Thursday 16 November 2017

የብልጽግና ወንጌል፣ ከጌታችን ኢየሱስ ያልኾነ ልዩና እንግዳ ወንጌል - ክፍል ፪

ክፍል አንድ
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መለኰታዊ ማንነት መካድ፣ በእምነት እንቅስቃሴ መምህራን ዘንድ እጅግ የታወቀና እንግዳ ያልኾነ ነገር ነው፡፡ ምንም እንኳ በትምህርቶቻቸው መካከል በኢየሱስ ክርስቶስ “እንደሚያምኑ” ቢናገሩም፣ ነገር ግን እናምናለን የሚሉትን ሲያብራሩትና ሊያስተምሩት ሲነሡ ግን በትክክል ሲክዱት ይስተዋላል፡፡ በእርግጥም፣ የኑፋቄ መምህራንን ከምንለይበት መንገድ አንዱ፣ በደፈናው እናምናለን የሚሉትን የትኛውም ትምህርታቸውን፣ “እስኪ አብራሩት” ሲባሉ፣ ኑፋቄያቸው ወለል ብሎ ይታያል ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃርኖ ይቆማል፡፡
    ስለጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውም ትምህርት እንዲህ የሚል ነው፦
   “ኢየሱስ መለኮታዊ መኾኑን ያወቀውና ያገኘው በውስጡ መኖሩን ፈልጐ ካገኘ በኋላ ሲኾን፣ ይህንንም በማወቁና ፈልጎ በማግኘቱ እጅግ ታላቅ አስተዋይ ሰው ነው፤ … ራሱም በአንደበቱ፣ “የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር” (ዮሐ.14፥28) ብሏልና፣ ከአብ ያንሳል፡፡ ሰው ብቻ ኾኖ እንጂ አምላክ በመኾን ፈጽሞ አልመጣም፡፡ ደግሞም በማናቸውም ሥፍራ ራሱን “እኔ አምላክ ነኝ” ብሎ አልገለጠም፡፡”
በማለት ይናገራሉ፡፡ ይህ ትምህርታቸው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት በግልጥ የሚክድ ነው፡፡
     በዚህ ትምህርታቸው ውስጥ ክርስቶስን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስን በመቃረን ብዙ ኑፋቄያት ተሰግስገው እናያለን፡፡ በዋናነትም ብንጠቅስም፦

1.     ጽሐፍ ቅዱሳዊው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ኑባሬ በግልጥ ተክዶ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የክርስቶስን አምላክነት ባለመቀበል የተወገዙት ቀደምቶቹ አርዮሳውያን(Arianism) ናቸው፡፡ አርዮሳውያን “ከፍጥረት ኹሉ በፊት መጀመርያ የተፈጠረና ከአብ የሚያንስ ነው”[1] ብለው ያስተምራሉ፡፡ እናም መናፍቃን በየዘመናቱ መልካቸው ይቀያየር እንጂ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት በመካድ ተመሳሳይነታቸው ወደር የለውም፡፡ ከእነዚህም ዋነኞቹ በዘመናችን “የተነሡት” የእምነት እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡
    የጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ኑባሬን ቅዱሳት መጻሕፍት በምልዓትና በስፋት ይመሰክሩልናል፡፡ አንድ መዘንጋት የሌለብን እውነት ግን አለ፣ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበት ዋና ዓላማው አምላክነቱን ሊገልጥልን ሳይኾን፣ “የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” (ማቴ.20፥28 ፤ ማር.10፥45)፣ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና” (ሉቃ.19፥10) ብሎ እንደተናገረው የመምጣቱ ዋና ዓላማ ሰውን መፈለግና ማዳን ነው፡፡ ደግሞም አምላክነቱን በትምህርቱና በሥራዎቹ ኹሉ ገልጦ ሳለ፣ “አምላክ ነኝ አላለም” ብሎ ሙግት ማቅረብ ከድኩም አመክንዮ መመንጨቱን ማስተዋል አይከብድም፡፡
     ይህ ማለት ግን ማንነቱና ሥራዎቹ አምላክነቱን አያመለክቱም ማለት አይደለም፡፡ ይህንንም በዝርዝር እንደሚከተለው እንመለከታለን፤
1.1. ስለቅድመ ኑባሬው የክርስቶስ የራሱ ምስክርነት
1.1.1         ሱን ከአብ ጋር ማስተካከሉ[አንድ እንደኾነ መቁጠሩ]፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጥረት ከመፈጠሩ በፊት ከአብ ጋር በአንድነት ነበር፡፡ ይህንንም በገዛ አንደበቱ፣ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ.10፥30)፤ በማለት ሲናገር፣ አይሁድም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር ስለማስተካከሉ ምክንያት፣ “እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር” (ዮሐ.5፥18)ይለናል ቅዱስ ቃሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ራሱን ሲያስተካክል በእግዚአብሔር ዘንድ እንዳለና ራሱም እግዚአብሔር እንደኾነ ያሳይ ነበር፡፡
   ከእግዚአብሔር አብ ጋር በአካል ቢለያዩም፣ በባሕርይ አንድ መኾናቸውን መጽሐፍ ይመሰክራል፡፡ በሊቀ ካህናትነት ጸሎቱ፣ “አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐ.17፥5) ብሎ እንደጸለየው፣ ከአባቱ ጋር በአንድነት ነበር፤ በዘፍጥረት ምዕ.1፥1 ላይ “መጀመርያ” ከሚለው መጀመርያ በፊት፣ መጀመርያ በሌለው መጀመርያ ነበር፤ (ዮሐ.1፥1 ፤ ፊል.2፥6 ፤ 1ዮሐ.1፥2 ፤ ራእ.19፥13)፡፡
    “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ፤” (ዮሐ.8፥58) ብሎ እንደተናገረውም፣ በአምላካዊ የእግዚአብሔር ልጅነቱ አስቀድሞ የነበረ መኾኑን ተናግሯል፡፡ እንዲያውም አብ ከዘላለም ዘመናት በፊት እርሱን ይወደው እንደነበርም፣ “ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥” (ዮሐ.13፥3) የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡን መጽሐፍ ይመሰክርልናል፡፡
1.2. ነቢያቱ ምስክርነት፦ ቅዱሳን ነቢያት፣ ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ከመጀመርያውም አምላክ እንደኾነ መሰክረዋል፡፡ ኢየሱስ የፍጥረት አስገኚና ራሱም ሕያው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም በመለኮታዊ ክብሩ ከአባቱ ጋር እኩል ነው፡፡ ነቢያት ይህን እውነት በማስረገጥ፣ “አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም መኾኑን” (ሚክ.5፥2)፣ “ ... ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ ... ተብሎ መጠራቱን” (ኢሳ.9፥6)፣ “ከእኛ ጋር የኾነ እግዚአብሔር መኾኑን” (ኢሳ.7፥14)፣ በዕድሜ ከሚበልጠው አጥማቂው ዮሐንስ ቀድሞ የነበረ መኾኑን (ዮሐ.1፥30) ... በግልጥ መስክረውለታል፡፡
    በብሉይ ኪዳን በያሕዌ ስም የተነገሩት ትንቢቶች በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ተፈጽመዋል፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል፣ “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔር ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤” (ኢዩ.2፥32) የሚለው ትንቢቱ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ሽባውን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር፣ በጌታ ኢየሱስ ስም ከፈወሱ በኋላ ይህን ቃል በግልጥ ለጌታ ኢየሱስ በመጥቀስ ጽፏል፤ (ሐዋ.2፥21)፡፡
1.3.   ሐዋርያቱ ምስክርነት፦ ከሐዋርያት የጥቂቶቹን ምስክርነት ብንጠቅስ
1.3.1.      ዱስ ዮሐንስ፦  የክርስቶስን ቅድመ ኑባሬነት ለዘላለም ከአብ ጋር የነበረ መኾኑን ያለአንዳች ጥርጥር በግልጥ መስክሯል፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” (ዮሐ.1፥1) በማለት፡፡ እንዲሁም፣ ቅዱስ ዮሐንስ አምላካዊ የኾነውን እንከን አልባ የኢየሱስን ክብር፣ ሕይወትነቱን ማየቱንም መሰከረ፤ (ዮሐ.1፥14 ፤ 1ዮሐ.1፥1)፡፡
    “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው፤” (ዮሐ.1፥18)[2] በማለትም፣ አምላክ የኾነው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለአባቱ እውነተኛውንና ትክክለኛውን ነገር እንደነገረን ያስረግጥልናል፤ “ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፤” (ማቴ.11፥27) እንዲል እግዚአብሔር ስለኾነው አብ፣ በምልአትና በትክክል ሊነግረን የሚቻለው እግዚአብሔር የኾነው ወልድ ብቻ ነው፡፡
1.3.2.     ዱስ ጳውሎስ፦ ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክነትን ሳይተው፣ ሥጋን መጨመሩን፣ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥” በማለት ሲገልጠው፣ (ፊል.2፥6)፣ “ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን፡፡” (ሮሜ.9፥5) በማለትም አምላካዊ ማንነቱን ይመሰክርልናል፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስያስ መልእክቱ ላይ ደግሞ፣ የሐሰት ትምህርትን በመቃወም ትክክለኛውን የጌታ ትምህርት ሲያስትምር፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ምሳሌ፣ የሁሉ ፈጣሪ፣ ከሁሉ በፊት የነበረ፣ ሁሉም በእርሱ የተጋጠመ መኾኑን፣ “ … የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል” (ቈላ.1፥15–17) በማለት አስፍቶ ገልጦታል፡፡
     የዕብራዊያን ጸሐፊ[3]ም፣ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (ዕብ.1፥2) በማለት ክርስቶስ ሁሉን የፈጠረና ያስገኘ መኾኑን ቅድመ ኑባሬውን ያስረዳናል፤ (ዮሐ.1፥3)፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው” (ዕብ.13፥8) በማለትም ያለና የነበረ የማይለወጥ ሉዓላዊ መኾኑን ጭምር ያስተምረናል፡፡ ከሁሉ በላይና አስፈላጊያችን የኾነ ሊቀ ካህናት፣ የእግዚአብሔር ልጅና ወራሽ፣ የእግዚአብሔር ባሕርይ ትክክለኛ መገለጫና ዓለማትን ሥልጣን ባለው እግዚአብሔራዊ ቃሉ ደግፎ የያዘ መኾኑን በትክክል ሲያብራራ እንመለከታለን፡፡ 
1.4. ደረጋቸው ነገሮች ምልከታ ምስክርነት፦ ጌታ ኢየሱስ የተሰየመበት ወይም የተጠራበት ስሞቹ፣ ያደረጋቸው ድርጊቶቹ፣ ያስተማራቸው ትምህርቶቹ ፍጹም አምላካዊ ባሕርይውን የሚገልጡ ናቸው፡፡
1.4.1.      ሥያሜዎቹ አምላክና ከቀድሞም የነበረ መኾኑን ይመሰክራሉ፡፡
·        ጀመሪያና መጨረሻ፦ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፦ አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል” (ራእ.1፥8)፡፡ ሁሉም ነገር መጀመርያ፣ ሁሉም ነገር መጨረሻ አለው፡፡ የሁሉም ነገር ጀማሪና ፈጻሚ፤ መጀመርያና መጨረሻ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ለኹሉም ነገር መጀመርያና መጨረሻ ያበጀው እግዚአብሔር እርሱ ግን መጀመርያም መጨረሻም የሌለው፣ አልፋና ዖሜጋ ነው፡፡ ስለዚህም ዘወትር ነበር፤ ዘወትርም ኗሪ ነው፡፡  እንዲህ የተባለው ለክርስቶስ ኢየሱስ ለጌታችንና ለአምላካችን ነው፡፡ እርሱ በሰው ልጆች ታሪክ ላይ እንኳ የበላይና በጅማሬና በፍጻሜው ኹሉ ተቆጣጣሪና ጌታ መኾኑን አመልካች ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ አምላክ ነውና ይህን ለራሱ አውሎታል፤ (ራእ.21፥6 ፤ 22፥13)፡፡
   እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ለእግዚአብሔር አብ የተነገሩትም አልፋና ዖሜጋነት ለጌታ ኢየሱስም በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን፡፡ በኢሳ.41፥4 ፤ 44፥12 የተነገሩት የእግዚአብሔር “ፊተኛና ኋለኛነት” ለእስራኤል መታደስ ሁነኛና የማይቀር ተስፋውን መስጠቱን የገለጠበት ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ምንባባት ውስጥም የምንመለከታቸው የጌታ ኢየሱስ “አልፋና ዖሜጋነት” ለአብ ከተነገሩት ጋር ፍጹም አንድ በኾነ መንፈስ ነው፡፡
·        ፦ ጌታ ኢየሱስ በዘመነ ሥጋዌው ጌታ ተብሎ ተጠራ፤ “በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ ...” (ማቴ.7፥22)፣ “ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ፦ ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ” (ሉቃ.5፥8)፣ “ቶማስም፦ ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት፤” (ዮሐ.20፥28)፡፡ በእነዚህ ንባባት ውስጥ የኢየሱስ ጌትነት አምላክነቱን አመልካች ነው፡፡ ቶማስ ኹሉን ቻይነቱንና ፍጹም አምላክና ጌታ መኾኑን አሰምቶ ተናገረ፡፡ ደግሞም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የኹሉ ጌታ ተብሎ ተጠርቷል፤ (ሐዋ.10፥36)፤ የጌቶችም ጌታ ነው፤ (2ጢሞ.6፥15)፡፡
    በራእይ መጽሐፍ የታላቋ ባቢሎን ቅጣታዊ ፍርድ በተነገረበት ክፍል፣ በጉን ለመዋጋት ከአውሬው ጋር የሚተባበሩትን ኹሉ ድል እንደሚነሣና እንደሚያሸንፍ ተነግሯል፤ (ራእ.17፥14)፡፡ ይህ “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥነት” በብሉይ ኪዳ ለእግዚአብሔር አብም የተነገረና እግዚአብሔር ወልድም በቅድመ ኑባሬው የኾነው ነው፤ (ዘዳግ.10፥17 ፤ 136፥2 ፤ ዳን.4፥37)፡፡
·        ሰው ልጅ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን በመልበሱ ምክንያት ፍጹም ሰው ወይም የሰው ልጅ ተብሎ ተጠርቷል፤ ራሱንም በዚህ ስም በመጥራቱ ፍጹም ሰው መኾኑን በራሱ አንደበት አረጋገጠ፡፡ ይህ ፍጹም ሰውነቱ ግን በአምላክነቱ ተግባርም ተጠቅሷል፡፡ ለያህዌ የተነገሩት ሁሉ ለእርሱም ተነግረው እናስተውላለን፡፡ መላእክትን ማዘዝ የሚቻለው ያህዌ ብቻ ነው፤ ለጌታ ኢየሱስም እንዲህ ተባለ፤ “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል” (ማቴ.1341) የሚለውን ቃል በተዛማጅነት በሉቃ.128-9 1510 መመልከት ይቻላል፡፡
    የሰው ልጅም ተብሎም ቢጠራ እንኳ፣ በራሱ ሕልውና አለው (Self-existence)፤ (ዮሐ.5፥26)፣ አይለዋወጥም፤ አይጠፋምም (ዕብ.13፥8)፣ በሁሉ ቦታ ይገኛል፤ (ማቴ 28፥20)፣ ሁሉን ያውቃል (1ቆሮ.4፥5 ፤ ቆላ.2፥3)፣ ሁሉን ይችላል (ማቴ 28፥18) ወዘተ … መጥቀስ እንችላለን፡፡ እናም ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ በቅድመ ኑባሬው ከሥላሴ አንዱ አካል ሆኖ ይኖር ነበር፤ ደግሞም ይኖራል፡፡ የክርስቶስን ቅድመ ኑባሬነት[ፍጹም አምላክነት] የሚመሰክሩ ብዙ ሌሎችም የተጠራበት ስሞች፣ ያደረጋቸው ድርጊቶች፣ ያስተማራቸው ትምህርቶች አሉ፤ ይህን ብቻ ግን በጥቂቱ ለምሳሌነት አንስተናል፡፡
    ይህን ርእስ ስንጠቀልለው፣ አንድ አባት ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ቅድመ ኑባሬነት ሲያስተምሩ እንዲህ ማለታቸውን አስታውሳለኹ፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋቸውን የእጁን ሥራዎችና ትምህርቶቹን የሰማ ማናቸውም ሰው፣ ወይ ፍጹም አምላክ መኾኑን ይመሰክራል፣ አልያ እብድ ነው ብሎ ይተወዋል” ብለዋል፡፡ በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን አንብበን አምላክነቱን ለመካድ ማሰብ ከማበድ[ኅሊናን ከመጣል] በምንም አይተናነስም፡፡ ስለዚህም የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት መካድ ክርስትናን ሙሉ ለሙሉ መካድና አለመቀበል ነው፡፡ እኛ ግን የክርስቶስን ፍጹም አምላክነት ከሚቀበሉና ከሚያምኑ፣ ከሚያመልኩትና ከሚገዙለትም ወገን ነን!!! እንዲህ እናምናለን፤ እንታመናለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ጌታችን ሆይ! ክርስቶስ ጌታችንን በልባችን፤ በኹለንተናችን አክብረው፤ እናመልከውም ዘንድ እርዳን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል … 





    [1] አርዮስ ይህን ትምህርቱን ለማብራራት፣ [ምሳ.8፥22 ፤ ቈላ.1፥15 ፤ 1ዮሐ.4፥9ን በዋናነት ይጠቅሳል] ይህንንም ትምህርቱን በኒቂያ ጉባኤ ላይ አቅርቦት ነበር፤ በተለይም “ወልድ ከአብ ጋር ያልነበረበት ጊዜ አለ” በማለቱ መናፍቅነቱን በግልጥ አሳየ፡፡ ነገር ግን በቅዱስ አትናቴዎስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሞጋችነት በ325 ዓ.ም ትምህርቱ ተወግዟል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ይህን ትምህርት በማስተማሩም ምክንያት የእርሱን ትምህርት የሚከተሉ ኹሉ “አርዮሳውያን” ተብለዋል፡፡  
    [2] በዮሐ.1፥18 አብና ወልድ ተጠቅሰዋል፤ በዚህ ክፍል አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በልጅነቱ ተገልጧል፤ ስለዚህም የተለየ አካል እንዳለው እናስተውላለን፤ ደግሞም ልክ እንደእግዚአብሔር ዘላለማዊና ፍጹም አምላክ መኾኑን እናስተውልበታለንም፡፡ አብን ለመተረክ ወደእኛ ሲመጣ አምላክ ነው፡፡ አምላክ የኾነውን አብን በትክክል ለመተረክ፣ አምላክ የኾነው የአብ አንድያ ልጅ ብቻ ይቻለዋል፡፡
   [3] የዕብራውያን መልእክትን በአብዛኛው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው ቢታመንም፣ በአንዳንዶች ዘንድ ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክቶች ጋር በአጻጻፍ ስልቱ  ባለመገናኘቱ ወይም ባለመዛመዱ በርናባስ ወይም አጵሎስ እንደጻፈው የሚናገሩም አሉ፡፡ ነገር ግን ዋናውና ልንረሳው የማይገባን ነገር ቃሉ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የተስማማ በእውነተኛ የመንፈስ ቅዱስ መነቃቃት የተጻፈ መኾኑን አምነን እንቀበለዋለን፡፡

6 comments:

  1. አንድ አባት ስለኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ቅድመ ኑባሬነት ሲያስተምሩ እንዲህ ማለታቸውን አስታውሳለኹ፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋቸውን የእጁን ሥራዎችና ትምህርቶቹን የሰማ ማናቸውም ሰው፣ ወይ ፍጹም አምላክ መኾኑን ይመሰክራል፣ አልያ እብድ ነው ብሎ ይተወዋል” ብለዋል፡፡ እውነት ነው፡፡ እጅግ ይደንቃል፡፡

    ReplyDelete
  2. aben tsega yibzalh grum sra new

    ReplyDelete
  3. Geta bezh guday anten slasnesa smu yibarek tru ማንቂያ nee

    ReplyDelete
  4. “ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋቸውን የእጁን ሥራዎችና ትምህርቶቹን የሰማ ማናቸውም ሰው፣ ወይ ፍጹም አምላክ መኾኑን ይመሰክራል፣ አልያ እብድ ነው ብሎ ይተወዋል” ብለዋል፡፡ በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን አንብበን አምላክነቱን ለመካድ ማሰብ ከማበድ[ኅሊናን ከመጣል] በምንም አይተናነስም፡፡ yegeremegn neger berta wendm tru sra new

    ReplyDelete
  5. ተባረክ ደስ የሚል አቀራረብ ነው በርታ ወንድም

    ReplyDelete
  6. የአዲሱ ጌታ ጌታ ውጤቱ በጣም ይዘንኩት በአይኔ ያየውት ነገር ስለዚ ይሄ ጌታ ጌታ የሚል ሁላ የስይጣን አዲሱ ይእምነት ማስካጃ ሲስተም ነው ዛሬ በይ አዳራሹ በይመንደሩ እየተስበስቡ ይስይጣን አገልጋይ መገልገያ ስንቱ ሆኑ ያሳዝናል እግዚአብሔር ይገስፀው የዚ ስለባ ላለመሆን መሞከር ነው በእግዚአብሔር አይታዘንም ወደን ፈቅደን ነው እምነትን እምንከዳው ልክ እንደ አውሬው በጋሻው ጌታን ተቀብያለው የበቀል ቅባት ቀብቶኛል የራሴን ቸርች እከፍታለው የጌታ ነኝ ከዚ የበለጠ ሞት የለም ይሄው ነው መጨረሻው እግዚአብሔር ይስውረን እና ይሄንን ስላየው ስለስማው ነው መጨረሻውም ምን እንደሚሆን ስለማውቅ ነው የተናገርኩት

    ReplyDelete