Thursday 13 December 2018

ቤተክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 4)

Please read in PDF
1.3.           የአስተምህሮ ዝንፈት
“ከትምህርት የተነቀለ ከሕይወት የተሰናበተ ነው።”[1]

“ …ፍሬምናጦስ አኹን ተገኝቶ ያለውን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊትና ድኅነት፣ ወንጌልና ትውፊት መደበላለቅና መተራመስ ቢመለከት ያዝን ነበር ብዬ አስባለሁ። …”[2]
“በክርስቶስ … ሆኖ” ሃይማኖትንና ምግባርን ሳይለያዩ ሁለቱንም በአንድነት ማወቅና አውቆም መፈጸም ለክርስቲያን ሁሉ አስፈላጊ ነው። ከሁሉ በፊት ሃይማኖት ይቀድማል። ስለሆነም … እርሱን በቅድሚያ መማርና ማወቅ ይገባናል። ዳሩ ግን ክርስትናችን ስለሃይማኖት በመማርና በመመራመር፥ በማጥናትና በማወቅ ብቻ አያከትምም። ምክንያቱም ከላይ እንደጠቀስነው “እምነት” ስንል “በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ” እንዲያው እምነት በተናጠል ብቻውን በእውቀትና በትምህርት ደረጃ ብቻ የቆመ ነገር አይደለም።”[3]

     የመጀመርያዪቱ ቤተ ክርስቲያን በኹለት እግሮቿ ጸንታ የቆመችው፣ “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም በመትጋት” (ሐዋ. 2፥42) ነው። የአስተምህሮ ጤናማነት አምልኮን፣ ልምምድን፣ ጸሎትን፣ መንፈሳዊ ኹለንተናን ይጠብቃል፤ የአስተምህሮ መዛነፍ ግን አምልኮን፣ ልምምድን፣ ጸሎትን መንፈሳዊ ኹለንተናን ይበክላል፣ ይመርዛል፣ ለሞትም አሳልፎ ይሰጣል። ለትምህርት አለመጠንቀቅ ለሕይወት አለመጠንቀቅ ነው፤ ማንም ሕይወቱን ለአደጋ አሳልፎ መስጠትን ገንዝብ አያደርግም፣ ለትምህርት አለመጠንቀቅ ቀስትን በቀሰተ ቀስተኛ ቀስት ፊት ደረትን ገልብጦ ከመሄድ ይልቅ እጅግ ይከፋል። የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ከእውነት ጽናት የተልመጠመጠችው “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም በመትጋት” ፈንታ ብዙ እልፍ የሰው ጥበብና ጽድቅ መጣፊያዎችን በመጣፏና አሸንክታብን በማብዛቷ ነው።
   ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ኾና ለትምህርቷ ካልተጠነቀቀች አይስቱ መሳት ትስታለች፤ በዓለም ላይ ትልልቅ ውድቀቶች የተከሰቱት፣ የቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ትምህርት መሳትን ተከትለው የመጡ ናቸው ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን። ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ትምህርት በተዛነፈችበት ዘመን ኹሉ፣ ዓለም ቅጥ አምባሩ በጠፋው ርኩሰት ውስጥና በሚዳሰስ የክፋትና የስህተት ጨለማ ውስጥ ይመላለስ እንደ ነበር ታሪክ ሕያው ምስክራችን ነው።
  የተሰቀለው ክርስቶስን የሚናኝ፣ የወንጌል ትምህርት ብርሃን የማታንጸባርቅ፣ አሰምታ የማታውጅ፣ ጮኻ የማትሰብክ … ቤተ ክርስቲያን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከመመላለስ በቀር ምንም ዕጣ ፈንታ፣ ጽዋ ተርታ የላትም። የወንጌል ትምህርት የቤተ ክርስቲያን ህልውና ነው፤ ሳትታክት የማትሰብክ ቤተ ክርስቲያን ህልውናዋን በገዛ ፈቃድዋ ለጥፋትና ሞት ትሰዋለች፤ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ክርስትና መቀጨጭና መቀንጨር፣ መውደቅና “እንደ ዕድሜው” ፍሬ ያለ ማፍራት ዋነኛ መንስኤው፣ የወንጌል እንደ ጌታ ፈቃድና ሃሳብ አለመሰበክ ነው።
    ወንጌሉ ሲሸቀጥ፣ ሲለወጥ እንጂ እንደ ዕድሜው ሲሰበክ፣ የምስራች ተብሎ ሲታወጅና ሲበሰር አልኖረም፣ ወንጌል የሚመስሉ ነገሮች በዝተው ታዩ እንጂ በርግጥ ወንጌል ሲሰበክ አልታየም፤ ወርቅ በእሳት እንዲያልፍ ጥቂቶች በብዙ መከራ ውስጥ አልፈው፣ ወንጌል በሕይወታቸው ጨክነው ቢሰብኩም፣ “ወንጌል ጨብጫለኹ”፣ ባለችው በዚህችው ቤተ ክርስቲያን በመራር መከራና ጆሮ ጭው በሚያደርግ ሰቆቃ አሳልፋ ገድላለች። ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ለዚህ ዋና ምስክር ናቸው።
ንኪያስ ምን እናድርግ?
ü  ሰው ጽድቅ የሚያቆሙ መጻህፍት ይወገዱ!
     የቀደሙት እስራኤል ዘሥጋ፣ “የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።” (ሮሜ. 10፥3) አይሁድ ክርስቶስን ብቻ በማመን የሚገኘውን ጽድቅ ሊያውቁ፣ ሊቀበሉም አልወደዱም፤ እናም ለዚህ ጽድቅ መታዘዝን አልመረጡም፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ያቆመውን ጽድቅ ንቀው፣ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ወደዱ፤ ይህም በገዛ ሥራቸው ለመዳን ወደዱ፤ ጌታ ኢየሱስ “እየተናገሩ አያደርጉትምና” እንዳለው፣ እነርሱ የሚናገሩትና የሚያደርጉት አንድ አልነበረም፤ (ማቴ. 23፥3)፣ ደግሞም “ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤” (ማቴ. 23፥5) በማለትም ከሰው ዋጋ ለመቀበል እንጂ ፈጽሞ ለእግዚአብሔር እንደማይታዘዙ በግልጥ ተናግሮአል።
    ሰው ሊድን የሚችለው እግዚአብሔር ባዘጋጀው በክርስቶስ ጽድቅ ብቻ ነው፤ በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ግን ከበቂውና ከብቸኛው ከክርስቶስ ጽድቅ ውጪ ብዙ “የመዳን የጽድቅ መንገዶች” ተዘጋጅተዋል፤ በመጻሕፍትም ደረጃ ተደራጅተው ተቀምጠዋል፤ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተትና ላሉት ነባራዊ ችግሮችና ውድቀቶች መሠረቶች ናቸው። የክርስቶስን ጽድቅ በመኰነን የሰውን ጽድቅ የሚያቆሙ እኒህ መጻሕፍት ሊወገዱ ይገባል የምንለው ለዚህም ነው። የሰውን ጽድቅ የሚያቆሙ መጻሕፍት በጉያችን ሸሽገን ይዘን፣ ጤናማ ክርስትናና መንፈሳዊነትን ማለም ከሕልምነትና ከቅዠትነት አያልፍም።
   ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ሰሚ አላገኙም እንጂ በግልጥ እንዲህ ብለው ነበር፦
“በታሪክም ሆነ በተጨባጭ ተሞክሮ እንደምናውቀው ሰው በክርስቶስ ላይ ባለው እምነቱ ይጸድቃል፤ ይድናል እንጂ የሙሴን ሕግ በመፈጸሙ ወይም በራሱ ጥሬትና ሥራ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ሰው ሕግን መፈጸም ስለተሣነው፣ ሕጉም ሰውን ለማዳን ስላልቻለ ሰውን ወዳጅ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ በእምነት የሚያጸድቅበትና የሚያድንበትን መንገድ በልጁ አዘጋጀ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር ሰው የመዳኑ ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲሁ ያለ ዋጋ እንዲያገኝ ሆነ። ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ በሰው ጥረትና ሥራ ስላልሆነ ማንም ሰው በሥራው ሊመካ አይችልም፤ (ኤፌ. 2፥8-9)።”[4]
    ቤተ ክርስቲያን ከወንጌል ውጭ፣ የሰውን ጽድቅ አበረታች የኾኑ መጻሕፍቷን ኹሉ ማስወገድና የክርስቶስን የጽድቅ መንገድ ብቻ ማሳየት አለባት፤ የክርስቶስን የቤዝወት ጽድቅ እየገፋች ሰዎች በግል ጥረታቸው፣ በመውጣት መውረዳቸው፣ በመጾም መስገዳቸው፣ ለድሃ በመቸራቸውና ገዳማትንና አድባራትን በመጎብኘታቸው … በዚህ በረከት፣ መዳን፣ ጽድቅ፣ የኀጢአት ስርየት … እንደሚያገኙ የሚያስተምሩ የትኞቹም መጻሕፍት ኾኑ መንገዶች፣ ከክርስቶስ ትምህርት ተቃራኒ ብቻ ሳይኾኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ከነችግሮቿ እንደ ነበረች አኹንም በአሰቃቂ ችግሮቿ ጭምር እንድታዘግም የሚያደርጋት የክፋት መንገድ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ተመየጢ!
ü እውነተኛው ወንጌል ይሰበክ
    ወንጌል የማናቸውም ችግር ፍጹም መፍትሔ ነው፤ ለመንፈሳዊና ለምድራዊው መፍትሔዎቻችን ኹሉ ከወንጌል የሚተካከል መፍትሔ እንዳለ በአማራጭ እንኳ ማቅረብ አለመታደልና የወንጌል ኀይልን በትክክል አለማወቅ ነው። ቤተ ክርስቲያን ከወንጌል የሚበልጥ ወይም የሚተካካል ምንም አቅምና ብቃት አልተሰጣትም። ቤተ ክርስቲያን እንኳን ለቤተ መንግሥት ምሳሌነት፣ ለራሷ እንኳ እርባና ቢስ የኾነችው በሙሉ ኃይሏ ወንጌልን መስበክ ባለመቻሏ ነው።
    መንፈስ ቅዱስ በሙሉ ሥልጣን እንዲሠራና ክርስቶስን ሊያከብር እንዲመጣ፣ የተሰቀለው ክርስቶስ በሙሉ ኃይል መሰበክ አለበት፤ መቼም እንዲህ ሲባል “ምነው ለኹለት ሺህ ዘመናት ኦርቶዶክስ ክርስቶስን ስትሰብክ አልነበረም ወይ? ለምድሪቱ ክርስቶስ መች እንግዳ ኾኖ ያውቅና? ክርስትናን በመቀበል ቀደምት አይደለንም ወይ? …” የሚሉ አያሌ ጥያቄዎች ሊግተለተሉ ይችላሉ፤ እውነት ነው፣ ክርስትና በመቀበል አውራ ነን፤ ከቀደምቶቹም ተርታ የምንመደብ ነን፤ ነገር ግን ክርስትናንም በመቃወም የሚተካከለን ያለ አይመስለኝም፤ በነ አባ ሠላማ የተሰበከው ክርስትና ያልጸናው፣ በደቂቀ እስጢፋኖሳውያን የተሰበከው ክርስትና ዶግ ዐመድ የኾነውና ለትውልድ እንዳይቀጥል የተደረገው የነገሥታቱን ክንድ ቤተ ክርስቲያን በንጉሣዊው ችሎት ፍርድና በሰይፍና ስለቱም ጭምር ታዝዝበት ስለነበር ነው። 
    እናም ቤተ ክርስቲያን የገፋችውን ወንጌል፣ የጣለችውን የሕይወት ክርስትና፣ የናቀችውን የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን፣ ያረከሰችውን የክርስቶስን ደምና የቤዝወት ሥራ ዳግም በንስሐ በማደስ ልትቀበለው፣ ልታውጀው፣ ልታከብረው፣ ልትቀደስበትም ይገባታል፤ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ወንጌል በሙሉ ኀይል መናኘትና ማወጅ ብቻ ነው!!! የዘመን ችግራችን ወንጌል ብቻውን ደምቆ፣ ገንኖ፣ ተልቆ፣ ልቆ፣ ያለአማራጭ ብቻውን አለመሰበኩ ነው! መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን።

ይቀጥላል …





[1] ወንድም ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን፣ በቀን 12/1/2011 በ1ጢሞ. 3፥16 ላይ ተንተርሶ ሲያስተምር ከተናገረው የተወሰደ።
[2] አንድ ኦርቶዶክሳዊ አባት ከተናገሩት የተወሰደ።
[3] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)። ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት። 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት (ማኅበረ ቅዱሳን)፤ ገጽ 13
[4] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)። ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት። 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት (ማኅበረ ቅዱሳን)፤ ገጽ 12

3 comments:

  1. አታድክሙን!!!
    መተታም፣ጠንቋያም ቄስ፣መሪጌታ...ጳጳስ፣ፓትርያርክ ከነ አስተብታቢና አስጠንቋይ ሰዎች ሙልጭ ብላችሁ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውጡ....ብትፈልጉ ጴንጤ ብትፈልጉ እስላም ሁኑ።
    .
    .
    በእናንተ የሞራል ውድቀትና ዝብርቅርቅ ምክንያት የሚፈጠርባችሁን ቁጭትና ብሶት ለመደበቅ የማታውቁትን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በመቃወምና በማጥላላት እንደ ሽፋን ተጠቅማችሁ ለመጰንጠጥና ለማጰንጠጥ እየተሯሯጣችሁ መሆኑን እናውቃለንና...አታድክሙን።
    .
    .
    .
    ብሶትና ቁጭታችሁን ብትፈልጉ ጰንጥጣችሁ ካልሆነም ሆስፒታል ሄዳችሁ መታከም መብታችሁ ነው።

    ReplyDelete
  2. Dirom ke aryos teketay min yitebekal.....atdkem

    ReplyDelete