Friday 29 October 2021

በገንዘብ ብዛት አትችሏትም!

Please read IN PDF

ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፤ እርሱ ብቻ ደግሞ ራስዋ ነው። የሚያምርና የተንቆጠቆጠ ካቴድራል አልያም ጽርሐ ወንጌል ላይኖራት ይችላል። አማኞቿ ጥልቅ ድኾች፣ ደምግባት አልባ፣ ያልተማሩ ገበሬዎች አልያም ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ቢኾኑም፤ በክርስቶስ ፊት እኩልና አንድ፤ ኹሉም ለክርስቶስ በኵራት ናቸው። በጌታ ቤት ታላቅና ታናሽ የለምና!

አዎን! ቤተክርስቲያን የተሰቀለው ክርስቶስ ቅድስት ፍሬ ናት። ማንም አልሞተላትምና ከክርስቶስም በቀር የሚገዛትም የለም። እርሷም ለእርሱ ታምና ስትኖር የእርሱ ክብር ክብሯ፣ ውርደቱም ውርደቷ ነው። ኢየሱስን የሰቀሉት አሕዛብ ብቻ ሳይኾኑ፣ ሃይማኖተኞችና ቀናተኞቹ እንደ ነበሩ አንዘነጋም። ይህም የቤተክርስቲያን መከራና ስደት ከአሕዛብ ይልቅ "እግዚአብሔርን ይፈራሉ" በሚባሉ ሰዎች ጭምር እንደ ኾነ ማስታወስ መልካም ነው።

ከዚህ እውነት ተነሥተን አንድ ታላቅ ነገር ላንሳ፤ የተሐድሶ አገልግሎት በአደባባይ እያገለገሉ ያሉትን፣ አኀው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እና ውሉደ ብርሃን(በቴሌቪዥን ስሙ ቃለ አዋዲ እየተባለ የሚጠራውን) ለማፍረስ፣ በአንድ "ሃብታም" አጋፋሪነት ሚሊዮናት ብር ተመድበው፣ "አገልጋዮች" እያማለሉ፤ አማኞች እያስኮበለሉ ወደ ራሳቸው እየሰበሰቡ እንደ ኾነ አውቃለሁ። ክርስትና፣ በሰው ዓይን ተመርጠው የተሰበሰቡ "የምርጦች ስብስብ" ሳትኾን፣ በክርስቶስ ደም የተዋጁ፤ ለክርስቶስም የተለዩ አማኞች ኹሉ ያሉባት "የደካሞች" ስብስብና ቅድስት ኅብረት ናት። ምንም ደካማ ብትመስልም ግን የገሃነም ደጆች ወይም የክፋት ኃይል አሠራሮች ኹሉ አይችሉአትም።

ውሸታሙ ክርስትና መስቀልን አርማው አድርጎ፣ አስቀያሚ ጦርነቶችን በማድረግ ሚሊዮናትን ገድሎአል፤ ኢየሱስን የማያውቀው ክርስትና በምድራችን ላይ የስእልን መብት ለማስጠበቅ ጦርነት አድርጓል። ዛሬ የመስቀል ጦረኞቹም፤ የስዕል መብት አስከባሪዎቹም ተዋርደዋል።

እውነተኛውን ክርስትና ከሚያሰድቡት ባለፈ፣ ለማጥፋትም የተነሱ ኀይላት ነበሩ። የሮም ቄሳሮች እውነተኛውን ክርስትና ለማጥፋት ያልበጀቱት በጀት፤ ያላሰማሩት ወታደር አልነበረም። ኮሚኒስት፣ ሶሻሊዝም ክርስትና ላይ ዘምቶ፣ ራሱ ውርደት ተከናንቦ እንደዋዛ አለፈ። የጌታ ቅሪቶች ግን ዛሬም በመላው ዓለም አሉ።

እና ምን ለማለት ነው፤ እናንተ "ቅምጥል የሃብታም ገበታ ዙሪያ ተሰብሳቢዎች" ሆይ፤ "እንዲፈርስ ተደርጎ የተሠራውን ፍኖተ አበውን" በቀላሉ እንዳፈረሳችሁት፣ ገንዘብና ነውር ወዳዶችን በቀላሉ እንደ ሰበሰባችሁት... አኀውና ቃለ አዋዲን በቀላሉ ለማፍረስ፣ ክርስትናንም ማጠልሸት አትችሉም። በብር ብዛትና ሌላውን ኅብረት ባንቋሸሸ መንገድ፣ የተሰበከ ክርስትና የሚሰበክም ክርስትና የለም!

መጽሐፍ፦ “ምድራዊ ደስታን የምትሻዋ መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተች ናት።” (1ጢሞ. 5፥6) እንዲል፣ በአገልግሎት ስም በምድራዊ ተድላ መቀማጠል የሚሹ ኹሉ፣ ከኢየሱስ ጋር ስደትና ውርደት እንደሚሻል ማን በነገራቸው?!

እንደ ማሳሰቢያ - አኀው፣ ቃለ አዋዲ ሌሎችም ኅብረቶች ውሽንፍሩንና ውጅንብሩን ለማለፍ በጸሎት ቢተጉ፣ አማኞቻቸውን ቢያበረታቱ፣ የአንድነት ጉባኤ ቢያዘጋጁ እጅግ መልካም ይመስለኛል።

በብራችሁ የምትመኩ ኅሊና ጠምዛዥ "ሃብታሞች" ከነብራችሁ ፈቀቅ ብትሉ መልካም ነው! ደካሞች ብንኾንም በኀጢአት አንርመጠመጥም!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)


6 comments:

  1. ጌታ ቤቱን ያጽዳ! እነዚህ አቋም የሌላቸው ህይወታቸው የሚያስጠላ ነውረኞች የሚከተል ካለ እራሱን ለምን እንደሄደ ይፈትሽ። ወንጌል ሲሞላ የምትፈነጭበት ሲጎድል የምትጥለው የቢዝነስ ፕሮጀክት አይደለም!!!

    ReplyDelete
  2. EGZEABHER tegawen yabzalehe bewenat enamesagenalen

    ReplyDelete
  3. egeziyabeher zemenehen yebarek tebareke yabate beruke

    ReplyDelete
  4. ኢየሱስ ጌታ ነው።👉ስለ አንተ እግዚአብሔርን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ

    ReplyDelete
  5. የማመልከው አምላክ ጌታ ኢየሱስ ቀሪ ዘመንህ ይባርከው እጅግ በጣም ጠቃሚ መልክት ነው

    ReplyDelete