Monday 8 March 2021

ኢየሱስ እስኪመጣ - ዘጠኝ የአገልግሎት ዓመታቴ

 Please read in PDF

በእግዚአብሔር ቸርነትና የተትረፈረፈ ምሕረት፣ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በብሎግ ወይም በጡመራ መድረክ አገልግሎት አገልግያለሁ፤ በእነዚህ ዓመታት ከእግዚአብሔር የሰማኋቸውን፣ የተቀበልኳቸውን፣ ቅዱስ ቃሉን ሳነብብና ሳጠና መንፈስ ቅዱስ የገለጠልኝን፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የደረሱትን እጅግ አሳዛኝ ሰቆቃዎችንና ከፍ ያሉ በደሎችን በአካል በስፍራው ተገኝቼ በመመልከት እግዚአብሔር ምን ይሰማው ይኾን? ብዬ ሙሾ አውርጄአለሁ።   

ያለፈው ዘጠኝ ዓመት ካለፉት ዓመታት ይልቅ ተግዳሮቴ እጅግ ከባድ ነበር። ብዙዎች “ሴራ በበዛበት የፖለቲካ” ዓመጽ እንድሳተፍ ነፍሴን የፈተኑበት፣ ወንጌል ያገለገልኳቸው መልሰው ያዋረዱኝ፣ የ“ታመኑ” ወዳጆቼ ከዳተኛና ድምጼን ለመስማት የተጠየፉበት፣ ከጉድለታቸው ቆርሰው ሲሰጡ የማይሰስቱ እጅግ አስደናቂ ባልንጀሮችን ያገኘኹበት፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ኹሉንም ያስችላል። በእኒህ ኹሉ ጊዜያት ከታላቁ የእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ፣ ካለፉት ስምንት ዓመታት ይልቅ የሚበልጥ መንፈሳዊ አናቅጾችን ጽፌአለሁ፣ ወደ ሩቅ አከባቢ ሄዶ የማገልገል ዕድሎችን አጊኝቻለሁ፣ በቅርቡ ከሕትመት የሚወጣ መጽሐፍን ጽፌአለሁ።

በእኒህ የአገልግሎት ዘመኔ በምንም ነገር ከጐኔ የነበሩትን ወንድሞችና እህቶችን፣ ጌታ ያህዌ ኤሎሂም በክርስቶስ እጅግ በብዙ በረከት እንዲባርካቸው የዘወትር ጸሎቴ ነው፤ ኹሌም በልቤ አሉ፤ ኹለቱ ሙሌዎች፣ ደሬ፣ አዲስ፣ ዓቢ፣ ሉ፣ ሚሻ፣ ሮትዬ፣ ጋሽ ፀሐዬ፣ ሰብሊ፣ ባያ እናንተ ለእኔ ከጌታ የተሰጣችኹኝ ጌጦቼ ናችሁ፤ ተባረኩልኝ፤ ተትረፍረፉልኝ። በአገልግሎቴ ብዙ የምትቃወሙኝ፣ እግር በእግር እየተከታተላችሁ የምትዝቱም፣ የምትሰድቡኝም የተሰቀለው ኢየሱስ በብዙ ይባርካኹ፤ መንፈስ ቅዱስ ልባችሁን ለወንጌል ልዝብ እንዲያደርግ ምልጃዬ ነው።

ኢየሱስ እስኪመጣ በጸጋው ታምነን እናገለግለዋለን!

 

በቴሌግራም ለመከታተል በዚህ ሊንክ ይግቡ https://t.me/ebenezertek

የጡመራ መድረኬ ወይም የብሎግ አድራሻ  የዲያቆን አቤንኤዘር ተክሉ ገጽ (abenezerteklu.blogspot.com)

የዩቲዩብ አድራሻ abenezer teklu - YouTube

No comments:

Post a Comment