Thursday 14 October 2021

“ለምን ሄዱ?” አንልም!

 Please read in PDF

(ይህ ጽሑፍ፣ በእውነተኛ ልብ ወንጌልን በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ውስጥ ለማድረስና ለሚሽነሪ አገልግሎት በሕይወታቸው ተወራርደው የሚያገለግሉ ታማኝ አገልጋዮችን አይመለከትም!)

ለምን አንልም?

ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ከውስጥ በሚነሳ አሸናፊነትና “ዘገምተኛ” በኾነ ጽኑ የፍቅር መንገድ የሚያሸንፍ እንጂ፣ በግድና በኃይል ማንንም መያዝና አብሮት እንዲኖር አይፈልግም። ጽድቅን ወዳዱ ጌታ፣ ጽድቅን ያደርግ ዘንድ የምድርን የታችኛው ክፍል በትእግሥት ዝግታ ረግጦ መራመዱ ይህን እውነታ በአድናቆት ያሳየናል! ከዚህ በተቃራኒ ግን “ሰሞነኞቹ”፣ እንደ 1980ዎቹ ትውልዶች፣ “‘እስክንድያ እናቴ’ ኦርቶዶክስ ሃይማኖቴ” ብለው መሄዳቸውን ስናይ ምን እንላለን? ምንም!

ከእኛ ጋር ኹኑ ብለን ግድ አንልም፤ የሚስቱት ደካሞች ብቻ እንዳልኾኑ፣ “የተመረጡት” (ማቴ. 24፥24፤ ማር. 13፥24) እንደ ዴማስና ይሁዳ ያሉት (2ጢሞ. 4፥10፤ ዮሐ. 12፥6)፤ “ይድኑ ዘንድ የእውነትን ፍቅር የማይቀበሉት” (2ተሰ. 2፥9)፣ በሰይጣን መበጠርን ወድደው እምነታቸውን ለማጥፋት የወሰኑት (ሉቃ. 22፥31-32)፣ የሰይጣንን የአታላይነት ዐሳብ የሳቱት (2ቆሮ. 2፥11) … እና ሌሎችም እንደሚስቱና እንደሚወድቁ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይነግረናል።

በእርግጥ አንዳንዶቹ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት፣

1.   አንዳንዶቹ ከፍ ያለ የገንዘብ መውደድ ስላሰከራቸው ሄደዋል፤ በብዙዎች ዘንድ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት፣ በአጭር ጊዜ ሃብታም መኾን እንደሚቻል አስበው መጥተው “ሳይመሽ” የሄዱ ብዙ ናቸው፤

2.   “በተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ የሚደርሰውን ተግዳሮትን መቋቋም ተስኖአቸው መመለስ ፈልገው የተመለሱ ናቸው፤

3.   በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ጨርሶ መሳተፍና አብሮ መኾንን ባለመፈለግ የተመለሱም አሉ።

4.   የተገለጠ ነውርና ርኩሰት ስላለባቸው፣ እርሱን መቋቋም ተስኖአቸው የተመለሱም አሉ። ነውራቸውንም ትክክለኛ ለማድረግም የስህተት መምህራንን ምሳሌ አድርገው ተጠቅመዋል፤ ለምሳሌ፦ ኢዩ ጩፋንና እስራኤል ዳንሳን የወንጌላውያን ተወካይ ማድረጋቸው ሳያንስ፣ ጭራሽ ከእኛ ጋር አንድ አድርገው በማቅረብ፣ ለነውራቸው መሸፈኛ ማድረጋቸው እጅግ ብልሃተኞች መኾናቸውን አሳይተውናል! ስለነዚህ ምንም ማለት አልደፍርም። ምክንያቱም እኒህ በገዛ ነውራቸው በየትም ስፍራ ሊገለጡ አላቸውና።

የሄዱት፤ የሄዱበትን ምክንያትና ግለ ጥልቅ ችግሮቻቸውን ከመናገር ይልቅ፣ መላውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ሲራገሙና ጥቅም አልባ አድርገው፣ ብሎም የወንጌላውያንን ቤተ እምነት “ሲያንኳስሱ” አስተውለናል። ነገር ግን ወደ ኦርቶዶክስ ሲመለሱ፣ የክርስቶስ ኢየሱስን የብቻ ቤዛነትና አስታራቂነት እንደሚቀበሉ፣ በእግዚአብሔር ጸጋና በእምነት ብቻ መዳን እንደሚቻል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም ሥልጣናዊነት በግልና በአደባባይ እንደሚሰብኩ፣ ለታቦትና ለፍጡራን[የጸጋም ይበሉት የአክብሮት] እንደማይሰግዱ፣ የማርያምንና የፍጡራንን መካከለኝነት እንደማይቀበሉ፣ አምልኮተ ስዕልና ንዋያት እንዲሁም በዕጸ መስቀሉ መመካትን፣ ለፍጡራን መዘመርንና ፍጡራንን በምስጋና ማምለክን እንደማይቀበሉ፣ የኀጢአት ሥርየት ከክርስቶስ በቀር በጾም፣ በግል ጥረት፣ በምጽዋት … እንደማያገኙ፣ ይህንም እንደማይቀበሉና ሌሎችንም አስተምህሮዎች ይቀበሉ አይቀበሉ፤ ይመኑ አይመኑ አልነገሩንም። በርግጥም እንዲነግሩን አንጠብቅም፤ ቀድመው ይህ ኹሉ ትምህርትና እውነት እንዳለ ያውቁ ነበርና!

ከሄዱት ይልቅ እኒህ ያስፈሩኛል!

ክርስትና የጸናና የማይናወጥ እውነተኛ ምስክር አለው፤ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ ነው! በሰዎች መውደቅና መነሣት ኢየሱስ አይደበዝዝም፤ ክርስትና አይወድቅም፤ አይጠለሽምም! ክርስትና በትውልድ መካከል ሳይበረዝና ሳይከለስ ጸንቶ የኖረው በቅሪት ቅዱሳን እንጂ በጀማ ወይም በሸንጎ ድምጽ  አይደለም!

“ኦርቶዶክስ እናቴ” ብለው የሄዱት አያሳስቡኝም፤ መርጠው ሄደዋልና። ነገር ግን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ ኾነው፣ በዘረኝነት የተጠላለፉ፣ ጦርነትን የሚደግፉ፣ ገንዘብን በመውደድ የተለከፉ፣ ለስህተት ትምህርት ግድ የሌላቸው፣ ከኹሉም[ከኀጢአት ገበታም ጭምር] ጋር ተመቻችተው ኃጢአትን ባለመጠየፍ የሚቀመጡ፣ ቋሚ ኅብረትና ኅብረት የማያደርጉ፣ የተጋ የጸሎት ሕይወት፣ መጋቢና እረኛ የሌላቸው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የማያነቡና የማያጠኑ፣  የማቆፍሩና የማይፈለፍሉ … እኒህ እጅግ ያስፈሩኛል!

ለሄዱት ምን እናድርግ?

1.   እንጸልይላቸው፦ ለእውነተኛ አማኝ በእግዚአብሔር ፊት ከመናዘዝና ኹሉን ነገር ከማስታወቅ የዘለለ አቅም የለውም! ስለዚህም ስሞቻቸውን ጠርተን በእግዚአብሔር ፊት እንጸልይላቸው! ስለ ወደቁትና ወደ ኋላ ስለ ተመለሱት ብቻ አልልም፤ ይልቅ የበረቱ የምንላቸውም ጭምር እንዳይዝሉ እንጸልይላቸው!

2.   በየውሃት ለማቅናት መጣር፦ ኢየሱስን ስንጠራ እንደሚቀልዱብን ብናውቅም፣ እንደ ተሳሳትን ደጋግመው ቢነግሩንም፣ ነገር ግን ባይሰሙንም መሲሑን መናገርን መተው የለብንም! ቢሰሙን ይጠቀማሉ ባይሰሙን ደግሞ ፍርድን በገዛ ራሳቸው በራሳቸው ላይ ያከማቻሉ! አዎን! በኀጢአት እሳት ውስጥ የወደቁትን ስናድን፣ እኛኑ ልብልባቱ በክፉ እንዳይጎዳን መጠንቀቅ ይገባል። “ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” (ገላ. 6፥1) እንዲል።

3.   ነውራቸውን ለመሸፈን የተጠቀሙበትን ተቋምና እነርሱን እንለይ፦ ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እኛም እውነተኛው የመሲሑ የመስቀሉ ብርሃን እንዲበራላት እንማልዳለን፤ ነገር ግን በነውራቸው ንስሐ ከመግባት ይልቅ ሌላ ጥግ የሚሹትን ፈጽሞ አንታገሣቸውም። እንደማንታገሣቸው ስላወቁም ነው አንዳንዶቹ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት። እናም ተቋሙንና ሰዎቹን እንለያቸው!

“የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።” (ራእ. 17፥14) አሜን።

4 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come,till your last breath.

    ReplyDelete
  2. ተባረክ ወንድማችን

    ReplyDelete
  3. አንተ ወሻ የበላህበትን ወጭት ሰባሪ

    ReplyDelete
  4. ተናግረህ ሞተሃ ቅድስት ድንግል ማርያም አንድ ናት የተጠራችው ግን በቦታው ነው

    ReplyDelete