Friday 10 February 2023

“ሰላም ለኹላችሁ ይኹን”

Please read in PDF

ይህን ቃል የተናገረው ናዛዜ ኅዙናን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንም ቃል የተናገረው ለተወደዱ ደቀ መዛሙርቱ ነው፤ ጊዜውም ደግሞ እርሱ በሥጋ ሞቱ በአይሁድ እጅ ከተገደለ በኋላና በመቃብር ተቀብሮ፣ ደቀ መዛሙርት ኹላቸውም በፍርሃት ቆፈን ውስጥ፣ “በመሸ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።” (ዮሐ. 20፥19)።

ደቀ መዛሙርቱ እጅግ ፈርተው በአንድ ቤት ተሰባስበው በነበረበት ቀን፣ በሰማይና በእግዚአብሔር መላእክት ዘንድ ታላቅ ደስታ፣ በሰይጣንና በሞት ግዛት ውስጥ ታላቅና ፍርሃትና መደንገጥ ነበር። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱን በፍርሃት ውስጥ በነበሩባት በዚያች ቅጽበት፣ አሃዜ ዓለማት መድኅን ክርስቶስ ከሙታን መካከል፣ የሞትንና የኀጢአትን ኀይል ሰብሮ፣ የሲዖልና የገሃነምን ደጆች ሰባብሮ፣ መቃብርን ድል ነሥቶና ሙስናን አጥፍቶ ተነሥቶአልና።

አይሁድን ፈርተው ደጆቻቸውን ዘግተው በውስጥ የተቀመጡት ደቀ መዛሙርት፣ አይሁድ የሰሙትን የክርስቶስን ከሙታን የመነሣት የድል ዜና ሳይሰሙ ቀርተዋል፤ ከዚህ ባሻገር አይሁድ፣ የክርስቶስን ከሙታን መካከል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመነሣቱን ዜና ለማስተባበል አዲስና የፈጠራ ውሸት እያወሩ ነበር፤ “የአይሁድ ካህናት … ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው፣ እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ።” (ማቴ. 28፥12-13) ብለው ሲዶልቱ ነበር።

የካህናቱና የሽማግሌዎቹ ትልቁ ፍርሃት፣ እውነት የኾነውን ኢየሱስንና ሥራውን በሐሰት ትርክትና ወሬያቸው ማስተባበል፤ መካድ ብሎም ሌሎች ሰዎች እንዳይቀበሉ ማድረግ ነው፤ ይህ የገዛ ክፉ ሥራቸውም ሰላም ነሥቶአቸዋል፤ ዕረፍት አሳጥቶአቸዋል። ምናልባትም ደቀ መዛሙርቱ ይህን እውነት ማውራት ሳይጀምሩ በአጭሩ ለማስቀረትም በማሰብ፣ ደቀ መዛሙርትን ለማሰርና ለመግደል መፈለጋቸው አይቀሬ ነው። በዚህ ኹኔታ ውስጥ ነው፣ ጌታችን የተወደዱ ደቀ መዛሙርትን ባሉበት ቦታና ኹኔታ ውስጥ፣ “ሰላም ለእናንተ ይኹን” አላቸው!

አዎን፤ አሜን፤ በፍርሃትና በመልፈስፈስ፣ በጥርጣሬ ማንነትና ኹኔታ ውስጥ ላሉ ኹሉ ሰላም ይኹን። “ምን እንኾን ወይም ምን ይኾን?” እያሉ ላሉ ኹሉ የክርስቶስ ሰላም ይኹንላቸው! ጌታችን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርት አስቀድሞ፣ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም።” (ዮሐ. 14፥27) ብሎ ነግሮአቸዋል፤ የተስፋና የኪዳን አምላክ እንደ ተናገረው ቃሉ “ሰላም” አላቸው። በመከራው ሰዓት፣ በጭንቁ ሌሊት፣ በስቅለቱ ጊዜ ጥለዉት ስለ ሄዱ አልተቀየማቸውም፣ አልተቈጣቸውም ይልቁን እንደ ብርቱ ወዳጅ ተጠጋግቶአቸው አጽናናቸው፤ አበረታታቸው!

የእርሱ ሰላም አስደናቂ ሰላም ነው፤ እኛ ሰላም ከምንለው ቃል ያልፋል፤ ዓለም በኹናቴዎች ላይ ተንተርሳ እንደምትለው አንጻራዊ ሰላም አይደለም፤ የእርሱ ሰላም ኹለንተናዊና ፍጹም ነው፤ በሚናወጠውና በሚታወከው ዓለም ላይ፣ ምንም ያልተፈጠረ ያህል የኢየሱስ ሰላም አዘልሎ፤ ዘና አድርጐ ያስቀምጣል፤ የሰላም አለቃ (ኢሳ. 9፥6) የኾነው የክርስቶስ ሰላም፣ “እንደ ወንዝ ጽድቁም እንደ ባሕር ሞገድ” ነው፤ (ኢሳ. 48፥18)፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ለልጆቹ የሚሰጠው ሰላም፣ ዓለም እንደሚሰጠው ያለ ሰላም አይደለም፤ ፍጹም ልዩ ነው፤ ይህን ሰላም የሚያገኙት የኀጢአት ሥርየትን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያመኑ ብቻ ናቸው፤ ይህ ሰላም፣ ተራ የአእምሮና ሥነ ልቡናዊ መረጋጋት አይደለም፤ በመጽሐፍ እንደ ተነገረ፣ አእምሮን የሚያልፍ ወይም ከማስተዋል በላይ የኾነ፣ ከሥላሴ ጋር በመታረቅ የተገኘ ፍጹም ሰላምና ጸጥታ ነው፤ (ፊል. 4፥7)።

ዓለማችን፣ አገራችንም ጨምሮ በብዙ ነገር ሰላሟን አጥታለች፤ ዓለም ሰላም እንዳትኾን የሚሹት ሰይጣንና ሰዎች በአንድነት በመተባበር ነው፤ እናም ሰላም አልባ ለኾነችውና ዕረፍት ለሚያሻት ዓለማችን መልእክታችን አንድ ነው፤ “የክርስቶስ ሰላም ለእናንተ ይኹን” የሚል ነው፤ ምክንያቱም፣ “ኹለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ[ክርስቶስ] ራሱ ነውና፤” (ኤፌ. 2፥14 ዐመት)። አሜን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment