Saturday 9 July 2022

“ራስህን ለካህን አሳይ”፣ ብሉያዊ ወይስ አዲሳዊ?

Please read in PDF

“ኀጢአትን ለካህን ለመናዘዝ ይገባል” ለማለት የሚከራከሩ ሰዎች፣ ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች መካከል ይህ ቀዳሚው ነው። ክፍሉ በቀጥታ እንዲህ ተብሎ በጌታችን ኢየሱስ ተነግሮአል፤ “… ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” ጌታችን ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ ከለምጽ ለነጻው ለምጻም ሰው ነው፤ (ማቴ. 8፥4፤ ማር. 1፥44፤ ሉቃ. 5፥14)። ጌታችን ይህን ለምጻም እንዲህ ብሎ ለምን እንዳዘዘው ከመናገር፣ አስቀድሞ አንድ ሰው ለምጽ ሲወጣበት ስለሚደረገው ብሉያዊ ሥርዓት በአግባቡ መረዳት ነገሩን ለማስተዋል እጅግ ይቀላል።

ለምጻም በብሉይ ኪዳን (ዘሌ. 13፥2፤ 5፥2)

በለምጽ መወረስ እጅግ አሰቃቂ በሽታ ነው (ሉቃ. 5፥12)፤ በለምጽ የተያዘ ሰው አስቀድሞ ገና ምልክቱን እንደ ተመለከተ ወደ ካህኑ ይመጣል፤ ምናልባት ፍጹም ከመገለሉ በፊት፣ ካህኑ በታየው ምልክት ላይ አክብቦ ለሰባት ቀን ያገልለዋል፤ በሰውየው ላይ የታየው ምልክት ለምጽ ካልኾነ፣ ወዲያው ወደ ሕዝቡ ይመልሰዋል። “ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ፦ ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል።” (ዘሌ. 13፥6) እንዲል፣ ወደ ሕዝቡ ይመለሳል።

ነገር ግን “በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። ካህኑም ያያል እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ፦ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው።” ብሎ ያገልለዋል (ዘሌ. 13፥8)። የመገለሉ አንደኛው ምክንያት ተላላፊ በሽታ ከኾነ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ በሽተኛው በአንድ ቦታ ተገልሎ ይቀመጣል። ኹለተኛው ምክንያት ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የመጣ ከኾነ የመንጻት ሕግ ሥርዓትን እስኪፈጽም ተገልሎ ይቀመጣል።

ይህ ሰው በካህኑ አዋጅ እንደ ተገለለና እንደ ተለየ፤ ሲፈወስም በካህኑ አዋጅ ማለት መንጻቱን መስክሮለት ነው የሚመልሰው፤ ሲመልሰውም መሥዋዕትን አቅርቦለት ያነጻዋል። “ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኵሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ በኋላም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል።” (ዘሌ. 14፥19) እንዲል ከዚያ በኋላ ሰውየው ከመሥዋዕቱና ከካህኑ ምስክርነት በኋላ ወደ ሕዝቡ በአዋጅ ይመለሳል።

ለምጽና ሌሎች በሽታዎች በአዲስ ኪዳን

ለምጽም ኾነ ማናቸውም በሽታ ያለበት ሰው በአዲስ ኪዳን ትምህርት፣ እንደ ኀጢአተኛ ወይም እንደ ርኩስ ሰው አይቆጠርም፤ በነገራችን ላይ ለምጽ ብቻ ያይደለ በብሉይ ኪዳን ወንድም ኾነ ሴት፣ ከሰውነታቸው ፈሳሽ የሚወጣ ከኾነ (ለምሳሌ፦ የወር አበባ፣ መግል ያለው ቁስል፣ ለሃጭ የሚያዝረበርብ …)፣ እሬሳ መንካትና ሌሎችም ተግባራት እንደ ርኩስ ያስቆጥሩ ነበር። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን የወር አበባም ኾነ ለምጽ፣ እሬሳ መንካትም ቢኾን አያረክሱም። አልያም እነዚህ ነገሮች የሚገጥሟቸው ሰዎች የሚያቀርቡት የእንሰሳት መሥዋዕቶች ዓይነት የለም።

ታዲያ ጌታችን ኢየሱስ ይህን ያደረገው ለምንድር ነው?

1.   ጌታችን ይህን ሰው እንዲህ ብሎ በማዘዙ ራሱ ጌታችን ሕግ እየጠበቀና ሰውየውም ሕግን እንዲጠብቅ እያደረገው ነው፤ የመሥዋዕትና የመንጻትን ሕግ ሥርዓት እየፈጸመ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ደሙን በማፍሰስ የእንሰሳቱን መሥዋዕት ገና አልሻረምና፣

2.   ለመፈወሱ ተጨማሪ ማረጋገጫና ምስክር እንዲኖረው እያደረገ ነው፤ መሥዋዕት ማቅረቡ የፈውሱን እውነተኛነት የሚያረጋግጥ ነው። ይህም ለምጽን መፈወስ የሚቻለው ያህዌ ብቻ ነው ብሎ ለሚያምነው ማኅበረ ሰብ (2ነገ. 5፥1-14) የኢየሱስ ፍጹም አምላክነትም በአብሮነት መገለጡን እንመለከታለን።

3.   በለምጹ ምክንያት የተገለለውን ሰው፣ ወደ ማኅበረ ሰቡም እንዲመለስና እንዲዋሐድ እያደረገው ነው። ሰውየው ለረጅም ዓመታት በሰውነቱ በነበረው ለምጽ ምክንያት በመገለል ኖሮአል፤ ነገር ግን አኹን በኢየሱስ ርኅራኄና ሃዘኔታ ተፈውሶአልና ወደ ሕዝቡ ለመመለስ የካህኑ ምስክርነትና መሥዋዕት ያስፈልገው ነበር።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ለምጻም የተናገረበት ዋናው ምክንያት ይኸው ነው እንጂ፣ ኀጢአቱን ለካህን መናዘዝ እንዳለበትና ንስሐ ለመግባትም ኀጢአትን ለካህን መናዘዝ ይገባል የሚለውን እንግዳ ትምህርት ሊያስተምር አይደለም። ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚጠቅሱ ሰዎች እንደዚህ ለምጻም፣ የእንሰሳትን መሥዋዕት ሲያቀርቡ አናስተውላቸውም፤ ስለዚህ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃላትና ሐረጎችን ከዐውዳቸው ነቅለን “ለትምህርታችን” ከመጠቀም እንጠንቀቅ።

ነገር ግን ኀጢአትን በተመለከተ፣ በክርስቶስ ለምናምን ለኹላችን አንድና የታመነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ለእርሱም ብቻ ኀጢአታችንን እንናዘዛለን። መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፣

እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” (ዕብ. 4፥14-16)።

አዎን የእኛ ሊቀ ካህናት፣

-       ድካማችንን፤ ኀጢአታችንን ያውቀዋል፤

-       በድካማችንም ይራራልናል፤

-       ደግሞም በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ ይሰጠናል፤ ስለዚህም ዘወትር ለምንደክም ልጆቹ ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቀርባለን፤ አሜን።

4 comments:

  1. በዙፋኑ ላይ ሆኖ በለበሰው የእኛነቱ ያለማቋረጥ የእለት ተእለት በደላችንን በአስታራቂነት ሀይሉ የሚያስወግደው ጌታ የመንፈስ ቅዱስን ሐብት በዘመንህ ሁሉ ያብዛልህ። ስለ አለሙ መዳን የታረደው የነጩ በግ (የኢየሱስ) ማዳን እንኩዋንስ በእነዚህ መጨረሻቸው ጥፋት፤ ሆዳቸው አምላካቸው፤ ክብራቸው በነውራቸው ሀሳባቸውም ምድራዊ በሆኑና አማልክቶቻቸው በበዙ ወሮበሎች ቀርቶ አለሙን በምድራዊ ስልጣናቸው ባንቀጠቀጡትም ቄሳሮች ሊገታና ሊቆም አልቻለም። ክብር ለብቸኛው መድሀኒት በጸጋ ላይ ጸጋን ላበዛልን ከመለኮቱ ሳይለይ በፈቃዱ እኛን ሆኖ ከሁለት ሞት ወደዘለአለም ሕይወት ላሸጋገረን ይሁን። ይህን ላልተረዱትና መድሀኒት ፍለጋ አማልክቶቻቸውን ላበዙትም የተስፋን(የማስተዋል) ልብ ይስጣቸው እላለሁ።

    ReplyDelete
  2. ጎበዝ በጣም ግሩም መልዕክት ነው። ቤተክርስቲያናችንን የክርስቶስ ተቃዋሚ ለማድረግ የሚጥሩትን የክርስቶስ ሠምራ አና የዘርዓ ያዕቆብ የልጅ ልጆች የሆኑትን የሸዋዎችን ጨዋዎች መቋቋሚያው ጊዜ አሁን ነው።የቤተክርስቲያናችን ራስ ምንጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

    ReplyDelete
  3. My brother, for you it is very mysterious to know about the mystery of the Holy Trinity. If you really want to know about it you have to ask to the giver of wisdom and knowledge which is the Holy Spirit. And also you have to study the holy bible from the true scholars of the bible. There is no mistaken, saying that, God is one in three and three in one. He is three in name, three in person and three in deed, but when we say they are three in names. . We are not saying there are three gods but One True God. God the Father, God the Son and God the Holy Spirit One true God. We are all baptized in the name of the Father, of the Son and of the Holy Spirit one God. please read Matthew chapter 28:19-20 with understanding and please pray before starting reading it. may the Holy Spirit opens the ear of you heart.

    ReplyDelete
  4. Powerful 🙇🏾‍♀️❤️❤️❤️

    ReplyDelete