Thursday 14 January 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፬)

 Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

·        የእግዚአብሔር ቊጣ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኀጢአት የእግዚአብሔርን ቊጣ እንደሚያነሣሣ በግልጥ ይናገራል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ባሕርይውና ፈቃዱ ቅዱስና ጻድቅ ነውና፣ በኀጢአት ፈጽሞ አይደሰትም። በሌላ ንግግር ኀጢአትን ፈጽሞ ይጠየፋል፣ ይጠላልም፤ በኀጢአት ከቶም ደስ አይሰኝም ማለታችን ነው። አደራረጉ ፍጹም ቅዱስና ንጹሕ ነው። ስለዚህም “በቍጣውና በመዓቱ ኀጢአተኞችን ይገለባብጣቸዋል፤ ኪዳኑን የሚተዉትንም ይነቅላቸዋል፤ ” (ዘዳ. 29፥23-28)። ቅዱሱ እግዚአብሔር፣ ያለ ተጨባጭ ምክንያት እንደ ሰው በንዴትና በብስጭት የሚቈጣ አይደለም፤ ቊጣው ወዲያው የሚነሣ ደግሞም ቶሎ የሚበርድም አይደለም። በተለይ ኀጢአተኞችን ለኀጢአታቸው በመተው ቊጣው ይገለጣል፤ (ሮሜ 1፥24)።

ቊጣው በጽድቅ የተሞላ ነው፤ ለዚህም ነው ቊጣው በጻድቅ ፍርዱ የሚገለጠው፤ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤” (ራእ. 16፥5) እንዲል። “በልጁ የማያምን … የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል …” (ዮሐ. 3፥36)፣ “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች … ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤” (ሮሜ 1፥18)፣ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና” (ኤፌ. 5፥8)። እኒህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ የእግዚአብሔር ልጅን በማያምኑ፣ እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉት፣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ የተገለጠና የሚመጣ መኾኑን ይገልጣል።

 አማኞች ክርስቶስን በማመናቸው ከእግዚአብሔር ቊጣ ይድናሉ (ሮሜ 5፥9)፤ ክርስቶስ በእኛ በኀጢአተኞች ላይ የነደደውን ቊጣ ተሸክሞአል፤

ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ …” እንዲል (1ተሰ. 1፥9-10)። የካንትርበሪ ጳጳስ አንሰልም፣ ስለ እግዚአብሔር ቊጣ “ከማስተማሩ በፊት ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ መኖሩን መካድ አይቻልም። ደግሞም የእግዚአብሔርን ቊጣ ምዕራባዊውያን “አጥብቀው” ስላስተማሩት ጨርሶ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም ብለን መተውና መጣል አንችልም። ምሥራቃውያንም እግዚአብሔር አዛኝና ሩኅሩኅ ነው በማለታቸው ብቻ፣ ኀጢአትን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቊጣ የለም ወይም አልነበረም ማለት አይችሉም።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ቊጣ የሚናገረው ኀጢአት ከሚጠላና ከሚጠየፍ ማንነቱና በኀጢአተኞችም ላይ ከሚፈርደው ጻድቅነቱ ጋር በጥብቅ አቆራኝቶ ያነሣል። ዮሐንስ በራእዩ በጉን ገራገርና የዋህ አድርጎ ቢጠቅስልንም፣ በኃጢአተኞች ላይ በዚያው ልክ ደግሞ ቊጣው የሚያርበደብድና “ተራራዎችንና ዓለቶችንም፦ በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? ” ብለው እስኪናገሩ ድረስ እጅግ አስፈሪ ነው፤ (ራእ. 6፥16-17)።  

በተለይም የሥርየትን ትምህርት ለማስተማር ስንነሣ፣ የእግዚአብሔርን ቊጣ መናገራችን ግድ ነውና። ኀጢአት ዘወትር የእግዚአብሔርን ቊጣ ስለሚያነሣሣ ማስተሥረያ ወይም ይቅርታ ማስገኛ ይቆም ዘንድ ግዴታ ኾኖአል። እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ከታላቅ ፍቅሩና ምሕረቱ የተነሣ ሲኾን፣ ያቆመውም ደግሞ በክርስቶስ ደም መፍሰስ ወይም በሞቱ ነው። የእስራኤል ልጆች በግብጽ ላይ ከወረደው ቊጣ ያመለጡት በበራቸው ላይ በቀቡት የፋሲካው በግ ደም መኾኑን መዘንጋት አይገባም፤ ያ ደም እስራኤል ዘሥጋን ከቊጣው እንደ ሸፈነ ዛሬም ከቊጣው የምንሸፈነውና የምናመልጠው በልጁ በማመን ብቻ ነው። 

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ስህተት

“የክርስቶስ መሥዋዕትነት ለአብ የቀረበ ነው የሚለው … አስተምህሮ እግዚአብሔር ክብሩና ፍትሑ እንደ ተነካበትና ከዚያም የተነሣ እንደ ተቈጣ፣ ለዚህም መካሻና የቊጣው ማብረጃ ይሆን ዘንድ ቀረበ የሚለው … ለእግዚአብሔር የማይገባ አገላለጽና አሰተሳሰብ ከመኾኑም በላይ … የአንዲት የቅድስት ሥላሴ ፈቃድ የሚነጣጠጥልና የሚቃረን እሳቤ ነው።”[1]

ይላል። ደምድሞም፣ “ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ አይደለም”[2] ማለቱ ፍጹም ስህተት ነው። አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ማለት አይደለም። እግዚአብሔር ኀጢአትን መጠየፉ እውንና እሙን ነው፤ መቆጣቱን ደግሞ ሰዋዊ አድርጎ ማቅረቡ ትክክል አይደለም። ወልድ ሰውነትን ገንዘብ ማድረጉ ውርደት እንጂ ክብረት አይደለም፤ ሰውን ለማዳን ግን ሰውነትን ገንዘቡ አደረገ፤ ተዋረደ ስንል፣ ለእርሱ የማይገባ አገላለጥ ነው አንልም፤ እውነት ነውና። እግዚአብሔርም ኀጢአትን አያውቅም፣ ስለዚህም ገንዘቡ ማድረግ አይወድምና ፈጽሞ ይጠየፈዋል፤ በጽድቅም በኀጢአትና ሊመለስ ባልወደደ ኀጢአተኛ ኹሉ ላይ ይፈርዳል።

ይቀጥላል …

 



[1] ያረጋል አበጋዝ(ዲያቆን)፤ መድሎተ ጽድቅ፤ ገጽ 79

[2] ዝኒ ከማኹ ገጽ 80

6 comments:

  1. ተባረክ አቤኒ

    ReplyDelete
  2. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come!!!!!

    ReplyDelete
  3. አንተ ከተቃወምከው ምርጥ መጽሀፍ ነው ማለት ነው በቃ 3ቱንም እንገዛዋለን።

    ReplyDelete
  4. ግብዝና ከንቱ ነህ ተናግረህ ሞትሃል

    ReplyDelete
  5. ቅናት አንገበገበክ ቻለው እኛ እንዲህ ነው ሠይጣንን የሚያቃጥል አምላክ እምነት አለ

    ReplyDelete