Wednesday 29 November 2017

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፬


ሰው መንፈስ ነውን?

   ሰው ሥጋና ነፍስ ወይም ሥጋና መንፈስ ነው፤ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የብልጥግና ወንጌል[1] መምህራን፣ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል፡፡”[2] በሚለው ፍጹም ክህደት ደምድመውታል፡፡ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርታቸውን የሚያስተምሩበት ዓላማቸው ኋላ ላይ አግተልትለው ከሚያመጡት “ፈጣጣ ክህደት” አንጻር እንጂ ወዲያው አይገባንም፡፡ በአጭሩ “ሰው መንፈስ ነው” የሚሉበት ዋና ዓላማቸው ሥጋ ለባሹን ሰው፣ “እግዚአብሔር ለማድረግ” ከሚባዝን ከንቱ ምናባዊ ቅዠት የተነሣ ነው፡፡ ይህንን በድፍረት ኢትዮጲያዊው የቃል እምነት መምህሩ ኃይሉ ዮሐንስ እንዲህ ይላል፦
   “ … አዎ ልክ እንደእግዚአብሔር ነን[ኝ] በሚለው እስማማለሁ፤ ምን ማለት ነው ይህ? መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች አሉኝ፤ በመጀመርያም የምሄደው ዘፍ.1፥26-28 ያለውን በመጥቀስ ነው፤ … ያ መልክና አምሳል ሙሉ ለሙሉ እግዚአብሔርን እንድንመስል ያደርገናል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡ ግን “detail” መሄድ ቢያስፈልግ ጌታችን ኢየሱስ ስለራሱ የተናገራቸው ነገሮች ትዝ ይሉኛል፤ በዮሐ.14፥8 ላይ … “እኔና አብ አንድ ነን” ያለበት ሃሳብ በእኔ አመለካከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ማለት ደግሞ ሰው ነው፤ በእኔ አመለካከት የሌላውን ሰው አመለካከት ልጋፋው አልችልም፡፡ ጌታ ኢየሱስ “እኔና አብ አንድ ነን” ካለ፣ ታላቅ ወንድማችን እንደዛ ካለ፣ እኛ ደግሞ ከአባታችን ጋር አንድነታችንን መናገር እንችላለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው እኛም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፡፡

    … የእግዚአብሔር ልጅና የእግዚአብሔር ልጆች ሶርሳቸው[ምንጫቸው] አንድ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ሮሜ.8፥28-29 ስናነብ፣ “የልጁን መልክ እንዲመስሉ እግዚአብሔር ወስኗል” ነው የሚለው፡፡ የተወሰነ ነገር ነው፡፡ የልጁን መልክ … በግማሽ አይደለም፣ 99% አይደለም፣ ሙሉ በሙሉ የልጁን መልክ እንድንመስል የወሰነው ራሱ እግዚአብሔር ከኾነ፣ ልጁ ማንን ይመስላል ብንል፣ ልጁ አባቱን ይመስላል፤ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አባቱን የሚመስል ከኾነ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የእኛም አባት ከኾነ አባታችንን እንደምንመስል ምንም ጥያቄ የለኝም፡፡ አንድ ሰው በዘፍ.1፥26 መሠረት እግዚአብሔርን እመስላለሁ ቢል ትክክል ብዬ ነው ማስበው፤ ለምን? የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋይ የሚለው ሃሳብ የተወሰነ መካፈላችንን ሳይኾን ሙሉ በሙሉ በመወለድ ከተላለፈ፣ ተወልደናል ብለን የምናስብ ከኾነ፣ የማደጎ ልጆች ካልኾንን፣ ከተወለድን የተወሰነ ባሕርይ Omit[አጉድዬ] አድርጌያለሁ አልልም፤ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሙሉ ለሙሉ ተካፍያለሁ ብዬ ነው የማምነው፤ … እግዚአብሔርን እንድመስል የሚያደርገኝ ዝርያ አለኝ ብዬ አምናለሁ፤ ከዚህ ዝርያ ቀረ ብዬ የማምነውም ነገር የለም፤ መወለድ የሚባለው ነገር እውነት ከኾነ … ያልተላለፈብን ባሕርይ የለም፤ …
    ምሳሌ ቢኾንም በሉቃ.15 ላይ ጠቅሶ የተናገረውን ስንመለከት ቤት የነበረውን ልጅ ምን አለው? ልጄ ሆይ የእኔ የኾነው ሁሉ ያንተ ነው፤ … የእግዚአብሔርን ባሕርይ አንዷንም ሚስ ሳናደርግ ሰው ከኾንን፤ ሰው መኾን ከቻልን አለን ብዬ አስባለሁ፤ የእኔ የኾነው ሁሉ ያንተ ነው በሚለው ቃል መሠረት የእግዚአብሔር አባቴ የኾነው ሁሉ የእኔ ንብረት ነው፡፡ … የሚታይና የማይታይ የአባቴ የኾነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እግዚአብሔር ያለው ሁሉ የእኔ ነው ከማለት ራሱ እግዚአብሔር የእኔ ነው፤[3]
      የኃይሉ ዮሐንስና የባልንጀሮቹ መምህራን ደግሞ እንዲህ ይላሉ፦
   “እግዚአብሔር አዳምን በሠራው ጊዜ እንዲህ አለው፦ አንተ የእኔ ዲኤንኤ አለህ፤ የወጣኸው ከእኔ ነውና፤ …” (ቲ.ዲ.ጄክስ)
   “መጽሐፍ ቅዱስን በማነብበት ጊዜ ኢየሱስ “እኔ ነኝ” በሚልባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ፈገግ ብዬ “አዎን፤ እኔም ነኝ እላለሁም” ብዬ እመልሳለሁ”(ኬኔት ኮፕላንድ)
    “ሁሉም የሚወልደው የራሱን ዓይነት ነው፤ የፈረስ ልጅ ፈረስ ነው፤ የድመት ልጅ ድመት ነው፤ … ከእግዚአብሔርም የተወለደ ሁሉ የእግዚአብሔር ዓይነት ነው፤…” (ጆይስ ሜየር)
     
    በእነዚህ የስህተት ትምህርቶች ውስጥ ብዙ የተሰገሰጉ ርምጥምጥ ሃሳቦች አሉ፡፡ መፈጠርና መወለድ በአንድ ላይ ተሰፍተዋል፤ እግዚአብሔርነት ወደሰውነት “ወርዷል” ወይም ሰውነት ወደእግዚአብሔርነት “አድጓል”፤ ከምንም በላይ በሚያሳፍር መልኩ ፈጣሪነት ከሰውነት ተራ ተመድቧል፤ የእግዚአብሔር ባሕርይ ይህ ነውን? እስክንል ድረስ ስህተቱ ደምቋል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከዓውዳቸው ተቦጭቀው ወጥተው፤ በማስጨነቅ እጃቸው ተጠምዝዞ ሲተረጎሙ፣ ከዓውድ ውጭ ወጥተው ሲነበቡና ሲፈከሩ ታይተዋል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የሌሉና ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳና ልዩ የኾኑ ትምህርቶች፣ ጠቅላላው የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማና ሃሳብ የማያንጸባርቁ፣ ይልቁን ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱና የሚቃረኑ፣ ምሳሌያዊ ትምህርቶች ለዶግማ መመስረቻ ሲጠቀሱና ሌሎችንም ግልጥ ስህተቶችን እናስተውላለን፡፡
የቃሉ እውነት ቁጥር ፩
“ሰው መንፈስ ሳይኾን ዘወትር ሰው፤ ሰው ነው፤ እግዚአብሔርም እግዚአብሔር ነው!”
   የቃል እምነት መምህራን ስህተታቸው የሚጀምረው፣ በዘፍ.1፥26-27 እና 2፥7 ላይ ሲያብራሩ ሁለት የተለያዩ የፍጥረታት ጊዜ[4] እንዳሉ መናገር ከመጀመራቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ትምህርታቸውን ስንጨምቀው፣ “እግዚአብሔር አስቀድሞ አካል የሌላት ነፍስን[መንፈስን] ፈጠረ፤ ከዚያም ቀጥሎ ሥጋን ፈጠረ፤ የፈጠረውንም ነፍስ[መንፈስ] ባበጀው ወይም በፈጠረው ሥጋ ውስጥ አኖረው፤ ስለዚህም ሰው መንፈስ ነው፤ በጊዜያዊነት በሰው ሥጋ ውስጥ ያድራል” የሚል ነው፡፡
    ነገር ግን ይህ የቃል እምነት እንቅስቃሴ መምህራን፣ “ሰው መንፈስ ነው፤ ደግሞም መንፈስ በመኾኑም ልክ እንደእግዚአብሔር ዓይነት ነው፤” የሚለው ትምህርታቸው መመለስ የማይችላቸው ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ጥቂቶቹን ጥያቄዎች ብናቀርብ፦
1.      ሰው መንፈስ ከኾነ በዘፍ.1፥27 ላይ ጾታዊው ምደባ ለነፍስ ወይስ ለሥጋ ተደርጎ ይኾን? መንፈስም[ነፍስም] ጾታዊ ምደባ[ወንድና ሴት] አለው ማለት ነው?
2.     ለመኾኑ እግዚአብሔር ፍጥረትን ፈጥሮ የጨረሰው በስድስቱ ቀናት አይደለምን? ስድስተኛው ቀንስ፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን፤” (ዘፍጥ.1፥31)፣ እንዲሁም “ሰማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ” (ዘፍጥ.2፥1) እንደተባለ፣ ፍጥረት በስድስተኛው ቀን መጠናቀቁን ይነግረናል፤ እንኪያስ እነርሱ እንደሚሉት ዘፍጥ.2፥7 ላይ የተጠቀሰው ሃሳብ የስንተኛ ቀን ፍጥረት ይኾን? በዘፍጥ2፥7 ላይ ያለው የዘፍ.1፥26-28 ማብራሪያ ነው ወይስ ከስድስቱ ቀን ውጭ የተፈጠረ ፍጥረት?
3.     ደግሞስ ዘፍ.2፥7 የዘፍ.1፥26 ቅጣይ ፍጥረት ከኾነ፣ በዘፍ.5፥3 ላይ የተጠቀሰውስ ሰው ለስንተኛ ጊዜ መፈጠሩን ሊነግረን ይኾን?
4.     ዘፍ.1፥26 ላይ ያለው “ሰው መንፈስ እንጂ ሥጋ የለውም” ለማለት ምክንያታችን ምንድር ነው? ዓውዱ ይላልን? ሌላስ የሚደግፈን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይኖር ይኾንን?
5.     ሰውን መንፈስ ነው ካልን፣ ሰውና መንፈስ አንድ ናቸው ወይስ የተለያዩ? ከንግግራቸው እንደምንረዳው የተለያዩ ናቸውና ከሰውና ከመንፈስ ማንኛቸው ይበልጣሉ? ወይስ ተካካይ ናቸው?
6.    ደግሞስ ነፍስ የማንኛቸው ክፍል ናት? የሰው ወይስ የመንፈስ? ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው ካልን፣ ነፍስ ያለው ማን ነው? ሰውየው ነው ወይስ መንፈሱ? ወይስ ነፍስ ያለው ሰው?
7.     ከማንነት ጋር በተያያዘ የመኖር እውነታ ጥናትን (Ontologically) ታሳቢ አድርገን ሰውና እግዚአብሔርን ብናስተያይ፣ ሰው እግዚአብሔርን መኾን ይቻለዋልን? እግዚአብሔርስ ወደሰውነት ይወርዳልን?
8.     በሥጋ ውስጥስ የሚያድረው ማነው? በሥጋ ውስጥ የሚያድረው መንፈሱ ነው ወይስ ሰውየው? በሥጋ ውስጥ የሚያድር መንፈስ ከኾነ ሥጋው ቀፎ ብቻ ነው ማለት ነው? ቀፎ ከኾነ ምንም አይነት ግልጋሎት የለውም ማለት ነው?
9.    ሰው አምላክ የሚኾነው መንፈስ ኾኖ በመፈጠሩ ወይስ ከእግዚአብሔር በመወለዱ ምክንያት ነው? ለቃል እምነት እንቅስቃሴ መምህራኑ መንፈስ ኾኖ መፈጠርና ከእግዚአብሔር መወለድ ውጤታቸው አንድ ነውን?
10.   የእግዚአብሔር መልክ ማለት መንፈስነት ከኾነ፣ መንፈስ ደግሞ እግዚአብሔር ከኾነ እኛም መንፈስ ስለኾንን እግዚአብሔር ልንኾን ነው ማለት ነው? ... እና ሌሎችም ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን፡፡ ለእነዚህና ለሌሎችም ጥያቄዎች መልስ እንደማይኖራቸው እጅጉን የተገለጠ ነው፡፡
      ከዚህ በታች የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌን ከሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች[ዘፍ.1፥26-28 እና 2፥7] አንጻር በትክክል ለእግዚአብሔር ቃል ሃሳብ በማድላት እናብራራለን፦
እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” የማለቱ ነገር፤ (ዘፍ.1፥26-31)
    ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እግዚአብሔር ሰውን ሕይወት ካለው እንሰሳ “ይሁን!፤ ይሁን!” በማለት አለመፍጠሩን ይነግረናል፡፡ ይልቁን አክብሮና ወድዶ በልዩ ክብር በእጆቹ ማበጀቱን፣ ይህንም በመልኩ እንደ ምሳሌው መፍጠሩን እናያለን፡፡ እግዚአብሔር የእርሱን ተሻጋሪ ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ከአፈጣጠራችን ጀምሮ ባለው ፈቃዱ ገልጦታል፡፡ በዚህም ሰው ከእንሰሳ ፈጽሞ የተለየ መኾኑን እናስተውላለን፡፡ ቃሉን በትክክል ለመረዳትም ቀደምት ተደራስያኑ[አይሁድ] ምን እንደተረዱ ማስተዋል ይገባል፡፡ ቀደምት ተደራስያኑ ከተረዱት ነገር ውጪ እኛ ዛሬ አዲስና ልዩ የምንረዳው ነገር አይኖረንም፡፡
   “መልክ” የሚለው ቃል በዕብራይስጡ፣ “ጼሌም” የተባለው ነው፤ ትርጉሙ ሥዕልን ወይም ምስያን አመልካች ነው፡፡ ቃሉ ጣዖታትን ለመግለጥና ለሌሎችም መገለጫዎች በተለያየ የብሉይ ኪዳን ምንባባት ውስጥ ውሏል፡፡ ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥቅሶች መመልከት ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፤ (ዘፍጥ.1፥26 ፤ 27 ፤ 5፥3 ፤ 9፥6 ፤ ዘኊል.33፥52 ፤ 1ሳሙ.6፥5 ፤ 11 ፤ 2ነገ.11፥18 ፤ መዝ.39፥6፡፡)[5] “ቃሉ በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ በሦስት መንገድ ይነገራል፡፡ (1) ዓይነት፣ ሁኔታ፣ አቋም፣ ቅርጽ፤ (2ሳሙ.14፥20፤ ኢሳ.52፥14፤ 53፥2፤ ዳን.2፥31፤ ማቴ.22፥20፤ (2) እንደጥላ የሌላውን ምሳሌ መያዝ፡፡ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ፤ (ዘፍጥ.1፥26)፡፡ ምእመናን የክርስቶስን መልክ ሊመስሉ ይገባቸዋል፤ ሮሜ.8፥29፤ 2ቆሮ.3፥18፡፡ የአምልኮት መልክ ሲል ሥርዓት ማለት ነው፤ (2ጢሞ.3፥5)፤ (3) እውነተኛ ምሳሌ፡፡ ክርስቶስ በእግዚአብሔር መልክ ሆኖ በሰው መልክ ተገለጠ፤ ፊል.2፥6-7)፡፡”[6] የቃሉን አገባብ በጠቅላላው ስንመለከተው ጣዖታትን በተመለከተ ቅርጻዊ ምሳሌን እንጂ ባሕርያዊ ወይም አካላዊ ወይም ሥነ ምግባራዊ ምስስልን ፈጽሞ አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም ምስያዎቹ ሕይወት አልባ ሲኾኑ፣ ተመሳዮቹ ደግሞ ሥጋና ደምን የያዙ ናቸውና፡፡
    በሌላ ምልከታ ደግሞ፣ በነገረ ሥጋዌ ትምህርት በመለኮታዊ ልዩ ዕቅድና ስለሰው ልጆች መዳን ሲባል፣ ክርስቶስ አምላክ ሳለ፣ ሰውነትን የጨመረበትን ሁኔታ ስንመለከት፣ ምስያችንን ሳይሆን በትክክል እኛን መምሰሉን እናስተውላለን፡፡ ይህ ግን በልዩትነት የሰውን ልጅ ስለማዳን የተደረገ መለኮታዊ እቅድ እንጂ ከሰው መፈጠር ጋር ተመሳሳይ ብለን መውሰድ የሚቻለን አይደለም፡፡ በፍጥረት ሂደት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል መመሳሰል አለ፤ ይህ ማለት ግን ሰው ልክ እንደእግዚአብሔር ወይም የእግዚአብሔር ዓይነት ነው ማለት አይደለም፡፡
   “አምሳል” የሚለው ቃል በዕብራይስጡ፣ “ዴሙት ወይም ዳማት”[7] ሲኾን፤ ቃሉ ከ25 ላላነሰ ጊዜ በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ውሏል፡፡[8] ትርጉሙም አርዓያ፣ እንደ[በንጽጽር የሚቀርብን] ብለን መተርጎም እንችላለን፡፡ “ሰው በእግዚአብሔር አርዓያ ተፈጠረ ስንል፣ ለምሳሌ፦ እግዚአብሔር መንፈስ ነውና አምሳሉ በሰው ላይ ሊታይ የሚችለው በነፍሱ በኩል እንጂ በሥጋው አይደለም፡፡ እውነት ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ዐይን፣ ጆሮ፣ እጅ … ወዘተ አለው ይላል፡፡ ሆኖም እነዚህ ቃላት በሰው አገላለጥ የእግዚአብሔርን ሥራዎች እንጂ ባሕርዩን አይገልጡም፡፡”[9] በጠቀስናቸው ጥቅሶችም ውስጥ ፍጹም የሆነ የባሕርይ ተዛምዶን ወይም አንድ አይነትን የሚያመለክቱ አይደሉም፡፡ በንጽጽር እንደመቅረባቸው መመሳሰል እንጂ ምንም አይነት ልዩነት የሌላቸው መሆናቸውን አያሳይም፡፡ አለቃ መሠረት ይህን እንዲህ ያብራሩታል፦
    “ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረ ማለት ምን ማለት ነው? አዎን፥ መልክና ምሳሌ፥ የስብእና ዓይነት እንደምን እንደሆነ የሚገልጽ አባባል አላቸውና ስለዓይነቱ ስብእና ህላዌ መጠየቅናመረዳት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡
      የስብእና አቋም ምንድን ነው? ቢሉ፣ በቀላሉ ለመግለጽ ያህል፥ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ እንዲፈጠር ተፈቅዶ መፈጠሩና፣ በዚሁ በተፈጠረበት አቋም እንዲኖር ተፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ዘፍጥ.1፥27፡፡ ም.2፥7፡፡
    ይህም እግዚአብሔር ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፣ ሰውም የሕይወት መንፈስ ያለበት ሆነ፡፡ ተብሎ እንደተገለጸ፣ በሰው አፍንጫ ላይ እግዚአብሔር እፍ ያለበት የእግዚአብሔር እስትንፋስ፥ ሰውን የሕይወት መንፈስ ያለበት እንዲሆን አበቃው፡፡ ዘፍጥ.2፥7፡፡ ኢዮብ 26፥3፤ 4፡፡ ኤፌ.4፥24፡፡
    ይህ መጀመርያ ከእግዚአብሔር ለሰው እፍ የተባለበት የእግዚአብሔር እስትንፋስ፣ እንዲሁም ደግሞ ለሰው ሕያው መንፈስ ያለበት መሆኑን የገለጸ ህላዌ፥ “ነፍስ ወይም መንፈስ” ተብሎ ተጠራ፡፡ እንግዲህ ህላዌ ስብእና የተሰኘው ይኸው ነው፡፡ ዘካ.12፥1፡፡
     ይህ የህላዌ ስብእና ሐዋርያው ጳውሎስ በሚፈጥረው ምሳሌ፣ የሆነ“የጽድቅና የቅድስና መልክ” ብሎ በማብራራት ሲገልጸው ይገኛል፡፡ ኤፌ.4፥23፣ 24፡፡ መመሳሰሉ እንደምንድን ነው? ቢሉ፦
1፥ በኩነት መመሳሰል፦
    ይኸውም በለባዊነት በነባቢነት በሕያውነት መመሳሰል ነው፡፡ ይህ ኩነት ባልተፈጠረ ዘለዓለማዊ በሆነ በእግዚአብሔር እንዳለ ሁሉ፣ በተፈጠረ በሰው መንፈስም እንዲገኝ ተደርጎአል፡፡
2፥ በጽድቅ በቅድስና መመሳሰል፦
    እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ፥ የሰው መንፈስም በጽድቅና በቅድስና እንዲኖር በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ታስቦ ተፈጥሮአል፡፡
3፥ በዕውቀትና በክሂል በሥልጣን መመሳሰል፦
   በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዕውቀትና ክሂል፥ ሥልጣን፥ ማመዛዘንና ወዘተ … እንዳለ ሁሉ፥ በሰውም መንፈስ ውስጥ ክፉንና ደግን፥ ጽድቅንና ኃጢአትን፥ እውነትንና ውሸትን፥ ቅድስናን፥ ርኩሰትን፥ ለይቶ ማወቅ፣ ይህንን ለይቶ እንደማወቁ መጠን፥ ተገቢውን የመምረጥና የመፈጸም ሥልጣንና ክሂል፥ አመዛዝኖ የመፍረድም ክሂል እንዲኖርበት ተፈጥሮበታል፡፡
4፥ በህልውና መመሳሰል፦
     እግዚአብሔር ልቡና ቃል እስትንፋስ ሲኖሩት ልቡ ያ ቃሉና ያለ እስትንፋስ፥ ቃሉም ያለ ልቡና እስትንፋስ፥ እስትንፋስም ያለ ልቡና ቃሉ ህልውናውን እንዳልገለጸ ሁሉ፣ መዝ.32/33/፥6 ሰውም ልቡ ያለ ቃሉና እስትንፋሱ፣ ቃሉም ያለ ልቡና እስትንፋሱ፣ እስትንፋሱም ያለ ልቡና ያለ ቃሉ አይገኝምና በእነዚህ በተዘረዘሩት ሁሉ ሰው እግዚአብሔርን ይመስለዋል ተባለ፡፡ ኢዮብ.28፥36፡፡ ም.10፥12፡፡ መዝ.138/139/፥5፣ 14፡፡ ሉቃ.10፥27፡፡ የሐዋ.13፥22፡፡ ምሳ.4፥23፡፡”[10]
    ቅዱሳት መጻሕፍትንም ስናጠና በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸው መኾናቸውን እናስተውላለን፡፡[11] ጠቅላላ የክፍሉ ዓውድ ሰው ከእግዚአብሔር እንጂ ሰው ራሱ እግዚአብሔር አለመኾኑን፣ የሰው ምንጭና መገኛ ራሱ እግዚአብሔር እንጂ ሰው በራሱ ቅድመ ኑባሬ የሌለው መኾኑን፣ ሰው በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተፈጠረ እንጂ ራሱ ፈጣሪ አለመኾኑን ይናገራል፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥር ሰውን ምንም “በልዩ መልክ” የተፈጠረ ቢኾንም፣ የእግዚአብሔር ፍጥረት አካልና እንደሌሎቹ ፍጥረታት በየወገኑ ሳይኾን ወንድና ሴት ኾኖ መፈጠሩን፣ ሰው ለእግዚአብሔር ክብር በእግዚአብሔር መፈጠሩን … ክፍሉ በሚገባ ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን “መልክና አምሳል” የሚሉት ቃላት “ሰው መንፈስ ነው” በሚሉ ወገኖች ዘንድ ለክርክር አጋልጠው ሲያቀርቡ እናያለን፡፡
   ስለዚህም መልክና አምሳል የሚሉትን ቃለት ስንመለከት ምንም እንኳ በዘፍ.1፥26 ላይ በአንድነት የተጠቀሱ ቢኾኑም ሁለቱም ቃላት ምንም የፍቺ ልዩነት እንደሌላቸው በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችና በተደራስያኑ ዘንድ እንዳለ ይታመናል፡፡ ይህንንም ቄስ ኮሊን ማንሰል እንዲህ ብለዋል፦
     በምዕራፍ 1፥26 ሁለቱም በአንድነት ይገኛሉ፤ በ5፥1 “ምሳሌ” ብቻ ሲገኝ፥ በ9፥6 “መልክ” ብቻ ተጽፏል፡፡ በምዕራፍ  1፥26 “በመልካችን እንደ ምሳሌአችን” ሲል የመስተዋድድ ልዩነት ይታያል፡፡ በ5፥1 እና በ9፥6 ግን “በእግዚአብሔር ምሳሌ” እና “በእግዚአብሔር መልክ” ቢልም የአሳብ ልዩነት ያለ አይመስልም፡፡ ደግሞም አዳም ልጅንም “በምሳሌው እንደመልኩ” ወለደ ስለሚል የመስተዋድዶች አጠቃቀም ስለተለዋወጠ፥ መለዋወጡ በእነዚህ ጥቅሶች ልዩ አሳብን ያመለክታል ብሎ ለማስተማር ምክንያት ያለ አይመስልም፤ ዘፍ.5፥3፡፡ ዛሬ የብሉይ ኪዳን ኪዳን ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት አጠቃቀም ላይ የሁለቱ ቃላት አሳብ አንድ መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ይህ ትክክለኛ ከሆነ፥ ጸሐፊው በሁለት ተመሳሳይ ቃላት የተጠቀመበት ምክንያት አጽንዖት ለመስጠት ነው፡፡”[12]
     “እንፍጠር”፣ የሚለው ቃልም እግዚአብሔር ከመፍጠሩ በፊት ሰውን ለመፍጠር ልዩ ምክር እንዳለው ያሳያል፡፡ ሰው በመልኩና በአምሳሉ በመፈጠሩም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አንድነትና ልዩነት መኖሩ እንጂ ፍጹም አንድነት አለመኖሩ ግልጥ ነው፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት የእግዚአብሔርን በረከት ተቀባይ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ “ተገንዛቢ”ና የፈቃዱ ፈጻሚ መኾኑን እናያለን፡፡ እናም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ተፈጠረ፡፡ የመጀመርያው የዚህ ቃል ተቀባዮች[ተደራስያን] “መልክና አምሳል” የሚሉትን ቃላት የተረዱት፣ የእግዚአብሔርን ወኪል(Vicegerent) መኾንን እንጂ ሰው እግዚአብሔር[መንፈስ] መኾንን አልነበረም፡፡
    አረማውያን በነበሩት ወገኖች እንኳ እንዲህ ያለ ማስተዋል በጥቂቱ መኖሩን፣ “ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ፦ እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን፤” (ሐዋ.17፥28) በማለት የሁለት ባለቅኔዎችን ሃሳብ በማንሳት፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር መኾናቸውን በአቴና ለነበሩት ፈላስፎች ተናገረ፡፡[13] ብዙ ጸሐፍትም ይህን እውነት በማጽናት ጽፈውታል፡፡[14]
     እግዚአብሔር የሰውን ሁለንተና ፈጥሮ የጨረሰው በዘፍ.1፥26-28 ላይ ነው፡፡ ፍጥረትም ሁሉ ተፈጥሮ የተጠናቀቀው በምዕ.1 ላይ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ፡፡ ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ፥ ስድስተኛ ቀን፤” (1፥31)፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈጠረውም ቀን፣ “እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፦ ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤” የሚለውን ባርኮት የሰጠው ለሁለቱም[ለአዳምና ሔዋን] ነው፡፡ ስለዚህም ያልተጠናቀቀውን[ሥጋ የሌለውን መንፈስ የነበረውን ሰው ብቻ] በዚህ ባርኮት ባረከው ለማለት ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የለንም፡፡
     በክርስትና ነገረ መለኮት ፍጥረት ተፈጥሮ የተጠናቀቀው በስድስት ቀናት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለ፡፡ እግዚአብሔርም እያንዳንዱ ነገር በራሱ መልካም መኾኑን ብቻ ሳይኾን፣ ነገሮቹ ሁሉ በአንድነት ተገኝተው እርስ በርሳቸውም ተስማምተው፣ ያለግጭት መኖር እንደሚችሉና የእግዚአብሔርን ዕቅድ እንደሚፈጽሙ “ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” የሚለው ቃል ያጸናዋል፡፡ ስድስቱ ቀናትም በምዕ.1 ውስጥ ተካትተው የተቀመጡ ናቸው፡፡
    እግዚአብሔር አምላክ ሌሎችን ፍጥረታት በየወገናቸው መፍጠሩን እንጂ እንደሰው፣ “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ተብሎ አልተጻፈም፤ በዚህም ሰው በፍጥረት ክብሩ ከእንሰሳት በሚልቅ ክብር መፈጠሩን እናያለን፡፡ ወንድና ሴት ተደርገው የተፈጠሩትና ፍጥረታቸውም የተጠናቀቀው በዚሁ ክፍል ነው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ በምንም ዓይነት ሁኔታ ወንድና ሴት የሚል ጾታዊ ምደባ የለውምና፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰው የተፈጠረበትን የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል መጽሐፍ እንደሚለን፣ ጽድቅና ቅድስናን (ኤፌ.4፥24)፣ ዕውቀትን (ቈላ.3፥10) … ከማመልከቱ ባሻገር በራሳችን ሌላ ከዚህ ጋር የማይመሳሰል ትርጉም ብንሰጠው በቃሉ ላይ ጨምረናልና ሐሰተኞች ነን፤ (ምሳ.30፥6)፡፡ እግዚአብሔርን እንዲህ ባለ ነገር እንድንመስል ከተጠራን እጅግ ተወደናልና ደስ ይበለን፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …






    [1] የብልጥግና ወንጌል አማኞች ቢባሉ፣ ትኩረታቸው ምድራዊ ብልጥግና ላይ ስለኾነ፤ የቃል እምነት እንቅስቃሴ ስንል ደግሞ እምነታቸው ሁሉ የተደገፈው በሚናገሩት ቃላቸው ላይ ስለኾነና ሌሎችም ስያሜዎችን ከድርጊታቸውና ከሚያምኑት ነገር ጋር ተያያዥ መሆኑን እንጂ የተለያዩ እንዳልኾኑ አንባብያን እንዲያስተውሉ እወድዳለሁ፡፡
   [2] ይህች አባባል፣ ለቃል እምነት እንቅስቃሴ መምህራንና አማኞች “ውዳሴ ማርያማቸው¡¡¡” ሳትኾን አትቀርም፤ ሁሉም በትምህርቶቻቸው ሳያዛንፉ ደግመው ደጋግመው ይሏታልና፡፡ የእምነቱ ዋና አደራጅ የኾኑትም ኬኔት ሔጌንም እንዲህ ይላሉ፦ “Man is a Spirit who possesses a soul and lives in a body.” (Hagin,Kenneth E.; “Man on Three Dimension” Vol. 1 of the spirit, soul and body series 18th printing; Tulsa; Kenneth Hagin Ministries; 1994 pp.8
   [3] ኃይሉ ዮሐንስ ይህንንና ሌሎችንም ክህደቶች በEBS ቲቪ፣ በዩቲዩብ እና በሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ያለከልካይ ሲያስተምር አስተውለነዋል፡፡ በጋሻው ደሳለኝም የዚህ ትምህርት ተጋሪ መኾኑን በባለፈው ጽሁፎቻችን ተመልክተናል፡፡
   [4]  ይህ በነገረ መለኮት ትምህርት “Gap theory” ይባላል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በዘፍ.1 ላይ የሰውን መንፈስ ከፈጠረ በኋላ ብዙ ዘመናትን አሳልፎ የሰውን ሥጋ ዘፍ.2 ላይ ፈጠረ፤ ስለዚህም በዘፍ.1 እና 2 መካከል እጅግ የሰፋ ምናልባትም በሚሊየን ዓመታት የሚቆጠር ጊዜ አለ በማለት የሚያምን[የሚያስተምር] መላምት ነው፡፡ የቃል እምነት እንቅስቃሴ መምህራን ይህን መላምት ለትምህርታቸው በዋናነት ይጠቀሙታል፡፡
     [5] የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “መልክ” የሚለው ቃል፣ በብሉይ ኪዳን ለአሥራ ሰባት ጊዜያት ጥቅም ላይ መዋላቸውን ያብራራሉ፡፡ እኒህም ከላይ የተጠቀሱትና 2ዜና.2317 መዝ.7320 ሕዝ.720 1617 2314 አሞ.526 በአንድነት የሚካተቱ መኾናቸውንም ያስረዳሉ፡፡
   [6] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ.29
   [7] አዳም በዕብራይስጡ፣ ምድርን ወይም አዳማ በሚለው ትርጉሙ ቀይነትን አመልካች ነው፡፡ ከምድር አፈር ከመበጀቱ ጋር ይዛመዳል፡፡ ሰባ ሊቃናት “አንትሮፖስ” ብለው የተረጎሙት ይኸንኑ ቃል በመተርጎም ኾኖ ወንድንም ሴትንም በእኩልነት ለማመልከት ተጠቅመውት ነው፡፡
   [8] “… ጥቅም ላይ የዋለባቸው 25 ስፍራዎች የሚከተሉት ናቸው፤ ዘፍ.126 513 2ነገ.1610 2ዜና.43 መዝ. 584 ኢሳ.134 4018 ሕዝ.15101316222628 82 101102122 ዳን.1016”[ጳውሎስ ፈቃዱ፤ ደ´ሞ የእግዚአብሔር አቻ ሆንን!?፤ ያልታተመ ጽሁፍ፡፡
     [9] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ.148
      [10] መሠረት ስብሐት ለአብ(አለቃ)፤ ሥላሴ በተዋሕዶ፤ 1988 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ Mekane Yesus Seminary Theological Literature fund, (ገጽ.171-172)
     [11] “መልክና አምሳል” በሚሉት ቃላት ዙርያ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች የተለያየ ምልከታዎችን ይዘዋል፡፡ አንዳንዶች  ምናችን በትክክል እርሱን እንደሚመስል የተገለጠ አይደለም ይላሉ፡፡ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህንን ክፍል በተመለከተ፦ ኢርንየስና ተርቱሊያን መልክ የሰውን ሥጋዊ ገጽታ፣ አምሳል ደግሞ የሰው መንፈሳዊ ገጽታን፤ የአሌክሳንደሪያው ቀሌምንጦስ፣ ኦሪገን፣ አትናቴዎስ፣ አምብሮስ፣ አውግስጢኖስና የደማስቆው ዮሐንስ ደግሞ መልክ ሥጋዊ ያልኾነ የሰው ባሕርይ፣ አምሳል ሊያድግ የሚችል እንደቅድስናና ወይም ግብረ ገብ ያለ የሰው ገጽታ፤ ቶማስ አኲናስ መልክ የሰው ተፈጥሯዊ የማሰብ ችሎታ እና ነጻነት፣ አምሳል ዋነኛው ተፈጥሯዊ ጽድቅ እና ከተፈጥሮ በላይ የኾነ ሥጦታ፤ ይህም በውድቀት ጊዜ የጠፋ ሲሉ በኋለኛ ዘመን የመጡ ተሃድሷውያን ደግሞ ሁለቱም ቃላት ምንም ዓይነት የፍቺ ልዩነት የሌላቸው መኾኑን ይገልጣሉ፡፡ ስለዚህም ከዕውቀት ከፍሎ ማወቅን፣ ሥነ ምግባራዊነትን፣ የውክልና ሉዓለላዊነት(የንጉሥነት ወይም የገዢነት) ያለው መኾኑን ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይስማሙበታል፡፡
    ነገር ግን ሁሉም አባቶች ምልከታዎቻቸው “ሰው መንፈስ መኾኑንና ከእግዚአብሔር ጋር ተካካይ መኾኑን” በየትኛውም ጽሁፎቻቸው አልገለጡም፡፡ ሲገልጡም፦ ከሥነ ምግባር፣ ምንም እንኳ መልክና ምሳሌን በተለያየ መንገድ ቢተረጉሙም የሰውን ሰው-ነት ግን ፈጽሞ አልካዱም፤ አልሸራረፉትምም፡፡
   [12] ቄስ ኮሊን ማንሰል፤ ትምህርተ ክርስቶስ፤ ገጽ.21-22
   [13] “(1) “የምንኖረውና የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነው በእርሱ ነው” ይህን ያለው ኤፒዴኒዴስ(600 ዓ.ቅ.ክ) የተባለው የቀርጤስ ባለቅኔ ነበር፡፡(2) “እኛም ደግሞ ልጆቹ ነን” ይህን ደግሞ ያሉት የኪልቅያው ባለቅኔ አራጠስና (315-240 ዓ.ቅ.ል.) ቅሊንጦስ (331-233) ዓ.ቅ.ል) ነበሩ፡፡” [ዐ.መ.ት ገጽ.1681)
[14]  ዓሥራት ገብረ ማርያም፤ ትምህርተ መለኮት፤ 1983 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ.175፤ አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡ ገጽ.88

5 comments:

  1. Woow tigstih yigermal. wedaje metsaf metsafun endatresa. Tru biir aleh. Geta tigat yichemrlh.

    ReplyDelete
  2. ሰው በቃ ሰው ነው።ሰው መንፈስ አይደለም ወደ ፊትም መንፈስ አይሆንም። ለምን ይርመጠመጣሉ???

    ReplyDelete
  3. ሰዎቹ ኬት አመጡ? እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር መጀመሪያ የሰውን መንፈስ ፈጠረ የሚል አልተጻፈም። ይህ አስተምህሮት ሰው ከአፈር ሳይበጅም በፊት ዘላለማዊ ሆኖ ይኖር ነበር የሚል አንድምታ አለውና። ይህን እንዳስተውል ጽሑፍህ አግዞኛል ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ አቤን።

    ReplyDelete
  4. ተዋህዶ ስንት መስዋህት የተከፈለባት እግዚአብሔር የሚመስገንባት ቅድስት እምነት ናት ተዋህዶ ለዘላለም ትኑር ጌታ ሆይ ስይጣን ወጥመድ ጠብቀን እንዳሻው ብልባችን ገብቶ እምነታችንን ማህተባችንን እንዳያስክደን ጠብቀን ማስተዋልን ስጠን አሜን ባንተ ደካማው ጌታ የተዋህዶ አምላክ እየሰራ ነውናወንድሜ ማንቃትህ ጥሩነው

    ReplyDelete
  5. እግዚአብሔርን እንዲህ ባለ ነገር እንድንመስል ከተጠራን እጅግ ተወደናልና ደስ ይበለን፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፤ አሜን፡፡

    ReplyDelete