Friday 22 April 2022

የኢየሱስን እንጂ የቆስጠንጢኖስን መስቀል አልወደውም!

 Please read in PDF

መስቀል የክርስትና ማዕከልና ዋና ትምህርት ነው። ያለ መስቀሉ ክርስትና ክብር አልባ ትምህርት፣ ሕይወት አልባ ጉዞ ነው። መስቀሉን ማዕከል ያላደረገ ክርስትና፣ ከውኃ የወጣ ዓሳ ያህል አንዳች ትርጕም የለውም። ከውድቀት ዘመን ጀምሮ፣ የሰው ልጆች “የእግዚአብሔር ጠላትና ለእግዚአብሔር ሕግ የማይታዘዙ፣ ለመገዛትም የማይፈቅዱ” የነበሩትን ያህል (ሮሜ 8፥7)፣ እንዲታዘዙና እንዲመለሱ፣ በሕይወትም እንዲኖሩ ጥሪ የቀረበላቸው፣ በታረደውና በመስቀሉ ላይ በተሰቀለው ጌታ “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃ. 23፥34) በሚለው፣ የመስቀል ላይ የጣዕር ድምጽ ነው።

እግዚአብሔር፣ “ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳውም” (ሮሜ 5፥8)፣ አንድያ ልጁን በመስቀል ላይ ነፍሱን አሳልፎ እንዲሰጥ በማድረግ ነው፤ ልጁም፣ “ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።” (ቲቶ 2፥14)፤ ስሙ ይባረክ! እንግዲህ ነፍሱን ለእኛ አሳልፎ ለሰጠውና “በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ለነበረው” (ሉቃ. 22፥44) ጌታና አምላክ፣ እኛም እንድንፈራውና በማክበር እንድንኖርለት ተጠርተናል። “ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤” (ዕብ. 12፥28) ተብሎ እንደ ተጻፈ።

በርግጥም እንድንኖርለት የተጠራነው፣ ለተመሳቀለው እንጨት ሳይኾን፣ በመስቀሉ በኩል ወደ ክብር የገባውን የተሰቀለው ክርስቶስን ነው። መጽሐፍ በግልጥ፣ “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።” (ገላ. 2፥20)። ከክርስቶስ ጋር የተሰቀለ አማኝ፣ ኑሮውና ሕይወቱ የተሰቀለው ክርስቶስ ነው። የምንኖርለት ለሞተልንና ራሱን አሳልፎ ለሰጠልን ለስቀሉና ለመከራ ተቀባዩ መሲህ ነው። የሞተልን እንድንኖርለት፣ የተሰቀለውም እኛ በክብርና በፍርሃት እንድናመልከው ነው።

ዛሬ ላይ፣ ይህ የመስቀሉ ትምህርት በብዙ መንገዶች ወይቦ ደብዝዞአል። ከደበዘዘባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ፣ የመስቀሉ ዓርማና ትምህርት መዛነፉና መኮሰሱ ነው። መስቀሉ በክርስትናው ዓለም የክርስቲያኖች መለያ የኾነበት ምክንያቱ፣ ክርስቲያኖችን ሊያሳፍርና ሊያዋርድ እንጂ ሊያስከብር የሚገባ ታሪክ የለውም። ይኸውም፣ ታላቁ ቆስጠንጢኖስ፣ ከመክስምያኖስ ዲያስ ቄሳር፣ ከሊኒኪዮስ፣ ከማክሴንዲዮስ እጅ ጠቅልሎ ሮማን አንድ አድርጎ ለመግዛት፣ “በጠፈረ ሰማይ ላይ በራእይ ተገለጠለት” ተብሎ፣ ከተጠቀመበት የጦርነት ዓርማ አንዱ “መስቀል” ነው። እናም የ“መስቀሉ”ን ዓርማ በሰይፉ፣ በፈረሱ፣ በግንባሩ፣ በጦር መሣሪያዎቹ ኹሉ በማድረግ የብዙዎችንም ደም በማፍሰስና በጦርነት በመዋጋት፣ ሥልጣኑን አስከብሮ ግዛቱን አስፍቶ ያዘ፡፡ ከዚያም በኋላ  የመስቀል ጦረኞች ጦርነት ሲቀጥልም ምልክታቸው፣ “መስቀሉ” ነበረ። ምናልባትም ብዙዎች ይህን ታሪክ ሲያስተውሉ፣ “ክርስትና ጦረኛ ሃይማኖት ነው” በማለትም ተናግረዋል፡፡ ኢየሱስ ግን የሰላምና የፍቅር፣ የእውነትና የጽድቅ መምህር ብቻ ነው!

ለብዙዎች መዳን በመስቀል ላይ የሞተው ጌታ ተዘንግቶ፣ እርሱ የሞተበት እንጨት ዓርማ ግን ለብዙዎች መጥፋትና መሞት አሳዛኝ ምክንዩ ኾነ። እናም ዛሬም ድረስ፣ ሰዎች የተሰቀለውን መሲሕ ሳይኾን፣ የተሰቀለበትን እንጨት ትልቅ ትርጕምና ዋጋ ይሰጡታል። ዕለት ዕለት ልንሸከመው የሚገባው፣ የክርስቶስ የመስቀሉ መከራና የስሙ ነቀፌታ፣ የሚታፈርበትና የማይፈለግ ኾኖ፣ የእንጨቱ መስቀል ግን እንደ ዋና ዕሴት ተቈጥሮ እንመለከተዋለን። እንግዲህ ወደ ዋናው ነገር እንመለስ፣ ስቅዩንና መከራ ተቀባዩን ጌታ በመውደድና በመከተል፣ በእርሱም በመጽናት ለሞተልን ጌታ እንኑርለት፤ ነቀፋውን ኹሉ ተሸክመን በፍቅርና በመታዘዝ እንከተለው፤ ሰዎች በሰው ሰራሽ ትምህርታቸው ካዘጋጁት “መስቀል” ይልቅ፣ እርሱ የተሰቀለው መሲሕና አዳኝ ቤዛ ኢየሱስ እንድንሸከመውና ተሸክመንም እንድንከተለው ያዘዘንን መስቀል እንኖረው ዘንድ እንውደደው።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

2 comments:

  1. እንዴት ነው የምታስበው ከዚህ በላይ የምለው ስለሌለኝ ለማንኛውም እግዚአብሔር መልካም ልቡና ይስጥህ። "አሜን"

    ReplyDelete
  2. Very interesting article. May God bless your work. Indeed, the Lord Jesus is the bridegroom of the Church. And his bride, the Church, longs for him, chanting MARANATHA (O Lord Come) so that he may come and take her to the Kingdom. For instance, the preparatory service of QEDDASE says: "who has seen a bridegroom who gives his flesh as a meal on the day of his wedding?" This unique bridegroom, is Jesus Christ, the only begotten Son of God, our Redeemer who has freed us from the bondage of the enemy.

    ReplyDelete