Wednesday 1 November 2017

ልዩውን ወንጌል በወንድማማችነት ስም አለመቃወም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም!

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ስለማመንና ወንጌልን ስለማገልገል በሚገጥመን ነገር፣ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” (ማቴ.10፥37) በማለት በግልጥ አስተምሯል፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ጌታችን ክርስቶስና የክርስቶስ ትምህርት ዋናና ዘወትር የቀዳሚነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ነው፡፡ በዓለም ላይ ከትዳር፣ ከቤተሰብ፣ ከልጅ፣ ከአባት፣ ከእናት፣ ከባልንጀራ፣ ከወዳጅ፣ ከሃይማኖት አባት፣ ከሰባኪ፣ ከዘማሪ፣ ከመጋቢና ከቄሱም … ከማናቸውንም ሰውና ነገር ይልቅ ጌታችን ክርስቶስ ዋናና ተከታይ የሌለው ነው፡፡
   የክርስቶስ ዋናነት በትምህርታችን፣ በሕይወታችን፣ በመንገዳችን፣ በመውጣት በመግባታችን፣ በኹለንተናችን ጭምር ነው፡፡ በዓውደ ምሕረትም፤ ከዓውደ ምሕረት ስንወርድም፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነትም ኾነ ለብቻችን በመንገዳችን ኹሉ ክርስቶስ ዋናና አይነኬ የክርስትናችን መሠረትና ማንንም የማናስነካው ዓይነ ብሌናችን ነው፡፡ ቅዱሱ መድኃኒታችን ክርስቶስ በቅድስና የምንኖርለት ብቻ አይደለም፣ የምንሞትለትም ጌታችን ነው፡፡ በማናቸውም መንገዳችን ክርስቶስንና ትምህርቱን ለድርድርና ለአማራጭ አናቀርበውም፤ አናስነካውምም፡፡

    የክርስቶስ መምጣት በግልጥ ያስቀመጠው ጠላትነት አለ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የክርስቶስ ተቃዋሚ መካከል ግልጥ ልዩነት፣ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምንም ተካፋይነት፣ ብርሃንም ከጨለማ ጋር አንዳች ኅብረት፣ ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት፣ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል እንደሌለው፣ በክርስቶስ ልጆችና በሰይጣን ልጆች መካከል ታላቅ ጠላትነት ኾኗል፡፡ ጌታችን ክርስቶስን በማመናችን የሚመጣብንን የትኛውንም ተቃውሞ ፊት ለፊት ለመቀበል፤ ለመቃወምም መንፈስ ቅዱሳዊ አቅም በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ተቀብለናል፤ (ማቴ.10፥20)፡፡ ነፍሳችንን በመሰሰት ስለክርስቶስ ቸል አንልም፤ እናጣታለንና፤ ስለእርሱ ነፍሳችንን ማጥፋት ካለብን እናደርገዋለን፤ ከእርሱ እጅ ልንቀበላት እንድንችል እንምናለንና፡፡
   ባለንበት ዘመን ግን ይህ እውነት ሲሸረሸር እያየን ነው፡፡ ስለክርስቶስ ወንጌል መከራን መቀበልና መገፋት ታፍሮበት፣ ባልንጀርነትን አስበልጦ ማየት እንደክብር ሲቆጠር እያየን ነው፡፡ ይህ ክርስቶስን እናመልካለን በሚሉ ወንድሞች መካከል መከሰቱ እጅግ አንገት የሚያስደፋና አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ ከኹሉ ይልቅ አንድ የማያደርገንና ልዩ ወንጌል [በተለይም የእምነት እንቅስቃሴ አማኞች] የጨበጡ “ቀድሞ ከእኛ ጋር የነበሩ አሁን ያይደሉትን በግልጥ ኑፋቄን እያስተማሩ እያየን በብዙ መታገሳችን፤ ዝምታን መምረጣችን፤ ተዉ ለማለት አለመድፈራችን፣ አለመገሳጻችን፣ የሳቱትን “ባልንጀሮቻችን” ላለማስነካት መጣራችንና ከብበናቸው ለእነርሱ ዘብ መቆማችን “ምን እየተኰነ ነው?” የሚያስብል ጥያቄ ያጭራል፡፡
    ወንድማማችነታችን በክርስቶስ ትምህርት ስንስማማና ተቀባብለን ስንገኝ ብቻ ነው፤ በክርስቶስ ትምህርት ከተቀራረንንና ከተለያየን ወንድማማችነት አብቅቶለታል፡፡ ወንድማችነታችንን ያጸናልን የክርስቶስ ደምና የኢየሱስ ደም፤ ቅዱሱም ኪዳን ከተክፋፋ፣ እንደርኩሰት ከተረገጠ፣ ከተጣጣለ ወንድማችችነት የዓመጻ ደቦ እንጂ ክርስቶስንና ክርስቶሳዊነትን ፈጽሞ ሊገልጥና ሊያውጅ አይችልም፡፡ ልዩውን ወንጌል ከጤናማው የወንጌል ትምህርት ጋር ለማስማማት አልተጠራንም፤ የተጠራነው ለክርስቶስ ወንጌል ታማኝ ባላደራዎች እንድንኾን፤ የታዘዝነውንም ብቻ እንድናገልገል ነው፡፡
    አገልጋዮችን በተመለከተ ከምዕመናን እስከ ፓትርያርክ ወይም እስከአባቶች አለቃ ድረስ ግንኙነታችን የጎንዮሽ ነው፤ የምንተያየው በእኩልነትና በማይበላለጥ ማንነት ነው፤ [በእርግጥ ይህ አባባል በሊቃነ ጳጳሳትና በካርዲናሎች በሚተዳደሩት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ብቻ ሳይኾን፣ “ነቢያትና ሐዋርያት” በሚመሯቸውም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድም እየቀረ የመጣ ይመስላል፡፡] ወደላይ ልንመለከት የሚገባን አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም የቤተ ክርስቲያን ራስ የኾነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ አንድ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ወደጎን ከመታየት ይልቅ ወደላይ አንጋጥጠነው እንድናየው ከፈለገ “ዲዮጥራጢሳዊነት” (3ኛ ዮሐ.9) በመካከላችን ገንኗል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም፣ “ክፉን የሚያደርግ ግን እግዚአብሔርን አላየውም” (3ኛ ዮሐ.11) ለማለት ትናጋችን ከተሳሰረ ባልንጀርነት በልጦ ክርስቶስና ክርስቶሳዊ ቤተሰብ አንሶብናል ማለት ነው፡፡
   ቤተ ክርስቲያን ያላት ራስ አንድ ብቻ ነው፤ አማኞችም ኾንን ምዕመናንና ምዕመናት ኹላችን ብልቶችና አካላት ነን፡፡ በሥራ ድርሻ እንለያይ ይኾናል እንጂ፣ ምንም የምንበላለጥበት ነገር የለንም፡፡ ስለዚህ ኹላችን የምንጠነቀቅለት አንድ ነገራችን ቢኖር ራሳችንን[ክርስቶስ ኢየሱስን]  ነው፤ የራስ ሕልውና ለሌሎች ብልቶችና አካላት ወሳኝ ነው፡፡ ራሳችን ቢቆረጥ የሌሎቹ አካላትና ብልቶች ሥራ ጭርሱን እንደሚያበቃለት እንዲኹ፣ ክርስቶስንና ትምህርቱን ያለማስነካትና ለእርሱም መጠንቀቃችን ለመንፈሳዊ ሕይወታችንና ጤንነታችን መውደቅና አለመውደቅ ታላቅ መሠረት ነው፡፡
    ክርስቶስን ችላ ብለን ወንድማማችነትን ካስቀደምን ራሳችን ተቆርጦ በብልቶቻችን ሙሉ ጤነኞች ኾነን እንኖራለን ብሎ የማሰብና የመሞኘት ያህል ነው፡፡ ከራስ አንጻር ብልት ዋና አይደለም፤ ከክርስቶስ አንጻር የትኛውም አማኝ ወይም አገልጋይ ዋና አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያንም ኾነ የእያንዳንዳችን ዋና ክርስቶስ ከኾነ የማንደራደርበት ሕልውናችን እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ ከእናትም፤ ከአባትም፤ ከልጅም፤ ከሚስትም፤ ከምርጥ ወዳጅም፤ ከየትኛውም የሃይማኖት አባት ወይም ወንድም ይልቅ የኹለንተናችን ምርጥና ወደር የለሽ አዳኛችን፣ ቤዛችን፣ መድኃኒታችንና አምላካችን ነው፡፡ በተለይም የሐሰትን መምህራን ታግሰን የብልትን ሠላምና ደኅንነት ለመጠበቅ እጅግ መታለል ነው፡፡
    እንኪያስ የእርሱ ትምህርት ሲነቀፍ፣ ሲሰደብ፣ ሲካድ፣ በትምህርቱና በስሙ ሲሸቀጥ ዝምታን መምረጣችን የጤና ነውን? ስሙ እየተጠራ፣ ከቃሉ እየተጠቀሰ፣ ወንጌሉ ተጨብጦ በእኛው መካከል እንክርዳድ ሲዘራ፣ ምድራዊው ነገር ገንኖ ሰማያዊ ነገር ኮስሶ ሲነገር፣ እንደካህኑና ሌዋዊው ዘወር ብሎ እንዳላየ ማለፍ (ሉቃ.10፥31-32) ከወቀሳ ያተርፈን ይኾን? የእምነት እንቅስቃሴ ትምህርትን መታገስና በዝምታ ወይም ትምህርቱን ተግተው የሚያስተምሩትን “አገልጋዮች” በ“ይመለሳሉ[እንመልሳቸዋለን]” ተስፋ መጠበቅ አግባብ ነውን? አዎን! በግልጥ ሊመለሱ ወድደው ቢኾን ደስ ባለንና ብዙ በታገስን! ነገር ግን እነርሱ ትምህርታቸውን ከማስተማር ሳይቆጠቡ፣ ደቀ መዛሙርትን ለራሳቸውን እያከማቹ፣ በኋላቸውም ስበው እያስከተሉ … እኛ ግን “ዝናቸውን እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ይችላል”[ይህን ሃሳብ ስሰማ የመከሩን ጌታ ጠባይ(ማቴ.9፥37-38)፣ አገልጋይና አገልግሎት እንዳልገባን ነው የተረዳሁት] በሚል ክህደታቸውን በዝምታ ማለፋችን፣ ለክርስቶስ የጨከንን አገልጋዮች ስለመኾናችን ያስጠረጥራል፡፡

  ወንጌል የተጠየፈውን ትምህርትና ልምምድ እኛ ለማላመድ ማሰባችን በራሱ አደገኛና ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህም ለእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ በመሸነፍ፣ እየኾነ ያለውን አስነዋሪ ተግባር ከመካከላችን ልናስወግድ ይገባናል፡፡ አልያ የሐሰት መምህራንን እየታገሰ፣ እውነተኛ በጎችን ለተኩላ አሳልፎ የሚሰጠው ማንነታችን ነገ ራሳችንን ወደተኩላነት ወይም ተላላ እረኝነት[ዛሬስ ትግታችን መች ታይቶ?] ላለመለወጡ ምንም አስተማማኝ ነገር የለም፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ለመከሩ የታመኑ ብዙ ሠራተኞችን እንዲያበዛልን እንማልደዋለን፤ ደግሞም ስለበጎቹ ይገደዋልና እንደሚያስነሣ እናምናለን፤ አሜን፡፡  

3 comments:

  1. ባለንበት ዘመን ግን ይህ እውነት ሲሸረሸር እያየን ነው፡፡ ስለክርስቶስ ወንጌል መከራን መቀበልና መገፋት ታፍሮበት፣ ባልንጀርነትን አስበልጦ ማየት እንደክብር ሲቆጠር እያየን ነው፡፡ ይህ ክርስቶስን እናመልካለን በሚሉ ወንድሞች መካከል መከሰቱ እጅግ አንገት የሚያስደፋና አስነዋሪ ተግባር ነው፡፡ ewnetm lb sebari new Geta Eyesus yidresln

    ReplyDelete
  2. አንተ ልጅ ከአይን ያውጣህ ጌታ አማኑኤል ይርዳህ

    ReplyDelete