Wednesday 6 October 2021

አትደነቁ!

Please read in PDF

“ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤” (1ጴጥ. 4፥12)

ቅዱስ ጴጥሮስ በአማኞች መካከል እንደ እሳት የሚፈትን ፈተናና መከራ ሊነሣ እንደሚችል በግልጥ ያስተምረናል። የፈተናው መነሻ ደግሞ እዚያው መካከላችን መኾኑንም ጭምር፤ አዎን! ከኢየሱስ ጎን ይሁዳ፣ ከጳውሎስ ጎን ዴማስ፣ ከዮሐንስ ጎን ዲዮጥራጢስ፣ ከኤልሳዕ ጎን ግያዝ … መኖራቸው እንግዳና ልዩ ነገር አይደለም። ዛሬ ላይም እንዲህ ያሉ ወገኖች መነሳታቸው ፈጽሞ አይደንቅም፤ አይገርምም። ገንዘብን ለማካበት መጐምጀት፣ ተሰሎንቄን አይቶ ከቅድስና መልፈስፈስ፣ በወንድሞች ላይ የጐበዝ አለቃ ለመኾን መቋመጥ … ያኔም ነበረ፤ አኹንም መኖሩ አይደንቅም፤ አይገርምምም!

ሰው፣ ከአስተምህሮ ሲዛነፍና ከቅድስና ሕይወት ሲንሸራተት፣ ዘጭ ብሎ ገንዘብን በመውደድ ማነቂያ ሲያዝ፣ አይስቱ ይስታል፤ አይወድቁ ይወድቃል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲህ ያለ ነገር ከመኖሩ ባለፈ፣ እኛን ሲገጥመን የመጀመሪያዎቹ አይደለንም ይላል ተወዳጁ የጌታ መጋቢ፣

“በአስተምህሮ አኳያ ችግር የገጠመን የመጀመሪዎቹ ክርስቲያኖች እኛ አይደለንም፤ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ውስጥ የምንገኘውም እኛ ብቻ አንኾንም። ከአጠቃላዩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዛቢያ ላይ የተነቀለ መንገድ ስለማይኖረን፣ ትርፉም ኾነ ኪሳራው ያገኘናል።”[1]

አዎን፤ በመሲሑ ራሱን የተመታው እባብ፣ ሰኰና ባለመንከስ ዝም ብሎ አይቀመጥም፤ ቤተ ክርስቲያንን በማናቸውም መንገድ መፈተኑ፤ ማበጠሩ አይቀሬ ነው። ያለመፈተን ዋስትና የለንም፤ ይልቁን ፈተናችንና ውድቀታችን የሚከፋው ርቱዕ አስተምህሮና ርቱዕ የቅድስና ሕይወትን ጥለን፣ ዓለማዊና ሰዋዊ ብልሃትን፣ ግለ ክብርን ሽተን፣ ከመስቀሉ ትምህርት የራቅንና የተለየን ጊዜ ነው። ከመስቀል ተፋትተን የሚያገኘን መከራና ፈተና፣ እስከወዲያኛው ሕይወታችንን የሚነሣንና የሚያጠፋን ሊኾን ይችላል።

ታድያ፣ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ሥራ፣ “ወደ ፈተና እንዳታገባኝ” የሚል ጸሎትን ማቅረብ ብቻ አይደለም፤ ይልቁን ሳታቋርጥ ተግታ፣ ጤናማውንና እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በሚገባ ሳትታክት ማስተማር፣ መምከር፣ መገሰጽ  ይገባታል። የተተከልነው በእውነተኛ ትምህርት ከኾነ፣ እውነተኛና የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ማፍራት አንቸገርም፤ ከእውነተኛው የወንጌል ትምህርት ጋር ግን ርቱዐዊ ግንኙነት ከሌለን፣ ፍሬው መንፈሳዊና እውነተኛ ይኾናል ብሎ መጠበቅ፣ ከኩርንችት የበለስ ፍሬን የመጠበቅ ያህል ከንቱ ትጋት ነው።

እናም፣ እንደ ኅብረት የገጠመን ተግዳሮት፣ እንግዳና በእኛ የጀመረ አይደለም፤ መፍትሔ ፈላጊዎችና “አይዞአችሁ በክርስቶስ ያላችሁ በርቱ!” ስንልም፣ እኛ የመጀመሪያዎቹ አይደለንም። እንግዳ ትምህርትና እንግዳ ሕይወትን ገንዘብ አድርገው ጉባኤን የሚያውኩ ትላንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ፤ ነገም ይኖራሉና ልንደናገጥ፤ ልንታወክ አይገባንም። ክርስትና ማመንን ብቻ ሳይኾን፣ በእምነት የተገኘውንም የጽድቅ ፍሬም እጅግ ይሻልና።

አይዞአችሁ በርቱ!

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)

 



[1] ሰለሞን አበበ ገብረ መድኅን(መጋቢ)፤ የደነበረው በቅሎ፤ 2007 ዓ.ም፤ ዐዲስ አበባ፤ ርኆቦት አታሚዎች፤ ገጽ 44

2 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny.May the SPIRIT be your guide and strength for days to come, till your last breath.

    ReplyDelete
  2. ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ ስለ አንተ እግዚአብሔር ይመስገን🙏🙏

    ReplyDelete