Monday 11 April 2022

እግዚአብሔር፣ ማርያምን ፈርቶ?!

 Please read in PDF

እግዚአብሔር አምላክ እጅግ የተፈራ አምላክ ነው፤ ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ መፈራቱ እንዲህ ይመሰክራሉ፤

   በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንዳንተ ያለ ማን ነው?” (ዘጸ. 15፥11)

      ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው።” (መዝ. 111፥9)

እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ኹሉ መጀመሪያ ነው፤ ደግሞም እግዚአብሔርን መፍራት ከኹሉ ነገር ያወጣል፤ አማኝ በመታመኑም ከኹሉ ነገር ይጠበቃል፤ በሰላምም ይኖራል፤ (ምሳ. 1፥7፤ መክ. 7፥18)፤ ነገር ግን ሰውን ወይም ፍጡርን መፍራት ወጥመድን ያመጣል (ምሳ. 29፥25)። ሰዎችን ስንፈራቸው ሕይወታችንን እስከ መቆጣጠር ይደርሳሉ፤ እናም በኹለንተናችን በእነርሱ አስተያየትና አረማመድ ውስጥ እንድንዘፈቅ ፍጹም በመጫን ያጠምዱናል። እግዚአብሔርን መፍራት ግን ምንም ወጥመድ የለበትም፤ ሳኦል ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን በመፍራቱ ምክንያት፣ ከንግሥና ዙፋኑ የሚያዋርደውን ታላቅ ስህተት ሠራ፤ “ሳኦልም ሳሙኤልን፦ ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ።” (1ሳሙ. 15፥24) እንዲል።

እግዚአብሔር መንግሥቱ የጸና ነውና አንዳችም ፍርሃትና ስጋት የለበትም፤ ቅድስት ድንግልን ጨምሮ ፍጥረት ኹሉ በቅዱስ ፍርሃት ይገዛለታል። እርሱ እግዚአብሔር እጅግ የተፈራ፤ ግሩም አምላክ ነውና። “አንተም ሁሉን ትገዛለህ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው።” (1ዜና. 29፥12) እንዲል። አዎን፤ የአምላካችን ግርማው እጅግ ታላቅ፤ የተፈራም ነው።

እግዚአብሔር የኹላችን ፈጣሪ፤ ከኹሉ የበላይ ነውና እንፈራዋለን፤ የምንፈራው እጅግ ስለምናከብረው ነው። አክብሮታችንም በፍጹም አምልኮ የተመላ ነው። እርሱን መፍራት ኹለንተናችንም ነውና ፈቃዱን በመፈጸም፤ ለትእዛዛቱም በመታዘዝ እንፈራዋለን፤ (መክ. 12፥13)። እግዚአብሔርን በድንጋጤና በመሸማቀቅ አንፈራውም፤ በደስታና ለእርሱ ያለንን ፍቅር በማሳየት እንጂ። እርሱን መፍራታችን በኃጢአት እንደ ታሠረው እንደ ፊልክስ ከጌታ አያርቀንም፤ (ሐዋ. 24፥25)።

ነገር ግን ይህን በመቃረን፣ ሰውዬው(“አባ” ገብረ ኪዳን የተባሉት) ሲቀጥፉ እናያቸዋለን፤ የሰውየው ውሸታቸው ዳርና ጫፍ የለውም፤ ሲናገሩ ከ“ቲቪ ነቢያት” በማይተናነስ ከራሳቸው ሐሰትን አፍልቀው ይናገራሉ። መጽሐፍ፣ ለዲያብሎስ፣ “ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥” (ዮሐ. 8፥44) እንዲል። በቅርብ በለቀቁት ትምህርታቸው እንዲህ ይላሉ፤ “እግዚአብሔር፣ ወደ ማርያም መልአኩ ገብርኤልን የላከው ማርያምን ፈርቶአት ነው፤ ምክንያቱም የሚፈራ ሰው ነውና አማላጅ የሚላክበት” ይላሉ። መቼም የስህተት መምህራን፣ “አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን የሚቃወሙ ናቸው።” (2ጢሞ. 3፥8) እንደ ተባለው ከቅዱስ ቃሉ በትክክል አይናገሩም።

እግዚአብሔር ፍርሃትም፤ ሥጋትም የለበትም፤ የማዳን ተግባሩንም የፈጸመው፣ ዓለምን በመውደዱና እንዲሁ በማፍቀሩ የፈጸመው ነው (ዮሐ. 3፥16)። የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያም ደግሞ፣ እግዚአብሔር ሰውን ስለ ማዳኑ ብቻ ከእርስዋ ሊወለድ የመረጣት ብቻ ናት! እናም ማርያምን በግድ ለማስመለክ የማያልቅ ተረታ ተረት በትውልዱ አትተርቱበት!

1 comment:

  1. ማርያምን በግድ ለማስመለክ የማያልቅ ተረታ ተረት በትውልዱ አትተርቱበት! best

    ReplyDelete