Saturday 18 February 2023

የብሔር ተስፋው ምንድር ነው?

Please read in PDf

 እግዚአብሔር አምላክን የምንከተለው ዛሬ የሚታመንና ነገ የሚፈጸም ተስፋ አለው ብለን ስለምናምን ነው። እግዚአብሔርን ብንታመነው የሰጠንን ተስፋ ፈጽሞ ያሳርፈናል፤ “ባናምነው ደግሞ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” (2ጢሞ. 2፥13)፤ እኛ ብንሰናከልና እግዚአብሔርን ብንክድ፣ እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና ታማኝ ኾኖ ይኖራል።

ከክህደታችን ንስሐ ገብተን ብንመለስ፣ ይቅር የሚለንና ተስፋውን የሚፈጽምልን አምላክ አለን፤ ብንክደው ግን ይክደናል፤ ጌታ እግዚአብሔር የማይቀበሉትን ሊቀበል አይችልምና። ተስፋውን የሰጠውና የሚፈጽመው፣ ታምነው ለሚከተሉትና ራሳቸውን አሳልፈው ለሰጡለት ብቻ ነው። ሰማዕታትና ቅዱሳን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ተስፋ ስላመኑ ፍጹም ተከተሉት። አላመነቱም፤ አልተጠራጠሩም፤ አልተግደረደሩም ወደው ተከተሉት!

እግዚአብሔር ለነገ ተስፋ ሲሰጥ፣ ዛሬ ላይ ተስፋውን ሳያስጨብጥ በከንቱ አይደለም፤ ተስፋን የሰጠ የታመነ ነው፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጹም ተስፋን ሰጥቶናል፤ ስለዚህም ራሳችንን በእርሱ ላይ ዥው አድርገን በመጣል እናምነዋለን፤ እንታመነዋለን። እግዚአብሔር ብናጣው የምናጣው ሕይወትና የዘላለም ተስፋን ነው፤ ብናምነው ደግሞ የምናገኘው የሚፈጸም ተስፋና የዘላለም ሕይወትን ወይም ራሱን እግዚአብሔርን እንወርሰዋለን። ስለዚህም እግዚአብሔርን ፍጹም እናምነዋለን።

አብርሃም፣ እግዚአብሔርን አመነ፤ ስለዚህም “ከአገርህና ከዘመዶችህም ወጥተህ ወደማሳይህ ወደ ማንኛውም ምድር ና” (የሐ. ሥ. 7፥3) ሲለው፣ ከቶ አልጠራጠረም፤ ምክንያቱም “መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።” (ዕብ. 11፥10)፤ ስለዚህም ተስፋውን አምኖ፣ እግዚአብሔርን ተከተለ። አብርሃም እግዚአብሔርን በመከተሉ እልፍ፤ ትእልፊት ትርፍ እንጂ አንዳችም ኪሳራ አልገጠመውም።

በዘመናችን ግን ክርስትናን ከተጣባውና አልላቀቅ ካሉ ተውሳኮች አንዱ ዘረኝነትና ጣጣው ነው። እርግጥ ነው ሰዎች ባህል፣ ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ እሴት፣ የተከለለ አገር፣ ድንበርና ብዙ ልማዶች አላቸው። ይህ ተፈጥሮአዊና በዓለም ኹሉ የታወቀ ነው። እኒህ ኹሉ ግን በዚህ ምድር ሳለን ብቻ የምንግባባቸውና እንደ ዕድገታችንና ዕውቀታችን የምንጠቀምባቸው ናቸው፤ ነገር ግን ለነገ የሚሰጡን አንዳችም ተስፋ የላቸውም! እኒህ ኹሉ እንደ ለበስናቸው ልብሶች ያረጃሉ፣ ይኮስሳሉ፣ ይጠፋሉ ብሎም ይረሳሉ።

ሰዎች እንደ ወደዱ እንደሚለብሱት እንዲሁ፣ የወደዱትንና ያደጉበትን ባህልና ቋንቋ ይከተላሉ፤ ይናገራሉ፤ ይህን በማድረጋቸውም ከልካይ የለባቸውም፤ ደግሜ እላለሁ፤ ነገር ግን ለነገ አንዳችም ተስፋ አይሰጡም። ታድያ አንድ ነገር ነገ ላይ የሚሰጠን ተስፋ ከሌለው፣ ለምን እንከተለዋለን? ለነገ ተስፋ የማይሰጥ ከኾነስ፣ ዛሬ ላይ እንዴት እንታመነዋለን? አንድ ሰው ኦሮሞ ወይም አማራ፣ አልያም ከንባታ ወይም ሲዳማ ነኝ ብሎ ቢያምን ወደፊት ምን ይደረግለታል? ባለመኾኑስ ምን ይጐድለበታል? በእግዚአብሔር ፊት አንድ ኦሮሞና አማራ ወይም መንጃና ሂንዱ መካከል ምን ልዩነት አልያ አብላጫ አለ? በመኾናቸው የተሰጠ ተስፋስ አለ? አንዱን ኾነን ሌላውን ባንኾን ምን ይጐድልብናል? ምንስ ይጨምርልናል? እንኪያስ የሚያመጣውም ኾነ የሚያስገኘው ነገር ከሌለው በምን አመክንዮና መንገድ ሰው ይጋደልለታል?

ከሰሞኑ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተነሣው “ብሔር ተኰር መገፋፋት”፣ አቡነ ኤርምያስ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ በተሰበሰበው ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፣ እገሌ የተባለው ጳጳስ ከእገሌ ብሔር ነው እያሉ ያብራራሉ፤ እንዲህ መናገር አለባቸው? ብዬ ራሴን ጠይቄአለሁ፤ አይገባም። እንዲህ እንዲሉ ያደረጋቸው ግን ለአገልግሎት የእግዚአብሔር ቃልና እውነት ተሽሮ፣ ብሔርተኝነት አካል ነሥቶ በመቅደስ ስለ ተንጎማለለ ነው፤ ነገር ግን በድፍረት እንዲህ እላለሁ፤ ወደፊት ተስፋ ለማይሰጥ ነገር መቆምና መጋደል፤ መታገልና መድከምን ያህል ምስኪንነትና ሞኝነት የለም።

አማኞች ሆይ፤ በእምነት የአብርሃም ልጆች አልያም አብርሃምን የምትከተሉ ከኾናችሁ፣ እግዚአብሔርን በማመንና በተገባላችሁ ተስፋ ጽኑና እግራችሁን አንሥታችሁ ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ በጽናት ተራመዱ! “ይህን መመሪያ ለሚከተሉ ኹሉና የእግዚአብሔር ወገኖች ለኾኑት እስራኤላውያን ሰላምና ምሕረት ይሁን።” (አት) አሜን።

No comments:

Post a Comment