Wednesday, 13 July 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፰)

Please read in PDF

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የወንጌላውያን ትምህርት

ከምዕራባውያን መካከል ከካቶሊካውያን በ16ኛው ምዕተ ዓመት የተለዩት ወንጌላውያን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣንና ትውፊት በተመለከተ “Sola Scriptua - መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚል ጽኑ አቋምን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ፣ “እንከን አልባ ለሰው ልጅ ብቸኛው መዳኛና የሕይወታችን መመሪያና የኹሉ ነገር ዳኛ” የሚል አቋምን በውስጡ የያዘና፣ ይህንም ብርቱ ሥልጣን ከመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ያገኘ መኾኑን ሲናገሩ፣

“ … መጽሐፍ ቅዱስ ‘ቅዱስ’ የተባለው እንከን የማይወጣለት፥ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያረፈበትና የመንፈስ ቅዱስ ውጤት ስለኾነ ነው። … የእግዚአብሔር እስትንፋስ ምሪት ምሉዕና ፍጹም ከኾነ፥ መጽሐፍ ቅዱስም በምሉዕ ምሪት የተጻፈ ፍጹም የእግዚአብሔር እስትንፋስ ያለበት መጽሐፍ ነው። … አንዲት ፊደል ትኹን ወይንም ነቁጥ እርሷ በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነች። እዚያ እንድትኾን የጻፋትም ሰው በእርግጥ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ ነው።”[1]

“የብሉይ ኪዳንንም ኾነ የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ሥልጣን መቃወም የክርስቶስን ሥልጣን መቃወም ማለት ነው። በከፍተኛ ደረጃ ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የምንገዛው ለኢየሱስ ክርስቶስ የጌትነት ሥልጣን ለመገዛት ስለ ወሰንን ነው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን መገዛት ለዕለታዊ የክርስትና ሕይወት አኗኗር ወሳኝ ነው፤ ያለዚያ ክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት፥ ክርስቲያናዊ ታማኝነት፥ ነፃነጽና ምስክርነት ሙሉ ለሙሉ ባይወድሙም እንኳ ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው አይቀሬ ነው።”[2]

“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቃለሉት መጻሕፍ የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ እልባት ያገኘው በማንኛውም የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ምርጫ አልነበረም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ያሉትን 66 መጻሕት በመምረጡ በኩል፥ መንፈስ ቅዱስ በተሞሉ አማኞች አማካይነት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሥራውን ይሠራ ነበር።”[3]

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣኑ

ለመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የሚገዙ አማኞች፣ መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ እግዚአብሔር መኾኑን ቅንጣት ታህል አይጠራጠሩም። መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነትና ለተግባር ብቸኛው መሠረት እንደኾነም ጭምር። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን፣ ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው (2ጴጥ. 1፥21)፣ “በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የጻፉት ነውና” (2ጢሞ. 3፥16)። ከእግዚአብሔር በተተነፈሰ እስትንፋስ ተጽፎአልና መጽሐፍ ቅዱስ የራሱ የእግዚአብሔር ቃል ነው። “ጳውሎስ ማለት የፈለገው፣ አኹን በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የምናገኛቸው ቃላት ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የፈለቁ ናቸው ለማለት ነው።”[4] የመጽሐፍ ቅዱስን ሥራ በቅዱሳን ሰዎች አማካይነት፣ መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ ያከናወነው፣ “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና” ነው፤ (ዕብ. 1፥1)።

አስደናቂ በኾነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ተያያዥነት ያላቸው ስድሣ ስድስት መጻሕፍት በአንድ ላይ መያዙና የተጻፈው ቃሉ ኹሉ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ለመጻፉ ቋሚ ማስረጃ መኖሩን የሚያመለክት ነው።[5] ቅዱሳት መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ ሥራ መገኘታቸው፣ ለሰው እምነትና አኗኗር ጥቅማቸው ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም በእነርሱ አማካይነት፣ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥” እጅጉን ይጠቅማሉና።[6] ከዚህም የተነሣ እንዲህ ደፍረን መናገር እንችላለን፤ ቤተ ክርስቲያን ለመጽሐፍ ቅዱስ ታስፈልገዋለች ሳይኾን፣ ለቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስፈልጓታል።

“ቅዱስ መጽሐፍ በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈ ስለ ኾነ ዘመን አይሽረውም፤ ዓላማውንም ጊዜ አይለውጠውም፤ ጥቅሙም ለተወሰነ ማኅበር ወይም ለግል ሰው አይደለም፤ ዓላማው ቀዋሚ የኾነ ሕጋዊ መጽሐፍ ነው። በቅዱሱ አምላክ ወደ ሰው የተላለፈ ስለ ኾነ ቅዱስ የሚለውን ስም ገንዘቡ አደረገ። … እንግዲህ ቅዱስ መጽሐፍ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፈ ስለ ኾነ ፍጹም እውነት ነው፤ ከቶ ሊለወጥ፣ ሊጨመርበትም፣ ሊቀነስበትም የማይገባ መጽሐፍ ነው (ማቴ. 5፥18)።”[7]

“ … እነዚህም መጻሕፍት ከሌሎቹ ኹሉ ተለይተው “መጻሕፍተ አምላካውያት” ይባላሉ፤ ምክንያቱም የአምላክን ነገር የሚናገሩ የአምላክ ቃል የተጻፈባቸው ስለ ኾኑ ነው። እነርሱም የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው። አሥራው መጻሕፍትም ይባላሉ፤ ይህም ማለት ብሉይና ሐዲስ ለቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ኹሉ ሥር መሠረት ስለ ኾኑ …”[8] ነው። እኛም በእውነት እንዲህ እናምናለን፤ ደግሞም እንታመናለን።

እንግዲህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን፣ የታመኑት “ኦርቶዶክሳውያን አባቶች” እንዲህ መጻፋቸውን ስናስብ እንደነቃለን። የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊም እንዲህ ያለውን እውነት እያመነታም ወይም እያደፈረሰም ቢኾን መጻፉ ይገርመናል። ከዚህ ባሻገር የመድሎተ “ጽድቅ” ጸሐፊ በመግቢያው ላይ እንዳመለከተው[ገጽ 17]፣ የስህተት ትምህርትን ለመመዘን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሳይኾን፣ ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባሻገር ሌሎችም መጻሕፍትንም ጭምር ሲናገር እንሰማዋለን፤ ነገር ግን በፊት ገጹ ምስል፣ ስህተት ያላቸውን መጻሕፍት፣ በሌሎች መጻሕፍት እንጂ በቅዱሳት መጻሕፍት ሲመዝን አልያም ሲዳኝ አይታይም

የመድሎተ ጽድቅ አንድ ፍጹም የተሳሳተው ነገር ቢኖር፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በቀር የእግዚአብሔር ቃል የሚባል ሌላ መጽሐፍ ፈጽሞ እንደ ሌለ አለማስተዋሉ ነው። ምክንያቱም ማናቸውም መጻሕፍት[ሐዋርያውያን አበውም ኾኑ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፉት] በቅዱሳት መጻሕፍት ይመዘናሉ እንጂ ራሳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሌሎችን ጽሑፎችን ሊመዝኑ የሚቻላቸው አይደሉም። ለዚህም ነው የአበው መጻሕፍት ራሳቸው ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሩናል እንጂ ራሳቸውን ከቅዱሳት መጻሕፍት አያስተካክሉም።

ልዩ (ባዕድ) ቃል ወደ ልባችን እንዳይገባ ቃላተ መለኮትን (ቅዱሳት መጻሕፍትን) ማድመጥ ይገባናል።”[9]

ይቀጥላል …


[1] B.H. Carroll, Inspiration of the Bible (Newyork, Chicago, London, Edinburgh: Fleming H. Revell Co., 1930), p. 55 ff.

[2] John R.W. Stott, The Authority of the Bible (Downers Grove, IL: Inter-Varsity Press, 1974), pp. 30,40

[3] ቢሊ ግሬሃም፤ መንፈስ ቅዱስ፤ 1977 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ SIM ማተሚያ፤ ገጽ 38

[4]  ክርስቶፈር ጄ. ኤች. ራይት፤ ከማር የጣፈጠ፤ 2011 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ርኆቦት አታሚዎች፤ ገጽ 5

[5] ተክሉ መንገሻ(ተርጓሚ)፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዋና ጭብጦች፤ 2003 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ላፕሲሊ ክሩክስ ፋውንዴሽን ፤ ገጽ 19

[6] ኮሊን ማንሰል(ቄስ)፤ ትምህርተ እግዚአብሔር፤ 2007 ዓ.ም 2ኛ ዕትም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ 67

[7] ሀብተ ማርያም ወርቅነህ(ሊቀ ሥልጣናት)፤ ትምህርተ ክርስትና፤ 1979 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 58፤ 61

[8] አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፤ ገጽ 54

[9] ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፤ ተግሣጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፤ 1987 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት። ገጽ 92


3 comments:

  1. You just telling that "the protestant church where you live is dying and decaying." What about the Orthodox churches where the place that you are living? do they growing? absolutely not. Look friend, the majority of the young generation in Ethiopia and here in US are living the Orthodox church Just because the they are looking for the son of God. you may be amazing in the near future, when Thadiso control the Orthodox church (wodedekem telahme) wheather you like it or not.

    ReplyDelete
  2. በመስቀል ላይ የተሰቀለው የወላዲት አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ጌታ ብቻ አይደለም። ሁሉንም ጌቶች የፈጠረ አምላክ ነው። የጌቶች ሁሉ ጌታ ነው።

    ReplyDelete
  3. Praise our precious Lord Jesus🥰🙏🏻💙💜

    ReplyDelete