜ ሳይታክቱ ኢየሱስን በጽናት የሚከተሉ ብጹዓን ወይም ዕድለኞች ናቸው” የሚል እንደ ኾነ አምናለሁ። ስለ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ውድ ነገሮችንና ታላቅ የሚባሉ ነገሮችን ኹሉ እንንቃለን፤ ከውዶቹና ታላቅ ከተባሉት ነገሮች ይልቅ ለክርስቶስ እንሰጣለን፤ በክርስቶስም እንታመናለን፤ እርሱን ብቻም ተስፋ እናደርጋለን።

ጌታችን ካስተማራቸው አስደናቂ ትምህርቶች መካከል አንዱ፣ ጠላትን ስለ መውደድ ነው፤ ክፍሉ የሚጀምረው በአይሁድ መሪዎች ዘንድ ከታወቀው አባባል፣ ማለትም “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህን ጥላ”  ከሚለው ማነጻጸሪያ ጋር በማስተያየት ነው። አባባሉ ለአይሁድ “ባልንጀራ” ማለት፣ አይሁዳዊ ብቻ ሲኾን፣ አሕዛብ ግን ጠላቶቻቸውና በእነርሱ ዘንድ የተናቁና የተጠሉ ናቸው። አይሁድ ከራሳቸው ወገን ያልኾነን አሕዛብ ወይም ሳምራዊ እጅግ ይንቁ እንደ ነበር ጌታችን በምሳሌ ጠቅሶ አስተምሮ እንደ ነበር አንዘነጋም፤ (ሉቃ. 10፥29-37)።

እንኪያስ በጌታችን ትምህርት ግን “ጠላት” ማለት፣ ኹሉን ሰው እንደሚያካትት በተለይም ደግሞ በችግር ላይ ያለን ማናቸውንም ሰው ሊያመለክት እንደሚችል እናስተውላለን። በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን ጠላቶቻችንን እንድንወድድ አብሮ የተናገረው ሐረግ እንዲህ የሚል ነው፣ “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ”። በሰማያት ያለው አባታችን፣ “ለጠላቶቹ” ወይም “ለክፉዎች” ጭምር ፀሐይንና ዝናቡን ሳያቋርጥ ይሰጣል፤ ልክ እንዲኹ ክርስቶስ “አዲስና ሕያው መንገድን” አስተምሮናል (ሉቃ. 10፥20)። ኢየሱስን ስንከተል አይሁዳዊ ብቻ ሳይኾን መላውን ፍጥረተ ዓለም ልንወድድ ተጠርተናል።

የሚወድዱን ብንወድድ ወይም መልካም ላደረጉልን መልካም ብናደርግ፣ ይህን ቀራጮችም ወይም ኀጢአተኞችም መልካም ላደረጉላቸው ያደርጋሉ። እኛ ግን በእኛ ላይ ጉዳት ያደረጉብንን ወይም ያደረሱብንን ሰዎች(ጠላቶቻችን የምንላቸውን) ልንወድዳቸው ይገባናል፤ እግዚአብሔር እኛን ጠላቶቹን ወድዶናል (ሮሜ 5፥10)፤ ወድዶንም ልጆቹ አድርጎናል፤ ልክ እንዲሁ እኛም የበደሉንን፤ ጠላቶቻችንን አሳዳጆቻችንን ልንወድድ ይገባናል፤ ይህ ብቻ ሳይኾን ልክ ወዳጆቻችንን እጅ እንደምነሳው፣ እንደምንባርከው እንዲኹ ጠላቶቻችንን፣ የበደሉንን ጭምር እጅ መንሳት፣ መባረክም ይገባናል። ይህን ካላደረግን በቀር ከቀራጭና ከኀጢአተኛ አንዳችም ልዩነት የለንም! ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ጽድቅና ፍቅር በክርስቶስ ፍቅራችን ካልበለጠ እጅግ ምስኪን ነን!

ታዲያ ይህ የሚቻል ነገር ነውን? የሚል ይኖር ይኾናል፤ በእርግጥም ይህ በሰማይ መንግሥት ወይም ክርስቶስ በሺህ ዓመቱ መጥቶ ሲነግሥ እንጂ አኹን አይቻልም ብለው የሚያስተምሩ “ተላላና ጸጋ አራካሾች” አሉ። ነገር ግን አዎ! ይቻላል ብዬ እነግራችኋለሁ፤ ጌታችን ኢየሱስ ስለ በደሉት እንደ ማለደ በቅዱሳት መጻሕፍት አንብበናል (ሉቃ. 23፥34)፤ ልክ እንዲኹ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ የኢየሱስን ዐሠረ ፍኖት በመከተል፣ በድንጋይ ይወግሩት ለነበሩት ጠላቶቹ፣ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።” (የሐ. ሥ. 7፥60) ብሎአል።

በሌላ ስፍራም ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፣ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።  (1ጴጥ. 2፥21)፣ “ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤” (ሮሜ 12፥20)። ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር መንግሥት እውነት ነው፤ ኢየሱስን ለምንከተል ይህ የታዘዝነው ታላቅ የጽድቅና የፍቅር ሕግ ነው፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በዚህ ሕይወት እንድንመላለስ ጌታ ጠርቶናል።

በዚህ ረገድ በዘመናችን ክርስትናችን የለዘዘ፤ መንፈሳዊነታችን የጠወለገ ይመስላል፤ አገራችን ደግሞ በቂምና በጥላቻ በቁሟ ተበልታ ልታልፍ በቋፍ ያለች ይመስላል፤ ጌታ ይራራልን፤ መንፈስ ቅዱስ በጥላቻ፣ በቂም፣ በዘረኝነት፣ በቡድንተኝነት፣ በጎሳና በዘር ከተያዝንበት ጥቁርና ድቅድቅ ጠላትነት ነጻ ያውጣን፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment