Wednesday 20 April 2022

ስለ ወገኔ እንዲህ ብጸልይስ?

 Please read in PDF

ጌታና ቸር የኾንክ አባት ሆይ፤ በአገራችን ላይ ጦርነት እንዳለ፣ ዛሬም ድረስ ሰቆቃው ገና እንዳላበቃ፣ ምጡ እንዳልባጀ፣ ጭንቀቱ እንዳልሰከነ...  ታውቃለህ፤ ደግሞም ይህ ጦርነት የአንድ አገር ሰዎች ኾነን፣ ነገር ግን መዋደድ ተስኖን፣ መፈቃቀር አቅቶን፣ መቀባበል ባንችልበት ነውና እባክህን ትግራዮችንም፤ አማራዎችንም፤ ኦሮሞዎችንም፣ ቤኒሻንጉልንም፣ አፋርንም፣ ሶማሌንም … በጥይት እሩምታ ፍጃቸው፤ በአዳፍኔና በባዙቃ አደባያቸው፤ በጦርና በገጀራ አስወግዳቸው። ነገር ግን ስለ ቅዱሱ ስምህ፣ ስለ ተወደደው አባታዊ ርኅራኄህ ሕፃናቱ አይነኩ፤ ሴቶቹ አይበደሉ፤ አረጋውያኑ አይባዝኑ፣ ባልቴቶቹ አይቅበዝበዙ፤ አካል ጉዳተኞቹ አይሰቀቁ፤ አሮጊቶቹ በበጎ ይታሰቡ፤ ወጣቶቹ በቁመታቸው ልክ አይጋደሙ።

ቸር ጌታ ሆይ፤ ምናልባት ግን እኒህን ኹሉ ማዳን ባትችልና ጸሎቴን ሳትመልስ እኒህን ኹሉ በቦንብ አጋይተህ፣ በእሳት ጢስ አፍነህ፣ በረሃብና በእርዛት፣ በጥምና በጦርነት፣ በአዳፍኔና በድማሚት … በአንድነት ብታጠፋቸው ግድ የለህም እኔ ይቅርታ አልነፍግህም፤ ይቅርታ አደርግልሃለሁ።  ጸሎቴን ባለመመለስህ አልደነቅም፤ አልቆጣምም፤ አልናደድም፤ አልከፋብህም።

አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ ይህን ኹሉ ስታደርግ እኔም እንዲህ ከምትፈጃቸው ሰዎች መካከል መኾኔን አትዘንጋ። እናም ዐደራ የምልህ፣ ኹሉም እንደ ፍጥርጥሩ፤ እንዳሻው ይኹን፣ የምለምንህ ግን ይህ ኹሉ ሲኾን፣ እኔን አንዳችም ጥይት አይንካኝ፣ የቦንብ ድምጽም አያስደንግጠኝ፤  የብዙዎች እንደ ቅጠል መርገፍም አያስፈራኝ። የቅርብም፤ የሩቅም ዘመዶቼን አይንካብኝ፣ ሚስቴን ልጆቼን፣ ጎረቤቶቼን ኹሉ አይሸበሩብኝ። አንዳችም የጥይት ፍንጣሪ እንኳ አይንካኝ፣ ኑሮዬን አያክብድብኝ፣ መንደሬ ሰላም፤ ቤቴ ደህና ይኹን።

 ዳሩ ግን፣ የፍጥረተ ዓለሙ መጋቢና አለኝታ የኾንኸው ጌታ ሆይ፤ ኹለቱንም ጸሎቶቼን ስለማትሰማቸውም አመሰግንሃለሁ፤ አሜን።

1 comment:

  1. This is a good piece; perhaps the best of all I have seen on this site. However, the author is afraid. Mr. Deacon, don't worry much; you have done a good job. No file will be opened against you..just kidding. I have been fasting it with an agenda as the author has suggested; I believe and hope that God will respond positively.

    ReplyDelete