Monday 17 December 2018

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 5)

Please read in PDF
1.3.           መለያየት
(ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት የፖለቲካ ትርፍ እንጂ፣ እንደ ጌታ ቃል አልታረቀችም)
    መለያየት ከሥጋ ሥራዎች አንዱ ነው (ገላ. 5፥21)፤ ቅዱስ ጳውሎስ በልመና ቃል “ወንድሞች ሆይ፥ ኹላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትኾኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይኾን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” በማለት ይናገራል (1ቆሮ. 1፥10)፤ መለያየት መነሻው የገዛ ምኞትን ከመከተል እንደኾነ ሲገልጥ ጠቢቡ “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” በማለት ገልጦታል።
    የታረደው በግ “ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ከዋጀ” (ራ. 5፥9) ቤተ ክርስቲያን ከልዩነት ይልቅ የመንፈስ አንድነት ላይ ትልቅ ሥራ ልትሠራ ይገባታል። የመለያየት መንፈስን ማጥፋት የሚቻለው ማንነታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የተወረሰና የእኛ የኾነ ምንም እንደሌለን መረዳት ሲቻለን ነው። ይህም ዳግመኛ መወለድን ማዕከል ያደረገ ነው፤ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ሮሜ 12፥10) የሚለን ሕያው ቃሉ እንደማይለያይ ወይም መለያየት እንደማይችል ቤተሠብ አንድ መኾናችንን ያገናዝባል።

    የሥጋ ወንድማማችነትን መካድ አይቻልም፤ ብንክደው እንኳ እኛ ውሸታሞች እንሆናለን እንጂ ወንድምነትን መካድ አንችልም። እንዲሁ አንድ የኾንበትንና የተወለድንበትን ዘር፣ ባህል፣ አከባቢ፣ ወንዝ … መካድ ፈጽሞ አንችልም።  “ትልቁንም ትንሹንም” መርጠን አላገኘነውም፤ ፈጽሞም ለልዩነት እንደ ምክንያት መቅረብ የሌለበት ነገር ነው። ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከዚህ ነውር ነጽታ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የፈረሰውን ልዩነት መልሳ ከመገንባት እጇን ልትሰበስብ፤ ይህን የሚያድርጉትን ልትምክር፣ ልትገስጽ፣ በመቆጣትም ልትመልስ ይገባታል።
  ላለመተያየት የጥላቻ ግንብ ገንብተናል። መናፍቃንና ከሐዲያንን ለማውገዝ የምንጠቀምበትን ሰማያዊ ሥልጣን ባልንጀራችንና ወንድማችንን ለማውገዝ በድፍረትና በትዕቢት ተጠቅመንበታል። አለም እስኪታዘበን ድረስ በአደባባይ መጠላላታችንንና መለያየታችንን በአዋጅ አሳውጀናል። ጥር 25 1999 ዓ.ም ከምሽት ዜና በኋላ ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው ሲኖዶስ በአሜሪካ የሚገኘውን ሲኖዶስ በመረረ ውግዘት ማውገዙን ሰምተናል፤
§  “ሊቃነ ጳጳሳት፣
§  ጳጳሳት፣
§  ኤጲስ ቆጶሳት፣
§  ቆሞሳት፣
§  ቀሳውስት፣
§  ዲያቆናትና መዘምራን፣
§  ምዕመናንና ምዕመናት በሙሉ … የተሰበሰቡትን የዘመናችን የጸረ ማርያምን የተሐድሶ መናፍቃን ስብስቦች ቃላቸውን እንዳታምጡ፣ ትምህርታቸውንም እንዳትቀበሉ፣ ኢ-ቀኖናዊ ሥርዓታቸውን እንዳትከተሉ፣ ሥልጣነ ክህነትም ከእነርሱ እንዳትቀበሉ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ከእነሱ ጋር እንዳትሳተፉ፣ የእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዟል” በማለት አባቶቻችን በአንድ በረት እንዳለ ኹለት ወይፈን መቻቻል ተስኗቸው ሲወጋገዙ ታዝበናል።
    በዚህ ሳያበቃ የአሜሪካውም ሲኖዶስ “ክፉን በክፉ በመመለስ” ጥር 30፣ 1999 በአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ፕሮግራም “… በሕጋዊው ሲኖዶስ የተወገዙትን… ቃል እንዳትሰሙ፣ ትምህርታቸውን እንዳትቀበሉ፣ በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከእነርሱ ጋር ኅብረት እንዳይኖራችሁ፤ … በስደት አገር የሚገኘው ሕጋዊው … ሲኖዶስ አውግዞአል …” በማለት አስነብቦናል።
   እንኪያስ፦ በቃለ እግዚአብሔር ዳኝነት ማን ይኾን ትክክል? “የውግዘትን ኃይል” የምንጠቀመው ለምንድር ነበር? ተወጋግዞ ጉዞ ለመኾኑ የት ያደርሰናል? ብዙዎች በዚህ ውግዘት መካከል ከማቀራረብ ይልቅ ውዳሴና መወደድን ለማግኘት ብለው በእሳቱ ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ሃፍረት እንኳ አልተሰማቸውም? ይህ ውግዘት ሳይፈታ ዛሬም ኹለቱም አካላት “ጸሎትን ለአምላካችን ነው” ይላሉ። ግና ባልንጀራን ላለመቀበልና ወንድምን በሚጠላ ነፍሰ ገዳይነት ውስጥ ኾነን (1ዮሐ. 4፥20)፤ የሰማይ ደጅን በገዛ እጃችን ቈልፈን ቅዳሴና ምህላ እንዴት ያለ ምስኪንነት ነው!!!? ብናውቅስ እግዚአብሔር አይዘበትበትም!
   የተወጋገዙት ጳጳሳት አብዛኛዎቹ ዛሬም በሕይወት አሉ። ግና አኹንም ለይቅርታ ሊሸነፉና ከእግዚአብሔር የለያያቸውን ቂመኝነትና አልታዘዝ ባይነት በንስሐ ለመሸፈን ያሰቡም አይመስሉም። ግና በገዛ እጃችን የገነባነውን የመለያየት ግንብ በንሥሐና በይቅርታ ካላፈረስን ለእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ “እየሰባን” ለመሆናችን ምንም አይጠረጠርም።
   በአደባባይ ተጣልተው በጓዲያ የታረቁ ሲኖዶሶቻችንን ጌታ ኢየሱስ ምሕረት ያድርግላቸው! አሜንበአደባባይ ለመወጋገዝ አቅም አለን፤ በአደባባይ ለመታረቅ ግን እናፍራለን፤ ነውሩ በመካከላችን ከበረ፤ ሊከበርበት የሚገባው ደግሞ ታፈረበት፤ ጌታ በምሕረቱ ይድረስልን፤ አሜን!

ስለመለያየቱ ምን ይደረግ?

ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ ትጠይቅ!
    የሮማው ፖፕ የነበሩት ዳግማዊ ጆን ፖል ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት የመራችውንና ለብዙዎች ማለቅ ምክንያት የኾነውን የመስቀል ጦርነት ዳግም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትወቀስ ያደረጉት፣ በዓለም ሁሉ ፊት በግልጥ ስለድርጊቱ ይቅርታ በመጠየቃቸው ነው። እግዚአብሔር “እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት ፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ … ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የሚዘገይ፥ ምሕረትንም የሚያበዛ ነው ፥ … ምሕረቱንም ለሚጠሩት ሁሉ የበዛ” ነው። (ዘጸአ. 34፥7-8፤ ነህ. 9፥17፤ መዝ. 85፥5)
   ይቅርታን ለሚሹ በእውነት እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነው። በኃጢአታችን ጸንተን እልኸኞች ብንኾን ግን “በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” (ዘጸአ. 34፥7) አብ በልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ በሞቱ የሰጠንን የይቅርታ ዘመን ልንጠቀምበት ይገባናል። አልያ ግን እግዚአብሔር ፈራጅም ነው። ቤተ ክርስቲያንም በመለያየትና ልዩነትን በማስፋት ዙርያ በግልጥ የተሰበሰቡ ጉባኤያትን በማረም፣ ስለስህተትነቱም ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባታል።

ንስሐ መግባት
     መለያየት ከሥጋ ሥራዎች አንዱ ነው (ገላ. 5፥21)፤ “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆንን ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለናልና” (ገላ. 5፥24) “ሁላችን አንድ ንግግር እንድንናገር በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበርን እንድንሆን እንጂ መለያየት በመካከላችን እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በፍቅር ልመና ተለምነናል” (1ቆሮ. 1፥10) በቤቱ ያለን ወንዶችና ሴቶች የክርስቶስን መንግሥት በመውረስ አንበላለጥም፤ ክርስቶስ ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ሲመጣ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” (ማቴ. 25፥34) የሚላቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ነው።
   አለም እንኳ መለያየት እንዳላዋጣት አስተውላ ወደ አንድነት መምጣት ከጀመረች፣ መሰነባበቷን የበርሊን ግንብ ተንዶ ጀርመን አንድ መኾኗን ትልቅ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። የክፉዎች አጋንንትም መለያየት መንግሥታቸውን እንደማያጸና ጌታ፦ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?” (ማቴ. 12፥24-25) በማለት አጽንቶ ተናግሯል። ክፉ እንኳ ለክፋቱ መተባበር እንዳለበት ካመነ ቤተ ክርስቲያን “ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያየች አብልጣ ማድረግ ያለባትን መሰባሰብንና እርስ በርስ መመካከርን” (ዕብ. 10፥25) ስለምን ይኾን የተወችው?
   ዛሬ ላይ ክርስትናን “ሊያጠፉ” (አይቻላቸውም እንጂ) የተነሱ አካላት በሙሉ ኃይላቸው በአንድነት ሲነሡ፣ ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿን አንድ የሚያደርግ የአንድነትን መንፈስ ማጣቷ እጅጉን ልብ የሚነካ ነገር ነው። ከመሥዋዕት በፊት መታዘዝ፣ ከመጰጰስና ከመመንኮስ በፊት ለባልንጀራ ይቅርታ ማድረግ፣ ቁርባን ከመፈፈትና ከመቀደስ በፊት ምሕረት ማድረግን ትተን ከቂም ጋር መቁረብን፣ ከጥላቻ ጋር ወንጌል መስበክን፣  ከመለያየት ጋር መዘመርን፣ ካለመስማማት ጋር ቀድሶ ማስቀድስን ከየትኛው ወንጌል ይኾን ያገኘነው?
  የሥልጣን እርከናችንና ትዕቢታችንን ለማጽናት ወንጌልን ወደ ጐን በመግፋት ለትውልድ የመለያየትን ነውር ማቆየታችን፣ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ቅጣት እንደምናገኝበት ግን ምንም ልንጠራጠር አይገባንም። እግዚአብሔር “ኹለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ. 18፥20) አለ እንጂ፣ በተለያዩና በማይስማሙ ሚሊዮኖች መካከል እገኛለሁ አላለምና ምክንያታችንን አስወግደን ያለምንም ቅድመ ኹኔታ ንስሐ እንግባ።

ይቅርታን መስጠትና መቀበል
    አባቶቻችን እውነተኛ አባቶች ከኾኑ የሚኖሩትን ኑሮ በእውነት ሊያሳዩን ይገባል። የጠብ ግድግዳቸውን በይቅርታ አፍርሰው “… በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ … እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” (ፊሊጵ. 2፥2-4) የሚለውን ቃል ፈጽመው ማየትን እንወዳለን። ሌሎችን ከማስታረቃቸው በፊት እነርሱ በትክክል እንደ ቅዱስ ቃሉ ታርቀው፣ ልዩነታቸውን ሽረው፣ ጠባቸውን በፍቅር አጥበው … በወንድማማች መንፈስ አንድ ኾነው አብረው በአንድነት ቅዳሴ ገብተው፣ የጌታ እራትን ላይ ተካፍለው ሲያካፍሉ ማየትን ነፍሳችን አብዝታ ትናፍቃለች!!! መቼ ይሆን?! ችግራችን እየተጐተተ ሲከተን መች ይኾን ቈርጠን የምንጥለው?!
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን።

ይቀጥላል …

2 comments:

  1. በአደባባይ ተጣልተው በጓዲያ የታረቁ ሲኖዶሶቻችንን ጌታ ኢየሱስ ምሕረት ያድርግላቸው! አሜን።

    ReplyDelete