Saturday 18 March 2023

ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ ትመሰክራለህን?

 Please read in PDF

“ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤” (ሮሜ 10፥9)

ይህን ቃል የተናገረው ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፤ የተናገረውም ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ነው። ሐዋርያው ይህን ምስክርነት የሚመሰክረው የመዳንን ታላቅና ብቸኛ መንገድ እያመለከተ ባለበት ክፍል ነው። በሮም ምድር የቄሳር ጌትነት ገንኖ ይነገር ነበር፣ አማኞች ግን የኢየሱስን ጌትነት በመመስከር ሰማዕታት ኾኑ፤ ምክንያቱም የኢየሱስ ጌትነትን መቀበልና አለመቀበል፣ ከዘላለም ጉዳያችን ጋር የተያያዘ ነውና።

አንዳንዶች የሙሴን ሕግ በመጠበቅ መዳን ይቻላል ይላሉ፤ በርግጥ የሙሴን ሕግ በመጠበቅ መዳን እንደሚቻል ሕጉ፣ “የሚሠራቸው ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራልና ሥርዓቴንና ፍርዴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” (ዘሌ. 18፥5፤ ሮሜ 10፥5) ተብሎአል። ነገር ግን ሕጉን በመጠበቅ መዳን የሚቻለው፣ ሕጉን ያለ ነቀፋና ያለ አንዳች እንከን መፈጸም ለሚቻለው ሰው ብቻ ነው፤ ነገር ግን የሕግ ፍጻሜ ከኾነው ከኢየሱስ በቀር፣ ሥጋ ለባሽ ኹሉ ሕጉን ያለ ነቀፋ መፈጸም አልተቻለውም፤ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤” እንዲል (ሮሜ 3፥9)።

ሌሎች ደግሞ ለመዳን “ወደ ሲዖል መውረድ ይገባናል” ይላሉ (ሮሜ 10፥7)፤ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ የመዳንን መንገድ ያመለክታል፤ እርሱም የክርስቶስን ጌትነት በማመን የሚገኝ የእምነት ቃል ነው ይለናል፤ ይህን የመዳን መንገድ ለማግኘት ወደ ሰማይ መውጣትም አያስፈልግም (ሮሜ 10፥6)፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ሰዎች ኹሉ እርሱን በማመን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ክርስቶስ ኾኖ ተገልጦአል። ወደ ሲዖል መውረድም አያስፈልግም፤ እርሱ ከሙታን መካከል ተነሥቶአል፤ ወደ ሰማይም መውጣት አያስፈልግም እርሱ ወደ ምድር ወርዶ ታላቅ ጽድቅን ሠርቶልናልና፤ አሜን።

ጌታችን ይህን ሥራ የሠራው በጌትነቱ ነው፤ ወደ ሲዖል፣ “ሄዶ በወኅኒ የነበሩ ነፍሳትን ሰብኮአል፤” (1ጴጥ. 3፥19) ደግሞም፣ “በሞት ላይ ኃይል ያለውን ዲያብሎስን በሥጋ ሞቱ  ደምስሶታል” (ዕብ. 2፥14-15)፤ በሰማያትም ቢኾን ቅዱስ አባቱ አብ፣ “ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኃይልና ከጌትነት” (ኤፌ. 1፥21) በላይ “በግርማው ቀኝ” (ዕብ. 1፥3) አስቀምጦታል፤ እናም እግዚአብሔር በሰማይም በምድርም፣ “ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት” (ኤፌ. 1፥22) ለዚህም ነው፣ በሰማያት ለታረደው በግ፣ አራቱ ሕያዋን ፍጡራንና ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች በፊቱ ተደፍተው(ራእ. 4፥8)፣ “ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ የነበሩ መላእክት … በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ” (ራእ. 5፥11፡ 13) በታላቅ ዝማሬ ሲሰግዱለት የምንመለከተው፤ እርሱ ጌታችን ኢየሱስ አዎን በሰማይም በምድር ጌታ ነው! ጉልበት ኹሉ የሚንበረከክለት አንድ ጌታ አለ፤ ኢየሱስ (ፊል. 2፥9-11)።

በዘመናት መካከል የኢየሱስ ጌትነት ርዕስ ያልኾነበት ጊዜ የለም። ርዕስነቱ ደግሞ በኹለት ጐራ ተከፍሎ ነው፤ አንደኛው የሚያምኑትና በነፍሳቸው ተወራርደው ወይም ነፍሳቸውን ሰጥተው ኢየሱስ ጌታ እንደ ኾነ ሲመሰክሩ (የሐ.ሥ. 15፥25-26፤ ፊል. 2፥30)፣ ሌሎቹ ደግሞ ለኢየሱስ ልክ በሌለው ጥላቻ ተሞልተው ጌትነቱን በመቃወም የሚቆሙ ናቸው፤ በኢየሱስ ጌትነት ዙሪያ ከእነዚህ ከኹለቱ ጐራዎች በቀር ሌላ ሦስተኛ ወይም ገለልተኛ የሚባል ጐራ የለም፤ የኢየሱስን ጌትነት ካመንን ወደን እንከተለዋለን፤ በእርሱም ድነን እንቀራለን፤ ጌትነቱን ከናቅነው ግን እንክደዋለን፤ የራሳችንንም ጽድቅ አቁመን ወይ በሲዖል ወይ “በሰማያት” በከንቱ እንንከራተታለን።

እናም ትድኑ ዘንድ በኢየሱስ ጌትነት እመኑ፤ ለመዳንና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የኢየሱስን ጌትነት በአፋችሁ መስክሩ፣ ደግሞም በልባችሁም እመኑ። በልባችን ሳናምን በአፋችን ብንመሰክር ሐሰተኞች ነን፤ በልባችን ያመንነውን በአፋችን ስንመሰክር ደግሞም ጌትነቱ በሕይወታችን ይታይ፤ ስሙ የቅድስናችንና የመዳናችን አዋጅ ምንጭ ይኹን፤ በኢየሱስ ጌትነት በኩል ማንም ምስጢራዊ አማኝ ወይም ክርስቲያን የለም! በአዋጅ እንናገራለን፤ ኢየሱስ ጌታ ነው! አሜን!

No comments:

Post a Comment