እግዚአብሔር
አምላክ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ከወጡ በኋላ፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር በተቃረቡ ጊዜ በተደጋጋሚ የተናገራቸው
ቃል ቢኖር እንዲህ የሚል ነው፤ “… ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን
እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤” (ዘዳግ. 8፥11፤ 4፥9፤ 6፥25)። የታዘዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ሊረሳ የሚችልባቸውን ምክንያቶችንም
ሲያስቀምጥ እንዲህ ይዘረዝራቸዋል፤
“ከበላህና ከጠገብህ
በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥ የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ
በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤ ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና
በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም
አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ በልብህም፦ ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን
ሀብት አመጣልኝ እንዳትል። ነገር ግን ዛሬ እንደሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት
ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ።” (ዘዳግ. 8፥12-18)
እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤል ልጆች በበሉና በጠገቡ፣ የተገጠገጠ ቤትም
ሠርተው ሲቀመጡ፣ ነገር በተደላደለ፣ ሥጋቸው በለደለደ፣ ኹሉ ነገር በተመቻቸ ጊዜ … በልባቸው በኩራት እንዳይንጓዱ፣ እንዳይመኩ፣
እንዳይታበዩ በብርቱ ማስጠንቀቂያ ነግሮአቸዋል፤ ምክንያቱም ሰው የመርሳት ባሕርይ አለበት፤ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር ሕዝቡን በፍቅር
የሚጣውና በወቀሳም የሚያቀናው ሰው ዝንባሌው መደዴ፣ አኗኗሩም ተላላነት የተመላበት ስለኾነ ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እንደ ኢያሱ ሃውልት ያሉ ምልክቶችን በእስራኤል በመካከላቸው
ያኖረው፣ እንደ ቅዱስ መቅደሱ ያለ ሊረሳና ሊጠፋ የማይችል ቋሚ ምስክር ያቆመው፣ በመሶብ ወርቅ እንደ ነበረው ሕብስተ መና ብዙ
ትዝታዎችን እንዲኖራቸው በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያስቀመጠው፣ ሕጉና ታቦቱ በመካከላቸው የነበረው፣ ታላላቅ ተአምራት የተደረገላቸውና
ዘወትር ተያይዞ ሲነገራቸው የነበረው እንዳይዘነጉትና በሕይወት ዘመናቸው ኹሉ እንዲያስቡት፤ ከአምላካቸው ፈጽመው በመለየት በኃጢአት
እንዳይወድቁ ለማስጠንቀቅም ጭምር ነው፡፡
ለብዙዎች ድሎትና ቅምጥልነት፣ መለዳለድና መደላደል አምላክን የሚያስረሳ
ክፉ ወጥመድ ነው፤ ትልልቅ የኃጢአት ዕቅዶች በብዙዎች ልቦች የተጸነሱት በምቹ ሰገነት ሲመላለሱ ነው፣ የኪዳኑን ታቦት ሸኝቶ ከጦርነት
የቦዘነው ንጉሥ ዳዊት፣ በሰገነት ሲመላለስ የድኻውን ኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህን በዝሙት አሰበ፤ በተከታታይ በፈጸመውም ስህተት፣ እጅግ
ታላቅ አወዳደቅን ወደቀ፤ ናቡከደነጾር ምድር ኹሉ በፊቱ በተገዛለት ጊዜና ነገር ኹሉ ተደላድሎለት በሰገነቱ ሲመላለስ ገና ኵራቱን
ተናግሮ ሳይጨርሰው ወደ እንሰሳነት ተለወጠ፤ ቅምጥልነት ለክፉ ነገር አሳልፎ ይሰጣል።ቅምጥሊቱ ግን በሕይወት ሳለች የሞተች ናት
እንዲል ታላቁ መጽሐፍ፣ ቅምጥልነትና በሃብት ስብ መስባትና እርሱን ፍለጋ ለሚንከራተቱ ከሕይወት መዝገብ ለመደምሰስ ምክንያት ኾኖባቸዋል።
ብዙዎቻችን በበላን በጠጣን ጊዜ ምን ይኾን የምናስበው? በተደላደልን ጊዜ
ምን ይኾን ትውስ የሚለን? የተገጠገጠ ቤት ሠርተን ስንገባ፣ ምቹ ደመወዝ ስናገኝ፣ ትዳራችን ሲሰምር፣ ርቢዎቻችን መንታ መንታ ሲወልዱና
ሲበዙ፣ እርሻችን መከሩ ሲትረፈረፍ ምን ይኾን ዕቅዳችን? ሌላ ጐተራ መገንባትና ማስፋፋት ወይስ ምን እናስባለን? የምናስበው ነገር
ውሎአችንና፣ አዳራችንን፣ ዘመናችንን ይወስነዋል።ለዚህ ነው እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች “እንዳትረሱ” በማለት ደጋግሞ ትድግናውንና
የሠራላቸውን ሥራ የሚያሳስባቸው፤ (ዘዳግ. 5፥15፤ 7፥18፤ 8፥2፡18፤ 9፥7፡27፤ 11፥2፤ 15፥15፤ 16፥3፡12፤ 24፥9፡18፡22፤
25፥17) አዎን መቼም የጥንቱን ዘመን፣ የሠራልንን፣ ያደረገልንን፣ ተአምራቱን፣ በተለይም ደግሞ
በኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠራልንን የጽድቅና የሕይወት ሥራ እንድንረሳ ፈጽሞ አይፈልግም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የተደረገልንን እንድንረሳ፤ ውለታ በል እንድንኾን አይፈልግም፤
እንዳልተደረገለት ሰው ያለ ኑሮ እንድንኖር አይፈልግም፤ እኛ አማኞች ሕይወት ተከፍሎልን የኢየሱስን ሕይወት የተቀበልን ነን፤ የተቀበልነው
ሕይወት በልቶ፣ ጠጥቶ፣ ከብሮ ደምቆ ከመኖር እጅግ ያልፋል፤ የተቀበልንም እንዳልተቀበልን እንድንኖር አልተባለልንም።
ጌታ እግዚአብሔር አብ ከምንም በላይ ልጁንና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል
ላይ ያደረገልንን ነገር እንድንዘነጋ አይሻም፤ ኢየሱስንና መስቀሉን መርሳት ከማንወጣበት አዘቅት ውስጥ ይጥለናል፤ ለዘላለምም ሞት
አሳልፎ ይሰጠናል፤ እርሱን ማሰብ ግን ሕይወትና ተድላ የዘላለምም ዕረፍት ነው፤ አሜን።
ይቀጥላል …
tru melkt new
ReplyDeletetsega yibzalih wendm abeni
ReplyDelete