Please read in PDF
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ከተነሣ በሃምሳኛው ቀን፣ ወደ
ሰማያት ባረገ ደግሞ በአሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ገባላቸው ተስፋ ቃል ከአባቱ ዘንድ በመላክ የቤተ ክርስቲያን
ልደት አብስሮአል።
ከግሪኩ “ፓራክሊቶስ” ወይም ከዕብራይስጡ “ፕራቅሊጥ” ከሚለው ግስ የተገኘው፣
“ጰራቅሊጦስ” የሚለው ቃል ትርጉሙ፦ “አማላጅ፣ አስታራቂ፣ አፍ፣ ጠበቃ፣ ትርጁማን፣ አምጃር፣ እያጣፈጠ የሚናገር፣ ስብቅል ካፉ
ማር ጠብ የሚል።…፤ ናዛዚ፣ መጽንዒ፣ መስተፈስሒ፤ መንፈስ ቅዱስ” በማለት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተርጉመውታል። [1]
ጌታችን ወደ ሰማያት ከማረጉ በፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ “ለዘላለምም ከእናንተ
ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል … ” (ዮሐ. 14፥16) በማለት ደግሞ የመንፈስ ቅዱስን አጽናኝነት በመግለጥ ለደቀ መዛሙርቱ፥
ልክ እንደ እርሱ መንፈስ ቅዱስም ሁሉን እንደሚያደርግላቸው የተስፋ ቃልን ሰጥቷቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መተርጉማን ደግሞ፣ ጰ[ፐ]ራቅሊጦስ
የሚለውን ቃል በቀጥታ ፍቺው “ፓራ” ማለት “አጠገብ” ማለት ሲኾን፤ “ካሌው” ማለት ደግሞ “መጥራት” ብለው በመተርጎም፣ ሲተነትኑት
“ሊራዳ፤ ከአማኝ ጎን የሚቆም” በማለት ተርጉመውታል። ይህም ሊያጽናና፣ ሊያበረታታ፣ ሊያረጋጋ፣ ሊራዳ፣ ሊያማክር፣ ሊሟገት፣ ወገንና
ወዳጅ ሆኖ ሊቀራረብ ከአማኝ ጐን ይቆማል የሚል ሃሳብን በውስጡ ይይዛል ብለዋል።
የመንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስነት ማለትም አጽናኝነት ለቤተ ክርስቲያን ዋናና
ዘወትር የሚያስፈልጋት ነው። ዓለሙ በክፉ የተያዘ ስለሆነ (1ዮሐ. 5፥19)፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ በጐች በተኩላዎች መካከል የተላከችና
በሸንጎ ፊት ተላልፋ ልትሰጥ፤ ልትከሰስ፤ በየምኩራቡ ልትገረፍ፣ ወደ ገዢዎችና ነገሥታት ልትወሰድ (ማቴ. 10፥16-20)፣ በጽኑ
መከራ ውስጥ ልታልፍ … ግድ ነውና፥ የዚያኔ “የምትናገረውን የሚሰጣት … እንዴት ወይስ ምን ብላ መመለስ እንዳያስጨንቃት ወይም
እንዳይቸግራት በእርሷ አድሮ የሚናገር አጽናኝ መንፈስ፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው።
እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ከአንድ አማኝ ጋር የሚሠራ ብዙ ሥራዎች አሉት ከእኒህ
ሥራዎች መካከል ማጽናናት አንዱ ነው። ልክ ክርስቶስ በምድር ሳለ ደቀ መዛሙርቱን ያጽናና፣ ያበረታ፣ ያማክር፣ ይሟገትላቸው፣ ይራዳቸው
እንደ ነበር፣ መንፈስ ቅዱስም “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” (ዮሐ.
14፥15) እንዲል፣ መንፈስ ቅዱስም ዛሬ በክርስቶስ ለሚያምን አማኝ ያንኑ ሥራ ሳያቋርጥ ያደርገዋል፤ እናም መንፈስ ቅዱስ ከአማኝ
አጠገብ ቆሞ የሚያጽናና፣ የሚያበረታ፣ የሚደግፍ፣ ሊራዳ ዘወትር የሚቆም የደስታ ወዳጅ ነው።
እውነተኛ አማኝ ሁልጊዜ ከሥጋና ከደም ጋር ያይደለ (ኤፌ. 6፥12) ከመንፈሳዊያን
የክፋት ሠራዊት ጋር፣ ከኃጢአትና ከክፉው ዓለም ጋር ከፍ ያለ ውጊያ አለበት፤ ውጊያው ደግሞ ለሥጋ ጠባይ እጅግ ደስ የሚያሰኝ አይደለምና
ብርቱ ክርክር፣ ፍትጊያ፣ ስቅየትና፣ መከራና ትግል አለበት፤ ይህን ደግሞ ማንም በሥጋው ይቋቋመው ዘንድ አይችልም። የምንዋጋቸውን
በሥጋ አቅም ልንዋጋ የማንሞክራቸው ከኾነ፣ የውጊያው ስልቱና መሣሪያውም መንፈሳዊ ከኾነ እስከ መጨረሻ በውጊያው ለመጽናትና ድል
ለመንሣት ብርቱ አጽናኝና “አይዞህ ካንተ ጋር ነኝ” ባይ ብርቱ አጽናኝ ወዳጅ ያሻናል።
በአጭሩ ብንመለከት ከሥጋ ጋር ያለን ውጊያ ውስጣዊና ኃጢአትን ፊት ለፊት
የምንቃወምበት ወይም የምንሸሽበት አጽናኝ አቅም ያስፈልገናል። ኃጢአትን ያለ ቅድስና ድል መንሣት አንችልም፣ ቅድስና ደግሞ መንፈስ
ቅዱስን ዘወትር ባለመተውና ባለማሳዘን (ኤፌ. 4፥30) የምንኖረው ሕይወት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሰውነትን ሥራ መግደል
እንችላለን፤ (ሮሜ 8፥13)። ቅድስና የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነውና፤ (ሮሜ 8፥3-4፤ 2ተሰ. 2፥13፤ 1ጴጥ. 1፥1-2)። ምንም
እንኳ “በቅድስና ያጌጥን” ብንኾን እንደ ዝሙት ያሉ ኃጢአቶችን ማምለጥ የምንችለው መንፈስ ቅዱስ በሰጠን ኃይል ጨርቃችንን ጥለን
እንደ ዮሴፍ መሸሽ ስንችል እንጂ ቆመን በመዋጋት ወይም በመጋፈጥ አይደለም።
ክርስቲያን ኃጢአትን በተመለከተ አቋሙ ግልጥና አንድ ነው፤ መጥላትና መጸየፍ
ብቻ። ክርስቲያን በማናቸውም መንገድ የመንፈስ ቅዱስን አጽናኝነት በትክክል ከተረዳና ከቀመሰ ፈጽሞ ስለኃጢአት አያመቻምችም፤ አያድበሰብስም።
መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኙ ከመምጣቱ በፊት ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘውን የእግዚአብሔር ልጅነትን ዘር በውስጡ ስለሚያኖር፣
አማኙ ዘወትር ልቡ፣ ሃሳቡ፣ ፈቃዱ፣ መሻቱ፣ ፍላጎቱ፣ መቃጥኑ ወደ ሕይወት ምንጭ ወደ እግዚአብሔር ያዘነብላል፤ “ከእግዚአብሔር
የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም” እንዲል
(1ዮሐ. 3፥9)። ይህን ለማድረግ ግን ያለ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት ልናደርገው አንችልም።
ከዓለምና ከሰይጣን ጋር የምናደርገው ትግልና ውጊያ ደግሞ እንደ ኃጢአት
ከውስጣችን የሚመጣ አይደለም፤ የሚመጣው ከሰውነታችን ውጪ ነው፤ ዘወትር ግን በዙርያችን የሚዞርና የሚንቀዋለል ነው፤ (ኢዮ. 1፥7፤
1ጴጥ. 5፥8)። ዓለምና ሰይጣን እጅግ ክፉዎች ናቸው፤ ኃይለኞችም ናቸው፤ ፈጽሞ በግልጥበብ፣ በራስ ጽድቅ፣ በጾማችን፣ ባለን ደግነትና
ርኅራኄ ልናሸንፋቸው የምንችል አይደለንም። ከጽናታቸውና ከብርታታቸው የተነሣም በሥጋ ጉልበት በፊታቸው መቆም አንችልም።
በማናቸውም የዓለም ተግዳሮትና በሰይጣን ሽንገላና ማስፈራራት ፊት እንድንቆም
የሚያበረታን፣ የሚያደፋፍረን አጽናኛችን፣ የሚያበረታን መንፈስ ቅዱስ ነው፤ (ሐዋ.
23፥11)። በማናቸውም መንገድና በየትኛውም ጥበብ እኒህን ሦስቱን ጠላቶች ፈጽሞ ድል ልናደርጋቸው አንችልም። መንፈስ ቅዱስ በዳግም
ልደት ተወልደን ያለነውን በእኒህ ጠላቶቻችን ላይ ድልን ያጐናጽፈናል።
ራሱን ለመንፈስ ቅዱስ ያላስገዛ አማኝ ከሦስቱ [ከኃጢአት፣ ከዓለምና ከዲያብሎስ]
ለአንዱ ማስገዛቱ አይቀርም፤ ሰዎች ኃጢአትን ጭልጥ አድርገውና በኃጢአት ጭላጭ ሲረኩ ስናይ ወይም ሰዎች በኃጢአትና በዓለም ክፉ
ምኞት ተወግተውና ተተብትበው ስንመለከት ማስተዋል ያለብን፣ ዲያብሎስ እንዴት እንዳዳለጣቸውና እንደጣላቸው በማጤን ልንራራቸው፣ ልናዝንላቸው፣
የመንፈስ ቅዱስ መጽናናት በክርስቶስ በደሙ መፍሰስና ከሙታን መካከል በመነሣቱ እንዲደርሳቸው ልንማልድ፤ በብርቱ መሻት ልንጸልይላቸው
ይገባል፤ እኛም ኹል ጊዜ በመጽናናቱ ጥላ ሥር በመኾንከኃጢአት ኹሉ ልንርቅና ልንጠበቅ ይገባናል፤ አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ በመጽናናቱ
ያመንነውን ያበርታን፤ ያላመኑትን ደግሞ በጽድቅ በፍቅር ይውቀስ፤ አሜን።
No comments:
Post a Comment