Wednesday 22 January 2020

ንቀት (ክፍል ፯)

ለምን ግን እንናናቃለን?
   አንዳንዶች በመልካቸው ብቻ ይናቃሉ፤ ለምሳሌ፦ በዓረብ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ያሉ ጥቁር ዓረቦች፣ ጥቁር ስለኾኑ ብቻ የተናቁ እንደ ኾኑ ይናገራሉ፤[1] አንዳንድ “ቤተ እምነቶች” ንቀትን የማበረታታት ትምህርቶች አላቸው፤ ለምሳሌ፦ ከእነርሱ ቤተ እምነት ውጪ ያሉትን ወይም የቤተ እምነታቸውን ቀኖናና ዶግማ የማይቀበሉትን ማናቸውንም ቤተ እምነቶች መናቅ እንደሚገባቸው ያምናሉ፤ ልክ አብዛኛዎቹ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ወይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አንዳቸው ሌላውን እንደሚንቁ። እንዲያውም እንደ እስልምና[2]፣ ጅሖቫ፣ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት፣ የእምነት ቃል አገልግሎት፣ ሞርሞንና ተመሳሳይ “ቤተ እምነቶች”፣ ማንኛውም ሰው የእነርሱን ቤተ እምነት ቀኖናና ዶግማ ካልተቀበለና ከእነርሱ ውጭ ካለው ማናቸውም ኅብረት ጋር፣ ኅብረት ቢያደርግ “ከርኩሱ ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳደረገ ወይም እንደ ተካፈለ” አጥብቀው ያስተምራሉ።

  ስለዚህም አብዛኛዎቹ ቤተ እምነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስና ከኢየሱስ ትምህርት እጅግ በራቀ ኹኔታ፣ “የቤተ ክርስቲያናቸውን ቀኖናና ዶግማ” በማላቅና በማተለቅ ሌሎችን በመጥላት ፍጹም የተጠመዱ ናቸው። በዚህም ከክርስቶስ ኢየሱስ የተለየና የራቀ ሕይወት እንዳላቸው በዚህ ማስተዋል እንችላለን። ክርስቶስ ኢየሱስ ኀጢአተኞችን በመውደድና ወደ እነርሱም በመቅረብ አብሮ በመብላት፣ በማሳለፍ፣ ተጠግቶ በማውራት፣ ሸክማቸውን በመሸከም እጅግ ሲራራላቸው እንመለከታለንና።
  የኢየሱስን ሕይወት ካስተዋልን ማንንም የማይንቅ አይደለም፤ አለመናቁን ቀርቦ የሚረዳና የሚራዳ ነው እንጂ። ከኢየሱስ ተቃራኒ የቆመ አማኝም ይኹን ኀጥአንንና ሰዎችን ኹሉ በመጥላት የተጠመደች ለመኾንዋ፣ ከዘመናችን አያሌ አብያተ ክርስቲያናት ሌላ ምስክር ማንሳት አያስፈልግም።
V  ሰዎች እግዚአብሔርን ሲንቁ ሰዎችን ይንቃሉ እስራኤል ያህዌን ባለመታዘዝ ስትጠመድ ምን ልታደርግ እንደምትችል ነቢዩ ሲናገር እንዲህ አለ፤ “ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ። በሌሎች አማልክት አስቀኑት፥ በርኵሰታቸውም አስቈጡት” (ዘዳግ. 32፥15-16)። እስራኤል ስትጠግብ በእግዚአብሔር ላይ ስትቀማጠል ያዳናትንና የታደጋትን መድኃኒት እንደምትተውና እንደምትንቅ ይነግረናል
   ምድር ከእግዚአብሔር ጋር ያላት መንገድ ጤናማ ከኾነ፣ በመከባበርና በመዋደድ ጸጥ ብላ በፊቱ ትኖራለች፤ ነገር ግን በእግዚአብሔርና በሕጉ ላይ ንቀትን ካሳየች፣ በመላው የእግዚአብሔር በኾነው ላይ የማታደርገው ነገር አይኖራትም። ይህን በሕዝቅያስ ዘመን የተደረገውን እውነታ ማስተዋል ይቻላል፤ ንጉሥ ሕዝቅያስ የእግዚአብሔርን ፋሲካ ኹለቱ የተለያዩ ሕዝቦች እንዲያከብሩ ወደ ኤፍሬምና ምናሴ፣ እስከ ዛብሎንም ድረስ መልእክትን ተናግረው ነበር። ነገር ግን ምላሻቸውን ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይነግረናል፤
  “መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፥ አፌዙባቸውም። ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ።” (2ዜና. 30፥10-11)
V  ሰዎች እግዚአብሔርን ከናቁ የእግዚአብሔርን የኾነውን ኹሉ ይንቃሉ፦ በእርግጥ ሰዎች እግዚአብሔርን ከናቁ፣ ከምድር የማይንቁት ነገር ምን ይቀራቸውና? ሰው ሰውን ሲንቅ በሰው ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል ይንቃል፤ በዚህም ራሱን እግዚአብሔርን ወይም እግዚአብሔር በሰው ላይ ያለውን ዓላማና እቅዱን ይንቃል።
   በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን የነበሩትን ሰዎች ያደረጉትን አስተውሉ! የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም እናክብር ሲባሉ፣ ንቀትና ፌዝን ከወዴት አመጡት? እግዚአብሔርን ማምለክ እንደ ፌዝና ንቀት ለምን ቈጠሩት? በታሪክ በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን እስራኤል ለኹለት መከፈሏን አንረሳውም፤ ከኹለቱ ክፋይ ደግሞ የሰማርያው ክፍል በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መዋጡን የምንዘነጋው አይደለም፤ መከፈሉ ሳያንስ በጣኦት አምልኮ ኀጢአት ውስጥ መዘፈቁ እጅግ ያህዌ ኤሎሂምን እጅግ የሚያዋርድ ተግባር ነው፤ የዚህ ድምር ውጤት የእግዚአብሔርን አምልኮ መናቅና በእርሱም ማፌዝ ኾነ!
   ዛሬም በምድራችን ላይ የምናየው እውነታ ይኸው ነው፤ በዘር፣ በድንበር፣ በወንዝ፣ በቀዬ፣ በመንደር፣ በጎሳ፣ በነገድ፣ በቤተሰብ፣ በሕዝብ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት … ተቈራርሰን ከጥላቻ በዘለለ ፍጹም በኾነ መናናቅ ውስጥ የተዘፈቅነው እግዚአብሔርን በመተው ልባችንን አወፍረን ስላሰባነው ነው። ከምድራችን አግዚአብሔርን ማወቅና መፍራት፣ ማምለክም ከእጅግ ብዙዎች እንደ ራቀ ለማስተዋል የምናየውና የምንሰማው በቂ ነው። እንደ ኤፍሬም ሰዎች ፊት ለፊት ወንጌልን በመቃወም “ለራሳችን ጥቅም” የቆምነው፣ ለእግዚአብሔር ነገር መሸነፍ ንቀትና ፌዝ ስለመሰለን ነው።
   ከእግዚአብሔር ሕዝብነት፣ ከመሲሑ ማኅበረ ሰብነት ዘርና ብሔራችን የበለጠብን፣ እግዚአብሔርንና ኹሉን ማቀፍ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ትልቅ አካልነት በመናቃችን ነው። የእግዚአብሔር አካል ከየትኛውም ነገድ፣ ሕዝብ፣ ወገንና ቋንቋ የሚመጣውን አማኝ ለመቀበል የሚችል ትልቅና ሰፊ ነው፤ እኛ ግን የራሳችንን አተልቀን ሌላውን ስንንቅ፣ የናቅነው ትልቁንና ኹሉን ማቀፍ የሚቻለውን ደግሞም ለክብሩ ይህን ያደረገውን የእግዚአብሔርን የአካል ትልቅነት ነው። ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።
ይቀጥላል …



[1] https://www.youtube.com/watch?v=FllNRQ8IC8U
[2] አቡደርዳ እንዳወራው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል፡- “አላህ አዳምን በፈጠረ ጊዜ የቀኝ ትከሻውን መታና እንደምስጥ የነጡ ነጫጭ ዘሮች ወጡ። የግራ ትከሻውን ሲመታ ደግሞ እንደ ከሰል የጠቆሩ ጥቁር ዘሮች ወጡ። ከዚያም ከቀኝ ትከሻው የወጡትን ገነት ትገባላችሁ ምንም ግድ የለኝምአላቸው። ከግራ ትከሻ የወጡትን ደግሞ እነዚህ ለገሃነም የተዘጋጁ ናቸው ምንም ግድ የለኝምአለ። ይህ ሐዲስ በአሕመድ የተላለፈ ነው።” (Al-Tirmidhi Hadith, Number 38; ALIM CD ROM Version) እንዲሁም  (Mishkat Al Masabih, English translation with explanatory notes by Dr. James Robson [Sh. Muhammad Ahsraf Publishers, Booksellers & Exporters, Lahore-Pakistan, Reprint 1990], Volume I, Chapter IV, Book I.- Faith, pp. 31-32)

No comments:

Post a Comment