Sunday 3 October 2021

የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ተሐድሶና ከዳተኛ ወንድማቸው

Please read in PDF

እስጢፋኖሳውያን፣ የወንጌላውያን ተሐድሶ በአውሮፓ ከመጀመሩ ከዓመታት በፊት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የወንጌል ችቦ እንደ ለኮሱ ይታመናል፤ አንዳንዶች የተሐድሶ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ አጭር ታሪክ ያለው ይመስላቸዋል። ነገር ግን እስጢፋኖሳውያን በኢትዮጵያ ውስጥ አስደናቂና ወንጌላዊ የኾነ ተሐድሶ አሥነስተው ለብዙዎች መዳንና ከጨለማው ዓለም ማምለጥ ምክንያት ኾነዋል። የዚህን ዘመን ክስተት፣ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ታላቅ ዕድል እንደ ነበርና እንዳልተጠቀመችበት የደቂቀ እስጢፋኖሳውያንን ገድል በጻፉት መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ።

“ቤተ ክርስቲያኑን በማገልግል ረገድ አፄ ዘርአ ያዕቆብን የሚወዳደረው ንጉሥ በተጻፈው በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የለም። ለቤተ ክርስቲያኑ ከልቡ አሳቢ ከሆነ፥ ሲሆን ከደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ ጋራ ያደረገውን ዕርቅ[1] ዓይነት ከደቂቀ እስጢፋኖስም ጋራ አድርጎ አብሮ ቢሠራ፥ አለዚያም እንዳላየ ቢያያቸው ኖሮ ምናልባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተአምር ይታይ ነበር። ንጉሡ ደቂቀ እስጢፋኖስን ሲቀጣቸው ክርስቲያኖችን የሚጠሉ ወገኖች አግኝተው እስጢፋኖስን ሲቀጣቸው ክርስቲያኖችን የሚጠሉ ወገኖች አግኝተው እንዲያሠቃዩዋቸው፥ በዚያውም ክርስትናቸው ረክሶ በሰማይም እንዲኰነኑ ቤተ ክርስቲያን ከሌለበት ክርስቲያን ካልሆኑ ሕዝቦች መካከል ወስደው እንዲጥሏቸው ያዝዛል። ብዙ ጊዜ የፈለገው ሆኖለታል፤ የሰማዩ ኵነኔ በነሱ ላይ መድረስ አለመድረሱን ባናውቅም፥ እስላሞቹ ደም በማስተፋት “ቁጣውን አስተንፍሰውለታል።”[2]

ተሐድሶ በኢትዮጵያ ምድር የተለኮሰው በእኛ ዘመን ወይም እኛ በአካለ ሥጋ በምናውቃቸው አገልጋዮች አይደለም፤ ከደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ጀምሮ ያለውን ዘመን ብንቆጥረው እንኳ፣ ከ500 ዓመታት በላይ ይፈጃል። ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን የያዙትን የወንጌል ነበልባል በተለይም፣ [መነኵሴ ሊጸልይና ቃለ እግዚአብሔር ሊያስተምር ይገባል፣ በእጆቹ ሊሠራ ይገባዋል እንጂ ዝም ብሎ ከሰዎች እየተቀበለ ሊበላ ብቻ አይገባውም] በማለት መነሳታቸው፣ ጠላትነትን ከቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥትን በተሻረኩና በተጣቡ ቀሳውስትና መነኮሳት፣ አጋጭና ወሬ አቀባይነት አማካይነት፣ ከመንግሥት ጋር ታላቅ ቅራኔ ውስጥ ገብተው ነበር።

ነገር ግን ተአምረ ማርያምን፣ አምልኮተ ስእልንና ዕጸ መስቀልን፣ ለዘርዓ ያዕቆብ የሚደረገውን ስግደት… በግልጥ መቃወማቸው፣[3] ከነገሥታቱ በተለይም ከዘርዐ ያዕቆብ ጋር በግልጥ አጋጭቶአቸዋል፤ እጅግ አሰቃቂ መከራን በዘመናቸው እንዲቀበሉም አድርጎአል፤ በዚህ ኹሉ ደግሞ ከቶውንም ፈቀቅ ሳይሉ ወንጌልን ሰብከዋል፤ በቅድስና ሕይወት ተመላልሰዋል፤ ሐሰትን በማያቅማማ ቃል ተቃውመዋል። በዚያ ጨለማና ቤተ ክህነት የመንግሥትን ዘንግ ጨብጣ በምትቀጣና እንዳሻት በምትናዝዝበትና በምታዝዝበት ወቅት፣ እኒህ ቅዱሳን ወንጌልን በሕይወታቸውና በትምህርታቸው መስክረዋል።

ይኹንና አብረው የወንጌል ጉዞ ከጀመሩ በኋላ፣ ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉ ብዙዎች በየዘመኑ አሉ፤ እናም ደቂቀ እስጢፋኖስን የጻፉት ፕሮፌሰር ጌታቸው፣ እስጢፋኖሳውያንን ስለ ከዳው ወንድማቸው እንዲህ ብለው ይናገራሉ፤

“ጉዳት ያደረሰው ከዳተኛ ወንድም

ቅዱሳኑ በዚያች ቆገት በምትባል ሀገር ሳሉ፣ ፩ ወንድም እንደ ወንድሞቹ ንጹሕ ሥርዓት መጠበቅ ባለመቻል ከነሱ ተለየ። (እንዲያውም) ሊከሳቸው ወደ ንጉሡ ሄደ። በጠባዩ የሚተባበረው ጓደኛ አገኘ። “በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ጥቂቶች ከዓለም ኃጢአት ከሸሹ በኋላ ዳግመኛ በእርሷ ተጠላልፈው በዚያ ቢሸነፉ የኋላው በደላቸው ከፊተኛው የባሰ ይኾናል። ዐውቀዋት ከጽድቅ መንገድ ከሚመለሱ ይልቅ ባያውቋት ይሻል ነበረ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል በነሱ ላይ እንዲደርስ (ሁለቱ) የሚሠሩትን ተወያዩ። ለንጉሡ ነገሩት።

ንጉሡ ሲሰማ መልእክተኞች ሰጥቷቸው፣ እንዲያመጧቸው አዘዘ። ታዘው ሄዱ። ከወጊ አገረ ገዢ ደረሱ፤ (ንጉሡ) እንደላካቸው ነገሩት። አገረ ገዢው ከብዙ ሠራዊት ጋራ ቀንደ መለከት እያስነፋ (ፍለጋ) ተነሣ። ቅዱሳኑን በየቤታቸው ከበቧቸው። ንብረታቸውን ወሰዱት፤ ቤታቸውን መዘበሩት። እነሱንም ያዟቸው፤ ቊጥራቸውም ፸፰ ነበረ። ወስደው በማነቆ እንደ ታሰሩ (ከንጉሡ አደባባይ) አደረሷቸው። …”[4]

ወዳጆች ሆይ፤ አትናደገጡ!

በየዘመኑ የወንጌልን መንገድ፣ ወንጌልን እየጠቀሱ እውነተኞች እየመሰሉ የሚቃወሙ፣ የሚከሱ፣ ወደ ኋላ የሚመለሱ፣ የማርያምና የመስቀል ወዳድና አምልኮ አስመላኪ ለኾነው አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ወሬ የሚያቀብሉና የሚሰልሉ፣ የሚጎዱ … ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ እነርሱም እጅግ ብዙ ደጋፊዎች እንደሚኖራቸው እናውቃለን። ነገር ግን ወንጌል አይታሠርም፤ ወንጌልን በቅንነትና በእውነት የሚሰብኩ ይታሠራሉ፣ ይገረፋሉ፣ በማነቆ ውስጥም ሊገቡ … ይችላሉ፤ የመንግሥቱ ወንጌል መስፋቱንና መውረሱን አያቆምም!

እናም የዘርዓ ያዕቆብ ደግነትና የማርያም መካከለኝነት ከሚነገርበት ቤት ተመለሱ የምትሉና መንገድ የምታደላድሉ፣ የከዳተኝነት መንገዳችሁን ተዉ ማለትን እንወዳለን፤ አይበጃችሁምና! በወንጌል ጸንተን ያለን ግን እንበርታ፤ እንጽና፤ የጸናውን መሲሕ እንይ፤ በጸናው መሲሕ እውነት ላይ ጸንተው እንደ ደመና ዙሪያችንን የከበቡንን እነርሱን ምስክሮች በማየት የጽዮን መንዳችንን አጽንተን በትእግሥት እንሩጥ!

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)



[1] ደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ ቅዳሜ እንደእሑድ ካልተከበረች ብለው ከኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥለው ነበረ፤ ንጉሡ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ዕርቅ አወረደ፤ Taddesse Tamrat, Church and State in Ethiopia, pp.229-231

[2] ጌታቸው ኀይሌ፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ “በሕግ አምላክ”፤ ካልጅቪል (ሚኒሶታ) 1996ዓ.ም፤ ገጽ.35-36)

[3] ደቂቀ እስጢፋኖስ ገጽ 171፤ 209

[4] ደቂቀ እስጢፋኖስ፤ ገጽ 187


2 comments:

  1. ለእኛ ላመነው ያድነናል አንተ ምን አገባህ አንተ በየ አዳራሹ ስትረገጥ ያላመመክ እኛ በጌታችን እናት መዳናችን አመመክ አይደል ይልቁኑ አሁንም አልረፈደብህም

    ReplyDelete