Friday, 10 March 2023

የ“ምኵራብ” አገልግሎት ቢቀጥልስ?

 Please read in PDF

የምኵራብ አገልግሎት፣ ባቢሎናዊው ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ የአይሁድን መቅደስ አፍርሶ፣ ሕዝቡን ማርኰና አፍልሶ ወደ ባቢሎን ሲወስድ፣ ሕዝበ እስራኤል ከአምልኮ ማዕከል ከኢየሩሳሌምና ከመቅደሱ ፍጹም በመራቃቸው፣ ለጸሎትና ለማኅበርተኛነት ልዩ ቤት(ምኵራብ) መሥራትንና በዚያ ጸሎትና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለማምለክ ምኵራቦችን አስቀድሞ በባቢሎን ኋላም ደግሞ በኢየሩሳሌም መሥራት እንደ ጀመሩ ይታመናል፤ (ሕዝ. 11፥16)።[1]

ምንም እንኳ እስራኤል እንደ ደንበኛው አምልኮ፣ በምኵራቡ ውስጥ መሥዋዕትን ባያቀርቡም፣ ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና መተርጐም ብሎም በዚያ መጸለይን ያዘወትሩ ጀመሩ። ምኵራብ ለመሥራትና ምኵራባዊ አገልግሎትም ለመመሥረት፣ ዐሥር ጐልማሳዎች በአንድ አከባቢ ካሉ፣ አንድ ምኵራብ በመሥራት የጋራ አምልኮ ይፈጽሙ፤ ኅብረትም ያደርጉበት ነበር።

የእስራኤል ቅሬታዎች ይህን በማድረጋቸው፣ የኪዳኑን ቃላት አልዘነጉም፤ ያህዌ ኤሎሂም ለእነርሱ የሰጣቸውን ተስፋዎች ከማሰላሰል ቸል አላሉም፤ ምድረ ርስትን አልረሱም፤ በኅብረት መያያዝን አልጣሉም፤ በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና በማንበብም ማምለክን አልሰለቹም፤ ይልቁን ተጉ፤ በረቱ፤ ጨከኑ፤ የያህዌ ተስፋ እስኪፈጸም በብርቱ መቃተት ቃተቱ!

ይህን የምኵራብ አገልግሎትን የሚመስል አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ እንደ ነበረ የሚያሳዩ ዋቢዎች አሉ፤ አንዳንዶች በታሪክ ጥናታቸው በአባ ሰላማ ወይም ፍሬምናጦስ እንደ ተጀመረ ሲያወሱ፣ ሌሎች ደግሞ በደቂቀ እስጢፋኖሳውያን መጀመሩን ይናገራሉ። አቡነ ጐርጐርዮስ፣ “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ፣ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ ካህናት የንስሐ ልጆቻቸውን በያሉበት መንደር ሄደው “ወንጌል” ሊያስተምሩ እንደሚገባ አዝዘዋል ብለው ጽፈዋል።

ያም ኾነ ይህ፣ ምኵራባዊ አገልግሎት ከዋናው የመቅደስ አገልግሎት በቁጥር አነስ ያሉ አማኞች የሚገናኙበትና አብረው በአንድነት አምልኮ የሚፈጽሙበት ዐውድማ ነው፤ በተሐድሶአውያን ዘንድ በተለምዶ የማኅደር አገልግሎት ተብሎ የሚጠራም ነው። ይህም ማለት በአንድ አከባቢ ያሉ አማኞች፣ ቁጥራቸው ከኹለት እስከ አሥራ ኹለት የሚጠጉ ኾነው፣ በአንድነት በአከባቢያቸው ባለ አንድ ስፍራ ተገናኝተው የሚጸልዩበት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነብቡበትና የሚያጠኑበት ነው።

ይህ እጅግ ብዙ ጥቅም አለው፤ ለምሳሌ፦ አማኞች ለአምልኮ የሚገናኙት በእሁዱ ወይም በተመረጡ ቀናት ብቻ አይደለም፣ ጸጋ ይከፋፈላሉ፣ ማን ምን ጸጋ እንዳለው ያስተውላሉ፣ በችግሮቻቸው ይወያያሉ፣ ይረዳዳሉ፣ ኅብረት በማድረግ ለእግዚአብሔር ክብርን ያመጣሉ፣ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ያጸናሉ … ወዘተ።

እናም እንደ አይሁድ ያለ፣ ወንጌል የምናጠናባቸው፣ የምንጸልባቸው፣ ጸጋ የምንከፋፈልባቸው … ክርስቲያናዊ የምኵራብ አገልግሎቶች ቢኖሩንና ብንጠቀምባቸውስ? ቢስፋፉስ? …

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።



[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 60

No comments:

Post a Comment