Wednesday 1 August 2018

“ … ይጸለይባችኋል” ፤ እንዲህም ደግሞ መች ነው የተጀመረው?

Please read in PDF
(ምነው ነውራችን አላልቅ አለ?)
   ከአንድ ወዳጄ ጋር በሥራ ምክንያት ተገናኝተን የቤተሰቡን የውርስ ጉዳይ ያማክረኛል። ሁሉም የተትረፈረፈ ሃብት አላቸው። የአባታቸው ውርስ ደግሞ የእነርሱን ይበልጣል። ሕጋዊውን መንገድ ከተጨዋወትን በኋላ መላ ቤተሰቡ ተማምነው ለታላቅ ወንድማቸው ውክልና ይሰጡትና ንብረቱ በየድርሻቸው በታላቅ ወንድማቸው እጅ እንዲተዳደር ይደረጋል። በሰላም ነገሩ ተቋጨ። ነገሩ ከተጠናቀቀ ከሦስት ወር በኋላ ግን የቤቱ አራተኛው ልጅ (ከሌሎቹ ይልቅ እጅግ ብዙ ሃብትና ተሰሚነት አለው) እኔው ያለሁበት ድረስ ይመጣል። ለካ፥ ከመካከላቸው አምስተኛው ልጅ ከአራተኛው ታላቅ ወንድሙ ጋር ተጋጭቶ በጠብ ይፈልገዋል።

   እጅግ አዝኖ መቸገሩንና የተላከለት ነገር ሚስቱን ይበልጥ እንዳስጨነቀው አጫወተኝ። ጠየቅሁት፥ አወራኝ። ሰምቼ ማመን አቃተኝ። ደብዳቤውን አሳየኝ አልኩት። ከነተላከበት ፖስታ አውጥቶ ሰጠኝ ፤ አንብበው ብሎ፤ አነበብኩት። እጅግ አዘንኩ። ከንግግሩ ሊሆን የሚችለው ከጠንቋይ እንደሆነ ባስብም ደብዳቤው የተላከው ከአንድ “ታዋቂ” ገዳም የተጻፈና በግርጌ በራስጌ ማኅተም አጊጦ፤ በገዳሙ አስተዳዳሪ ፊርማ ተውቦ፤ እርሱና ሚስቱ በተባለው ቀን ባይመጡ  “እንደሚጸለይባቸው” ደብዳቤው በማስጠንቀቂያ ይናገራል። (ደብዳቤውን ማውጣት ወንድሜ ላይ ጥቃት እንዳያደርሱበት ስለሠጋሁ አላደረግሁትም)
   ባለሁበት ሆኜ ብዙ አሰላሰልኩ፤ በተለይም “ይጸለይባችኋል” የሚለው ቃል አልዋጥልህ እያለኝ ደጋግሜ አየሁት። ግን ባፈጥም ምንም ለውጥ የለውም፤ ያው ቃል መልሶ ያፈጥብኛል። “ይጸለይባችኋል”። ለምን እንዲህ እንደ ተጻፈ ደግሜ ማሰላሰል ጀመርኩ፤ እንዲህ እያስፈራሩ ባርያ ለማድረግ ነውን? እንዲህ ከማለት የሚያገኙት ትርፍ ምንድር ነው? ደግሞስ ከማን ተማሩት? ጠንቋይ ከዚህ የተሻለ ምን ሥራ ይሠራል?
    ጌታ ኢየሱስ፥ “ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት” (ኤፌ. 5፥26) ተብሎ እንደ ተነገረለት ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞ ነፍሱን ሳይሳሳ እስከ መስጠት ይወዳታል። በእርግጥም ስለትልቅ ፍቅሩ፦ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ. 15፥13) ተብሎለታል። እርሱ የአንድ ነፍስ ነገር እጅግ “ያባክነዋል”፤ ስለዚህም “አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የሚሄድ” ትሁት ጌታ አለን። (ሉቃ. 15፥4) በእርግጥም ትልቁ ደስታ የአንድ ኃጢአተኛ ወደ እግዚአብሔር መግባት ወይም ከኃጢአቱ መመለስ ነው።
    ለእያንዳንዱ አማኝ የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ያለምንም ልዩነት እኩል ነው። ለሁሉም እኩል ዋጋን ስለከፈለም ጥሪውና መሻቱ፥ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራእ. 3፥20) የሚል ነው። ማንም ለክርስቶስ የእንግድነት ልቡን ከከፈተና ሊቀበለው ከወደደ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር እራትን ይበላል ፤ አብሮም ሕብረትን ያደርጋል። “ማንም” የሚለው ቃል  የትኛውንም ሰው የሚወክል ነውና።
   ቤተ ክርስቲያን ከመሪዋ መንፈስ ቅዱስም ሆነ፥ ከሞተላት በትንሣኤው ካከበራት ኢየሱስ የተማረችው አንድን ነፍስ ለማዳን ማድረግ ያለባትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባት ነው። በታላቁ ተልእኮም የተነገራት ነገር ቢኖር፥ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” (ማቴ.28፥19) የሚል ነው። የዚህ ታላቅ ተልእኮ የመጨረሻው ግብ፥ “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌ. 1፥10)
    ለዚህ ሥራ ቤተ ክርስቲያን ለአህዛብ ሁሉ ያለአንዳች አድሎ ወንጌልን ልትመሰክርላቸው ፤ ለመሰከረችላቸውም ደግሞ የክብሩ ወንጌል ብርሃን በልባቸው እንዲያበራ በመራራት ልትጸልይላቸው ይገባል። ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ብቻ ሳይሆን አህዛብ ሁሉ እንዲድኑ በምልጃ ጸሎት ልትተጋላቸው ይገባል። ከዚህ በዘዘለ ግን በልጆቿ መካከል ክርክርና አለመግባባት (በተለይም በንብረት ጉዳይ) ሲፈጠር ቤተ ክርስቲያን ጠንቃቃና እጅግ አስተዋይ በመሆን ሁለቱንም ወገኖች እኩል በመስማት ያለአድልዎ ልትፈርድ ይገባታል።
    አንድ ወገንን በማድመጥ ብቻ ግን ለመንፈሳዊ ሥራ ዋና መዋጊያዋ የሆነውን የጸሎት ኃይል ለክፋት ብትጠቀመው ከባድ ወቀሳን እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ትቀበልበታለች (1ቆሮ. 6፥1-5)። አስቡት እስኪ! ለአንድ ቤተሰብ “ይጸለይባችኋል” የሚለው ቃል ምንኛ ከባድና እጅግ አስፈሪ እንደሆነ?! በውኑ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ልትል ይገባታልን? ደግሞስ አንድን ወገን ብቻ ሰምቶ ፍርድ ከወዴት መጣ? ይጸለይባችኋል ከማለት በፊት፥ “ኑ ልጆቼ እስኪ ልምከራችሁ” ማለቱ አይቀድምምን? በተለይ አንድ ወገን ሰምቶ መፍረድ በአብያ ክርስቲያናት አከባቢ እጅግ እየበዛ ነውና፥ ሥር ሰዶ ሥርዓት ሳይሆን ቀድመን ብናስብበት፤ ርዕስ አድርገን ብንወያይበትና ብዙ መንፈሳዊ ነገራችንን ስለሚያረክስብን ነቅለን ብናወጣው እጅግ መልካም ነው።
     ከ“ይጸለይባችኋል” አስነዋሪ ቃል ይልቅ፥ “ኑ እንጸልይላችኋለን” ማለትን ብናዘወትር ፤ ብንለምድም እጅግ መልካም ነው። ያ እንኳ ባይሆን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን “ጦመውም ከጸለዩ በኋላ፥ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው።” (ሐዋ. 14፥23) እንደ ተባለ አደራ መስጠት ወይም ለአቅራቢያው አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እንዲያስታርቋቸው ማድረግ በተገባ ነበር። ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የአንድ ወገንን ቅሬታ ብቻ በመስማት ለአስተያየትም ሆነ ለተግሳጽ ከመቸኮል ሌላውንም ወገን እኩል መስማት እጅግ ተገቢ ነው። የገዳሙ አስተዳዳሪ ወደ ሌላ ቦታ በሥራ ዝውውር ሲሄዱ እንዲህ ያለውን ክፉ ጠንቋያዊ ልማድ እንዳያዛምቱ በቅንነት ሊታሰብበት ይገባል።
(ይህ ጽሁፍ ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት ተጽፎ የነበረ ነው)


2 comments:

  1. ከዛስ! ምን ይጠበስ ; ይህ ሁሉ የቅናት መንፈስ ይመስለኛል ፡፡

    ReplyDelete