Please read in PDF
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጠመቁን ነገር በየዓመቱ በኢትዮጵያ አብያተ
ክርስቲያናት “ታስቦ” ይውላል፤ መታሰቡ “መልካም” ቢኾንም፣ የሚታሰብበት መንገድ ግን ፈጽሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መራቁ፣ እጅግ
የሚደንቅ የሚያሳዝንም ነው። በአገራችን “በዓለ” ጥምቀት አብዛኛውን ጊዜ ከመንፈሳዊ ነጸብራቅነቱ ይልቅ፣ ባሕላዊና ʻሃይማኖታዊ
ሥርዓት መከናወኛ ብቻ ኾኖ ሲከበርʼ እናስተውላለን። ጭፈራ፣ ሽለላ፣ ʻታቦትʼ እጀባ፣ ሎሚ ውርወራ፣ የአዳዲስ ልብስ ማሳያና …
ሌሎችም ተግባራት፣ ልኩንና ገደቡን በጣሰ መልኩ የሚቀርቡት በዚሁ በጥምቀት “በዓል” ቀን ነው። ቤተ ክርስቲያን ወደ ኢየሱሳዊ
መንፈሳዊነት ፍጹም አለማዘንበልዋ እንዲህ ላለ ሰፊ ተላላነት ተላልፋ መሰጧን ማስተዋል አያዳግትም።
መጽሐፍ ቅዱስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ አጥማቂው እጅ ይጠመቅ
ዘንድ፣ ከናዝሬት ገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መምጣቱን ይነግረናል፣ (ማቴ. 3፥13)፤ ገሊላ በከተማነቷ ጭምር የተናቀችና ነዋሪዎቿም
የተናቁ ማኅበረ ሰቦች መኾናቸውን ከታላቁ መጽሐፍ እንረዳለን። በትንቢት የተነገረላትና ያገለገለባትም ገሊላ፣ የአሕዛብ ገሊላ
ተብላ ተጠቅሳለች፤ (ማቴ. 4፥15) አሕዛብ ወደ እርሷ በመግባታቸው ምክንያት ይህን ስም ልታገኝ ችላለችና፤ (2ነገ. 15፥29፤
17፥24)። ከዚህም የተነሣ ኹለቱም ገሊላዎች በሌሎች አይሁድ ዘንድ እጅግ የተናቁና ተቀባይነት የሌላቸው ነበሩ፤ (ማቴ.
26፥73፤ ዮሐ. 7፥52፤ 1፥47)።
ቋንቋቸውና ኑሮአቸው እንደ ሌሎች ወይም በኢየሩሳሌም እንደሚኖሩ አይሁድ
አይደሉምና እጅግ የሚገለሉ ናቸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌሎች ከተሞች ይልቅ በተደጋጋሚ ወደነዚህ ከተሞች በመምጣት
አስተምሮአል፤ ተአምራትንም አድርጎአል፤ (ሉቃ. 4፥14፡ 15፤ ዮሐ. 1፥44)፤ በኋላ ላይ እንኳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ደቀ መዛሙርትን የጠራው ከገሊላ እንደ ኾነ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ (ሐዋ. 1፥11፤ 2፥7)። ተወዳጁ መሲሕ ወደ
ተናቀውና ወደ ተረሳው ማኅበረ ሰብ መምጣቱ እንዴት የሚደንቅ ግሩም ነው!!!
ወደ ተናቀና ወደ ተጠላ፣ “ፈጽሞ አልወደድም” ወይም “የሚወደኝ ፈጽሞ
የለም” ወደሚል ሰውም ኾነ፤ ማኅበረ ሰብ ከኢየሱስ በቀር ማንም ሊመጣ አይችልም። እርሱ ለተንኮታኮተውና በኀጢአት ምክንያት
ከእግዚአብሔር ፍቅር ርቆ ለቆመው የሰው ዘር ኹሉ፣ ክብሩንና ሰማያዊ ግርማውን ትቶ የመጣ ተወዳጅ መሲሕ ነው፤ ይህ ተወዳጅ
መሲሕ[ብቃት ያለው አዳኝ] ዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ከተናቀችውና ካደገባት የናዝሬት ገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ንጉሣዊ ክብር ያለው
ጌታ፣ ንጉሣዊ ክብሩን ጥሎና ትቶ ስለ ኀጢአተኞች “ጽድቅን ኹሉ ይፈጽም ዘንድ” ከጐስቋላዪቱ ምድር መጣ!
ጻድቅና ቅዱስ፣ ነውርና ዕድፍ የሌለበት የእግዚአብሔር በግ (ሉቃ.
1፥35፤ ዕብ. 7፥26፤ 9፥14፤ 1ጴጥ. 1፥18-19) ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ኀጢአተኞች ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ በዮሐንስ እጅ
ወደሚጠመቁበት፣ ከኀጢአተኞች ጋር ተሰልፎ ሊጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። መጠመቅ የማያስፈልገው ጌታ ከኀጢተኞች ጋር የተቈጠረ
ይኾን ዘንድ በአንድነት አብሮ ተጠመቀ። እርሱ ራሱን ከኀጢአተኞች ጋር በመቊጠሩ እኛ ጻድቃን እንደ ኾንን አስተውሉ!
ለኀጢአተኞች ብቃት ያለው አዳኝ መሲሕ፣ አደባባያዊ የመሲሕነት አገልግሎቱን
በመጀመር፣ ከኀጢአተኞች ጋር እንደ ኀጢአተኛ በመቈጠር ወደ ዮሐንስ አመራ፤ ለዚህ ታላቅ አገልግሎትም አባቱ አብ ምስክርነትን
ሰጠ፤ “በእርሱ
ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” በማለት። ኀጢአተኛው ዓለም አብን ደስ ያሰኝ ዘንድ ባይችል ወይም ደስ ለማሰኘት ፈጽሞ ቢሳነው፣
የአብ አንድ ልጅ መሲሑ ኢየሱስ ግን አብን ደስ ያሰኘው ዘንድ፣ ስለ ሰው ልጆች ኹሉ ብሎ ከኀጢአተኞች ጋር እንዴት እንደ ተቈጠረ
አስተውሉ!
“ለኃጢአት
ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር … እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት
አደረገው።” (2ቆሮ. 5፥21፤ ዕብ. 4፥14-15፤ 1ጴጥ. 2፥24) እንዲል፣ ጌታችን ኢየሱስ እጅግ ዝቅ ብሎ እንደ ኃጢአተኛ
ተቈጠረ። መጠመቅ አይገባውም፣ አስፈላጊውም አልነበረም፤ ነገር ግን ኀጢአታችንን ይሸከም ዘንድ የተገባ እንዲኾን፣ መሲሑ ራሱን በማዋረድ
ከዮርዳኖስ ወንዝ በኀጢአተኛው እጅ ተጠመቀ። ኢየሱስን የምትከተሉ አማኞቹ ኹሉ ሆይ! እንዴት ዝቅ እንዳለላችሁ ተመልከቱ! ከኀጢአት
ባርነት ያድናችሁና ነጻ ያወጣችሁ ዘንድ እንዴት ተዋረደና በኀጢአተኛ እጅ ሊጠመቅ እንደ ፈቀደ ተመልከቱ!
አዎን! ከቅድስት
ድንግል ሲወለድና ወደዚህች ምድር መጥቶ ከትውልዳችን የዘር ሐረግ ውስጥ ሲገባ፣ በሰው ምትክ እንደ ኀጢአተኛ በመቈጠር የመላለሙን
ኀጢአት ይሸከም ዘንድ የእግዚአብሔር ጽድቅ ፈቃዱ ነበር። አብ ልጁን “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ” ሲል፣ በኢየሱስ ስለሚገለጠው
ኹለንተናዊ ጽድቅ አብ ፍጹም ደስተኛ ነው፤ የወደደውም ነው። ምክንያቱም በፍጹም ሰውነቱ አንዳች እንከንና ነውር ሳይገኝበት አብን
ያረካና ደስ ያሰኘ ከኢየሱስ በቀር በሰማይና በምድር አንዳች የለምና!
መጥምቁ
ዮሐንስ አስቀድሞ ሊያጠምቀው አልወደደም፤ ምክንያቱም አንዳች ኀጢአት እንደሌለበት አውቆ ነበርና፣ ከሚጠመቁ ሰዎችም እጅግ የተለየ
ጻድቅ እንደ ኾነ አስተውሎ ነበር! “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” በማለትም መስክሮለት ነበር። አብም
መጥምቁ ዮሐንስም እንደ መሰከሩት ኢየሱስ የዓለምን ኀጢአት ይሸከም ዘንድ የመጣ ፍጹምና ጻድቅ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ለዮሐንስም
የተገለጠው ያ እውነት ለሌሎችም ተገለጠ፤ መሲሑ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑና ከኀጢአተኞች ጋር የተቈጠረ መኾኑ ለመላለሙ ታየ! ከኀጢአተኞች
ጋር የተቈጠረው መሲሕ ስለ ኹላችን በደል ተላልፎ የተሰጠና ያዳነን ነው፤ ኀጢአታችንን ሊሸከም የሚገባው መሲሕ፣ እርሱ እንደ ኀጢአተኛ
ተጠመቀ፤ በደሙ ቤዛነትም አጸደቀን፤ አሜን።
amen tebarek
ReplyDeletetsega yibzalh wendmachen
ReplyDeleteGeta yirdah
ReplyDeleteAmen Amen Amen Amen Amen Amen Amen, zemenehe yebareke
ReplyDeleteI love the way you preach the Gospel. You are very wise + passionate. Remain blessed.
ReplyDeleteGod bless you the message is support me very much
ReplyDelete