Monday, 11 January 2021

ብሔራዊ ውርደታችን!

Please read in PDF

ዛሬ ላይ በምንም ዓይነት ሚዛን፣ አጼ ኃይለ ሥላሴን እንዲያ መዋረዳቸውን፣ 60ዎቹ ሚኒስትሮቻቸው ደግሞ በአንድ ጉድጓድ ውስጥ በጅምላ ተገድለው መቀበራቸውን የሚደግፍ ሰብዓዊና ጤነኛ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም።  ይህን የማይደግፈው አጼው አልበደሉም፤ ሚኒስትሮቻቸውም ንዑዳን፤ ቅዱሳን ናቸው ብሎ እንዳይደለ፤ ነገር ግን አገር ለመሩ፣ ጥቂት ውለታ ለዋሉ ምንም ያህል ክፉ ቢሠሩ ብድራታቸው ግድያ፤ በጅምላ መረሸን፣ መዋረድና መንገላታት እንዳልኾነ ዕዝነ ልቡናው ያስባል፤ ያሰላስላል ብዬ እንጂ።



በአንድ ወቅት ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፣ እስራኤል ከኀጢአት እንድትመለስ፤ ከዓመጻዋ ዘወር እንድትል በብዙ ምልጃ ለምኖአት ነበር።  መላ ዕድሜውን እርሱን ጨርሳ በማትሰማው እስራኤል መካከል ተቀምጦ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ደግሞ፣ ደጋግሞ በልመና፣ በተግሳጽ፣ በቊጣ ቃል ሳይሸሽግ ተናገረ።  ነገር ግን አንዳች የሚሰማው ሰው ሊያገኝ አልቻለም፤ እርሱንም እግዚአብሔርንም የሚሰማ ታጣ።  እንዲያውም ንግግሩንና ትምህርቱን የሰሙ እጅግ ብዙዎች አላገጡበት።

የእስራኤልን ነውርና ርኩሰት ከልጅነቱ እያየና እየሰማ በማደጉ፣ የእስራኤልን ኹኔታ በሚገባ ያውቅ የነበረው፤ ግለ ሕይወቱን ጭምር ለትችትና ለስድብ አጋልጦ በብዙ ከበደል እንድትመለስ ለእስራኤል እየተናገረ የኖረው ነቢይ፣ በማናቸውም መንገድ ግን ለእግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ፈጽሞ አልተወም። አኹን እንደ ዋዛ እየሠሩት ያለው ኀጢአት ፍርድን እንደሚያስከትልና እንደሚያዋርዳቸው ቢናገርም፣ ይሁዳ በጽኑ ኀጢአት በመጽናቷ፣ ኤርምያስ የፈራው ያ የውርደትና የግዞት ቀን መሰስ ብሎ መጣ።

ባቢሎናውያን፣ ይሁዳ ውኃና ምግብ እንዳታገኝ ለዓመታት መጥተው ሲከብቧት ኤርምያስም ከተከበበው ሕዝብ ጋር የጽዋው ተጋች ኾነ፤ ይሁዳ በውርደት ወደ ባቢሎን ስትወርድ በብርቱ ሲቃትት የነበረውም ነቢይ አብሮ ወረደ፤ በዚያን ጊዜ ኤርምያስ፣ ካህናትና ሽማግሌዎች ምግብ ከማጣት የተነሣ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ በምግብ ፍለጋ በየከተማዎቹ ጎዳና ሲክለፈለፉ አይቶአል (ሰቆ. 1፥19)፣ የጽዮን ደናግላን በውርደት ሲያዘቀዝቁ ተመልክቶአል (ሰቆ. 2፥10)፣ ሕዝብ ኹሉ በውርደት አቀርቅሮ ነበር፤ የታላቁ ንጉሥ ሴዴቅያስ ኹለቱ ልጆች በንጉሡ ፊት ተገደሉ፣ የራሱ የንጉሡ ዓይኖች እንዲወጡ ተደረጉ፣ ይሁዳ ከላይ እስከ ታች ተዋረደች፤ ሰቆቃዋ መረረ።

ኤርምያስ ስለ ኾነውና ስላገኘው ሐዘን ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!” (ኤር. 9፥1) እንዴት ያለ ጥልቅ ሐዘን ነው! ኤርምያስ ብዙ የለመናቸው ሕዝቦቹ አይወርዱ ወረዱ፣ አይዋረዱ ተዋረዱ፤ ነገር ግን እንደ ተናገረው የኀጢአታቸው ፍርዱ ሲመጣና ሲገለጥ፣ ኤርምያስ ደነገጠ፤ ጉበቱ ፈሰ፤ አንጀቱ ተቃጠለ፤ የይሁዳን ውርደት ልክ እንደ ራሱ ውርደት ተመለከተ።  ይሁዳ ስትሰበር እርሱም አብሮአት ተሰበረ።

በአገራችን የኾነው እውነታ ከኤርምያስ ዘመን ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ትላንት አገር ይመሩ የነበሩ ሰዎች በዚህ ልክ፣ በገረጣ ፊት፣ በጠወለገ ቆዳ፣ በጠቆረ ኮስማና ሰውነት፣ በሞገገ አጥንት መታየታቸው … ፍርድ ቢኾንም አለመደንገጥ ግነ ያሰቅቃል። ማዘን ነበረብን፤ መደንገጥ ነበረብን፤ ሙሾና ሰቆቃ እንደ ኤርምያስ ማውረድ ነበረብን … ግን እጅግ ብዙዎች እንዲህ በመኾናቸው ደስ አለን፤ እንዴት ልብ ይሰብራል?! በዚህ ጉዳይ እንዴት ግን “አማኞች” ከማያምኑቱ ጋር በአንድ ተስማሙ? እንዴት አቤል ነን ያሉቱ በቃየል ሞት ደስ ተሰኙ?! እንዴት?!

ፍትሕ ሌላ ነገር ነው፤ ይህ ግን እንደ አገር የውርደትና የጉስቁልናችን ታሪክ ነው፤ የቱም ወገን ተንሸራትቶም ኾነ ባፍ ጢሙ ተደፍቶ መውደቁ፣ ከዙፋን መሰደዱ … ያሳዝናል፤ ልብ ይሰብራል እንጂ አያስደስትም።  እኔ ግን እንዲህ እላለሁ፣ በዚህ በውርደቱ ጊዜ ማን ይኾን የኤርምያስን ልብ የያዘ?! ጌታ ሆይ፤ የማርከንን አንተን አስበን፤ እጅግ ኀጢአተኞች ላልናቸው ምሕረትን እንቆርስ ዘንድ፤ ውርደታቸውን ውርደታችን እንደርግ ዘንድ መግቦትህን አብዛልን፤ አሜን።

4 comments:

  1. የጽውፍ አቀራረብህ እጅግ ደስ ይላል ፤ የታሪክ መንደርደርያህ የመጽሃፍትን ሐሳብ በእኛ አውድ አምጠህ ለማስረዳት የሄድክበት መንገድ ተመችቶኛል ፤ በሌላ መንገድ ደግሞ የእግዚአብሔር እጅ በየትኛው የህይወታችን ክፍል እንዳለች ሁሉ በዚህም ተገለጠች ብዬ አምናለሁ ፤ ፍርድን ከብዙ እንባ ከጌታ ለፈለጉ ሰዎች በእርግጥ መልስ ይሆናል ፤ እኛ ግን ለሰዎቹ በብዙ ርህራሄ መጸለይ አለብን ፤ አዳኙን ሳያውቁ ይችን ምድር እንዳይሰናበቱ ከብዙ እንባ ጋር እንጸልይላቸው። እኛ በአለም ብንሆንም ከአለም ግን አይደለንም ።

    ReplyDelete
  2. I AM BLESSED BY YOUR TEACHING

    ReplyDelete
  3. It’s really are so so so much powerfull , I don’t know how to express my feeling.

    ReplyDelete