Thursday, 11 March 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፮)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

ባለፉት ጊዜያት የ“መድሎተ ጽድቅ” መጽሐፍን በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱስ ከመመዘናችን በፊት፣ በመጽሐፉ ውስጥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ዐሳብ ውጭ በኾነ መንገድ እንደ ገና ተተርጕመው የቀረቡትን ቃላት መመልከት መጀመራችን ይታወሳል። ቃላቱን በተመለከተ ዛሬም ቀጣዩን ክፍል የምናቀርብ ይኾናል። መልካም ንባብ።

·        መዳን፦ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥና በአጭር ቃል ስለ መዳን ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “በእርሱ[በክርስቶስ] የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐ. 3፥16)። በመጽሐፍ ቅዱስ መዳን የሚለው ዐሳብ፣ ልክ በዚህ ክፍል እንደ ተጠቀሰው የዘላለም ሕይወት፣ አዲስ ልደት (ቲቶ 3፥5)፣ አዲሱን ሰው መልበስ (ቈላ. 3፥10)፣ አለመጥፋት (ዮሐ. 3፥16፤ 2ጢሞ. 2፥11)፣ ልጅነት (ሮሜ 8፥13)፣ ዳግመኛ መወለድ (ዮሐ. 1፥12-13፤ 3፥3-8) በሚሉ ተካካይ ዐሳቦች ገልጦት እንመለከታለን። 


የቅዱሳት መጻሕፍትና የቅዱሳን ሰዎች ኹሉ ስብከትና ትምህርት፣ በእነርሱ በኩል ሰዎች ኹሉ በልጁ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ነው (ዮሐ. 1፥7፤ 20፥31)። ስለዚህም አንድ ሰው ወንጌል ሲመሰከርለት መዳኑ ወይም ልጅነት የማግኘቱ ጉዳይ ከማመኑና ያመነውን ለመቀበል ከመወሰኑ ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ በወረደ ቀን የመጀመሪያውን ስብከት በሐዋርያው ጴጥሮስ አማካይነት ሲያቀርቡ፣ በትክክል የሰሙአቸው ሰዎች በቀረበው ስብከት ልባቸው ተነካ (ሐዋ. 2፥37)፣ ይህም ማለት ቀድሞ በኢየሱስ ባለማመናቸው ተጸጽተው አኹን ግን ማመናቸውን የሚያመለክት ነው።

ጌታችን ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ ከወንበዴዎቹ አንዱ፣ በመስቀል ላይ ሳለ በክርስቶስ ማመኑንና ከክርስቶስም ጋር ዛሬ[ወዲያው] በገነት[በእግዚአብሔር ደስታና ዕረፍት ውስጥ] መኖር መጀመሩን ሉቃስ አስደናቂ በኾነ መንገድ ያስቀምጥልናል (ሉቃ. 23፥42-43)። ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በወኅኒ ታስረው ሳለ፣ ይጠብቃቸው የነበረው የመቶ አለቃ በተከናወነው ተአምራት በተደናገጠ ጊዜ፣ ካረጋጉት በኋላ እንዲህ አሉት፣ “በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ” (ሐዋ. 16፥31)፤ እርሱም አመነ፤ ዳነም፤ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ፤ (ቊ. 34)

በክርስቶስ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ደግሞም አይፈረድበትም፤ የሚያምኑ ኹሉ ይጸድቁ ዘንድም ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ኾኖአል (ሮሜ 10፥4)፤ ስለዚህ መዳን የተመሠረተው በአዳኙ ብቃትና ችሎታ እንዲሁም፣ ኹለንተናዊ ባሕርይው ላይ ሙሉ ለሙሉ በመደገፍ እንደ ኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። አብርሃም እንዴት እንደ ዳነ አስተውሉ፤ አብርሃም የጸደቀው በእምነት ነበር፣ ምክንያቱም ጽድቅ በሥራ ከኾነ፣ ከቶውንም ጸጋ ሊኾን አይችልምና።

“አብርሃም በሙያው በጉልበቱ ከብሮ ቢኾን በሙያው በጉልበቱ ከበረ ተብሎ በተመሰገነ ነበር፤ በእግዚአብሔር ቸርነት ባልተባለም ነበር … አብርሃም ግን ኃጥእን በሚያከብረው በእግዚአብሔር ቢያምን ማመኑ ጽድቅ ኾኖ ተነገረለት፤ ከጽድቅ ገብቶ ተቈጠረለት።”[1]

በሌላ ስፍራም፣

“ጽድቅ የሕይወት ጐዳና እኔ ነኝ በእኔ ካልኾነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ ማንም ማን የለም አለ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ አንድ ገዢ ነው።”[2] እንደገናም፣

“ሕግ አፍረሽ ጲላጦስ ይዘብትበት ዘንድ በመስቀል ይሰቀል ዘንድ በመቃብር ይቀበር ዘንድ በሦስተኛው ቀን ይነሣ ዘንድ ምን አተጋው? በፍዳ ተይዘን የነበርን እኛን ያድነን ዘንድ ለእኛ ብሎ አይደለምን?”[3]

“አለኝታችን (ተስፋችን) በዕሩቅ ብእሲ (በፍጡር ሰው) አይደለም በእግዚአብሔር ነው እንጂ በእግዚአብሔር ብቻ በቀር በሌለ የሚያምን ርጉም ነው።”[4]

ተብሎ በአበው ትምህርት እንደ ተነገረ። ለዚህ ነው “ክርስቶስ” የሚለው ስም፣ “ብቃት ያለው አዳኝ” ተብሎም የተተረጐመው።

በምሥራቃዊው አስተምህሮ፣ መዳን ሂደታዊና እስከ ዕለተ ሞት ድረስ መታመንና መቀደስን የሚጠይቅ፤ የሚያድግም ነው። በዚህ መንገድ ተከትለን የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ አቋም ስንፈትሽ፣[5] የጥንተ አብሶን ትምህርት የሚቀበልና የሚያምን ነው፤ ምንም እንኳ እርሱ በመጽሐፉ ጥንተ አብሶአዊ ትምህርት የአውግስጢኖስ ብሎ ደምድሞ ቢጽፍም። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት በርግጥም ድነናል፣ እየዳንን ነው፤ ፍጹምም እንድናለን፤ ኹሉም ግን በክርስቶስና በመንፈሱ ብቻ ነው።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ መልሶ ቢያፈርሰውም፣ የእግዚአብሔርን[የክርስቶስን] ብቻ አዳኝነት በተደጋጋሚ ሲናገር እንሰማዋለን።[6] ከዚህም ባለፈ መዳን የኹሉም የክርስትና ትምህርቶች ማዕከል እንደ ኾነ ጭምር ሲናገር እንሰማዋለን፤[7] ነገር ግን መልሶ ሲሸቅጥም እንመለከታለን። መዳን በእግዚአብሔርና በእግዚአብሔር ብቻ ከተፈጸመ፣ በእርግጥም ክርስትና የእግዚአብሔር መንገድ ነው፤ መዳን የፍጡር እጅ ካለበት ግን በርግጥም ክርስትና በፍጡር መመሥረቱና የሰው ሃይማኖት መኾኑ አያጠራጥርም።

የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ የመዳን ትርጕም ስህተቱ

“ለመዳን ከማመን ቀጥሎ ለድኅነት ወሳኝና አስፈላጊ የሆኑ ምስጢራትን መፈጸም ይገባል። እነዚህም በመጀመሪያ ጥምቀት፤ ቀጥሎ ሜሮን እና ከዚያም ቅዱስ ቁርባን ሲሆኑ ከዚያ በኋላ በሕይወት ሂደት ለሚገጥሙ ነገሮች ደግሞ ንስሐ ናቸው። … ቅዱስ ጳውሎስን በሚያስደንቅ ሁኔታ ራሱ ጌታችን ተገልጦ ከጠራውና ካነጋገረው በኋላ ለመዳን የሚያስፈልገውን ነገር ያገኝ ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሄድ ነበር ያዘዘው። …”[8]

እንግዲህ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ መዳን በእምነት ነው ብሎ ቢነግረንም፣ ክርስቶስ የሠራውን ሥራ ማመንና መቀበል በቂና ብቸኛ አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ፣ “መሠረት እንጂ መደምደሚያ፣ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም”[9] በማለት፣ የክርስቶስን የማዳን ሥራ ሲነቅፍ ይስተዋላል። ቅዱሳት መጻሕፍት ግን መዳን በክርስቶስና ክርስቶስ የሠራውም ሥራ በቂና “ዘወትር ለምንሠራው ኀጢአት” ዋስትናችን መኾኑን አስረግጦ ይናገራሉ። ከአዳም ጀምሮ ላገኘንም ኾነ፣ ዛሬም ለምንሠራው ኀጢአት ማስተስረያችን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሠራው ሥራ ነው፤ (ሮሜ 5፥8፤ 8፥34፤ ኤፌ. 2፥4-10፤ ዕብ. 7፥24-25፤ 1ጴጥ. 1፥3-5፤ 1ዮሐ. 1፥7፤ 2፥1-3፤ ራእ. 1፥4-6)። 

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ግን ይህን ትምህርት በመቃወም የሚቆመው፣ ከክርስቶስ የመስቀል ሥራ ይልቅ የምስጢራትን ትምህርትና እምነት፣ የኀጢአት ማስተስረያነት ለማጽናትና ሚዛን እንዲደፉ አድርጎ ለማቅረብ መኾኑን ማስተዋል ይገባል፤ ምክንያቱም ስለ መዳናችን ዘወትር የሚያስታርቀንና ማስተስረያችን የኾነው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነውና።[10] በክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ፤ አሜን።

ይቀጥላል …



[1] የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ንባቡና ትርጓሜው

[2] ሃይማኖተ አበው ዘባስልዮስ ምዕ. 32 ቊ. 12

[3] ሃይማኖተ አበው ዘእለ እስክንድሮስ ምዕ. 16 ቊ. 3

[4] ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ ምዕ. 7 ቊ. 59

[5] ገጽ 111

[6] ገጽ 93

[7] ገጽ 94-97

[8] ገጽ 126

[9] ዝኒ ከማኹ

[10] መ/ር ብርሃኑ ጎበና፣ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለማርያምና መ/ር ኃ/ማርያም ላቀው(አዘጋጆች)፤ አዕማደ ምስጢር ፩ እና ፪፤ 1996 ዓ.ም፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ገጽ 61

2 comments:

  1. አንተ ዲቁናህ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለተቃዋሚው መንፈስ ነው፡፡አንተን በአጭሩ ማለት የምችለው መድሎተ ከርስ ነው፡፡ሐራሁ ለዲያቢሎስ ዘተከሰትከ በስመ ዲቁና፡፡ዳእሙ ግብርከ ነበበነ አንተ ከመ ኮንከ ፀዋሪ ምንፍቅና፡፡

    ReplyDelete
  2. አንተም ተማር መጀመርያ ከመሳደብህ በፊት

    ReplyDelete