Tuesday 1 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አምስት)

Please read in PDf
የምንዋጋባቸው መሣርያዎቻችን
    መጽሐፍ ቅዱስ ከማን ጋር መዋጋት እንዳለብን አበክሮ የተናገረውን ያህል ከጠላታችን ጋር በመዋጋት በትክክል ስለምናሸንፍበት መሣርያም በግልጥ ይናገራል፡፡ ከዚህ በፊት እንዳየነው የምንዋጋው የእምነት ጦርነት ነው፡፡ የውጊያውም የጊዜ ቆይታ እስከክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡ “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታን ሆነን … የዲያብሎስን ሽንገላ መቃወም እንዲቻለን፣ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ መልበስ ያስፈልገናል”፡፡ ልብሱንና የጦር ዕቃውን መልበስና መለማመድ ግድ ነው፤ ያልተለማመድንበትና አብረን “ያልሰለጠንበት” ልብስ ለውጊያ ሊሆነን ፈጽሞ አይችልም፡፡
     የመሣርያው ዓይነት፣ የትጥቆቹ ይዘት በመከላከልና በማጥቃት ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ሥራዎች[መከላከልና ማጥቃትን] ክርስቲያኖች መፈጸም እንዳለባቸው ያስተምራል፡፡ ለጌታ መታዘዝን በባርያ ማንነት ውስጥ ሆነን የምናሳየውን ትጋት ያህል፣ ለጠላትና ለሚያስጨንቀው ገዢ አለመታዘዛችንና ግልጥ ተቃውሞዓችንን የምናሳይበት መንፈሳዊ ጠባይ የጌታ መንፈሳዊ ወታደር በመሆን ነው፡፡

    የበግ እረኛው ዳዊት ከጎልያድ ጋር ያደረገው ፍልሚያ መንፈሳዊ ወታደርነትን ለማብራራት የሚያስደንቅ ምሳሌ ነው፡፡ “ያልተፈተነበትንና ከዚያ በፊት ለብሶ የማያውቀውን ዘርፋፋውን” የሳዖልን ልብስ መልበስ ፈጽሞ አልወደደም፡፡ ልብሱ እጅግ ያማረና ውብ ነው፤ በክብርም ደረጃ የንጉሡ የክብር ልብስ ነው፡፡ ነገር ግን ለውጊያው ፈጽሞ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ዳዊት ለጦርነት ፈጽሞ እንደማያገለግል ዕቃ በማውለቅ መለሰው፡፡
   በዚህ ሃሳብ ውስጥ ሳዖል የራሱን ልብስ በማልበስ ዳዊትን ወደጦርነት መሸኘት የፈለገው፣ በዳዊት ገድልና ድል የራሱን ስምና ክብር ለማስጠበቅ በማለም ይመስላል፡፡ የእርሱ ባልሆነ ሥራ ስሙን ለማስጠበቅ መፈለጉን ዳዊትም ስለተረዳ “አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም” (1ሳሙ.17፥39) በማለት ልብሱን በማውለቅ በእረኝነት ሜዳ በሰለጠነበት በራሱ ልብስ ወደጦርነት ሥፍራው ሄደ፡፡ እያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን “በራሳችን ልምምድ” እንድንዋጋ ተጠርተናል፡፡ ሌሎች ከሚዋጉልን ይልቅ እኛ ከእግዚአብሔር በመዋጋት የምናካብተው መንፈሳዊ ቅዱስ ልምምድ ልባችንን በእግዚአብሔር ላይ ብቻ እንድናጸና ብርታት ይሆነናል፡፡
      ለውጊያውም የተሰጡን መሣርያዎች፣ “እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤” (ኤፌ.6፥14-18) ተብለው የተጠቀሱት ናቸው፡፡ እኒህንም በጥቂቱ ብንዘረዝራቸው፦
1.     ውነትን እንደዝናር መታጠቅ፦ በመካከለኛው ምሥራቅ ዝናር ወይም ድግ ወይም በዘመናዊው ቋንቋ ቀበቶ በወገብ የሚታጠቁት ዋና የሥራ ወይም የጦር ዕቃ ነው፤ አንድ ሰው ጠንካራ ሥራ ሊሠራ ከፈለገ ልብሱ በመንዘርፈፍ እንዳያስቸግረው ሰብሰብ አድርጐ የሚያስይዝበትና አጠር አድርጐ የሚታጠቅበትም ነው፡፡ አንድ ሰውም እንዲህ ባለ መልክ ሲታጠቅ ራሱን ለታላቅ ሥራ ማዘጋጀቱን ያሳያል፡፡
   ስለመሲሑ የወገብ መታጠቂያ ነቢዩ ኢሳይያስ ሲናገር፣ “የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይሆናል” (ኢሳ.11፥5) በማለት፣ ጽድቅና ታማኝነት ዋና መታጠቂያው እንደሆነ ተናግሮለታል፡፡ ታላቁ ቅዱስ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሠራ ላለው የፍርድ ተግባር በባሕርይ ዝግጁ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ እርሱ በእርግጥም እውነት ነው፤ (ዮሐ.14፥6)፡፡ እርሱ የእውነት መምህር ብቻ አይደለም፤ ራሱም እውነት ነው፡፡ ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ሁለንተናው እውነት ነው፡፡ እርሱን ማመንና ቃሉን መጠበቅ በእውነት መኖር ተብሎ ተጠቅሷል፤ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” (ዮሐ.8፥31-32)፣ እንዲል፡፡
    ወገብን አጥብቆ ለመያዝ ዝናር እጅግ አስፈላጊና በጦርነት ሥፍራ መታጠቅ እንደሚገባ እንዲሁ፣ ለመንፈሳዊ ውጊያ እውነትን እንደዝናር መታጠቅ ይገባናል፡፡ በውጊያው ውስጥ ከእውነት በቀር ሌላ  ነገር መቀላቀልና መሸቃቀጥ ፈጽሞ አይገባንም፡፡ በውጊያው ውስጥ ከጭካኔና ካለመራራት ይልቅ እውነተኛ የሆነውን የክርስቶስን ጠባይ በሕይወታችን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል፡፡ እውነትን እየሠዉ ውጊያ የለም፣ ከእውነት እየቀነሱ ውጊያ የለም፣ በእውነት ላይ እየጨመሩ በመሸቃቀጥ ውጊያ የለም፤ እውነት እንደዝናር ታጥቆ በመዋጋት ግን እውነተኛ ውጊያና ድል በዚያ አለ፡፡
   የተጠራነው፣ “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አይደለም”(2ቆሮ.13፥8)፤ ማናቸውንም ነገሮች መፈጸም ያለብን በእውነት መንገድ ብቻ በመሄድ ነው፡፡ ያለእውነት ሰይጣንንም ሆነ አገልጋዮቹን  ሐሰተኝነታቸውን በማጋለጥ ድል ልንነሣቸው አንችልም፡፡ በማኅበረሰባችን እሳቤ “ዋሽቶ ማስታረቅ” እንደመልካም እሴት ይቆጠራል፤ ነገር ግን ያለእውነት የሚሆነው ማናቸውም ትጥቅ ለዲያብሎስ ፈንታ የመስጠት ያህል ምቹ ነው፡፡
2.    ድቅን እንደጥሩር መልበስ፦ “ጥሩር ከብረታ ብረት ወይም ከቆዳ የሚሠራ ከአንገት እስከ ጉልበት የሚለበስ የጦር መሣርያ መከላከያ”[1] ነው፡፡ ጥሩር ከፊት ለፊት የሚመጣን ማናቸውንም የጦር መሣርያን መከላከል ወይም መመከት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ቃል የወሰደው፣ “ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ” (ኢሳ.59፥17) ከሚለው ምንባብ ነው፡፡ ንባቡ በግልጥ እንደሚያመለክተውም እግዚአብሔር ኃጢአትን ሊዋጋ እንደሚነሳና ፍትሕ ለተነፈጋቸው ሰዎች የሚያደርግላቸውን ፍጹም ማዳን የሚያመለክት ነው፡፡
    እውነተኛ ክርስቲያኖች የኃጢአትን ዓለም ከሚገዛው ከዲያብሎስ ጋር ሲዋጉ ሊለብሱት ከሚገባቸው ዋና ልብስ አንዱ የጽድቅ ጥሩር ነው፡፡ ዲያብሎስ ከሚያቀርብብን ክሶች አንዱና ቀዳሚው፣ በክርስቶስ ያመንነውና በሞቱና በትንሣኤው የቆምነውን “ጻድቃን አይደላችሁም” የሚል ነው፡፡ ከዚህ የኃጢአት ክስ የተነሣም በክርስቶስ የተደረገልንንና የተቆጠረልንን ጽድቅ አሳንሰን እንድናይና ጽድቁን እንደጥሩር ከመልበስ ቸል እንድንል ያደርገናል፡፡ ይህንን እርሱን በመስማት ስንቀበለው ውድቀታችንን እንደምናቻኩለው ያውቀዋል፡፡
    በክርስቶስ ጽድቅ አለመሸለም፣ በተቀሰተ ቀስትና በተወረወረ ጦር ፊት ዕርቃን የመቆም ያህል ነው፡፡ ሰይጣን በክርስቶስ ጽድቅና ትክክለኛነት መመካትና ጽድቁን ለብሶ መቆም እጅግ ታላቅ ነገር እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዋና ዓላማም በክርስቶስ ጽድቅ ተሸልመን በእግዚአብሔር ፊት እንቆም ዘንድ ነው፡፡ ስለኃጢአት፣ ስለጽድቅ ቢወቅሰን ፊታችንን ወደክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዘወር እናደርግ ዘንድ ነው፡፡ ያለክርስቶስ ደምና ያለመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ከሰይጣን ፊት ለፊት ቆመን መዋጋትም ሆነ ድል መንሳት የማይቻል ነገር ነው፡፡
    ባላጋራችን ሰይጣን ሁል ጊዜም ሰዎች ከዚህ ጽድቅ በመሸሽ የራሳቸውን ጽድቅ እንዲያቆሙ ራስን ያለመካድና በእኔነት የመቆምን መንገድ ያሳያል፡፡ የራስ ጽድቅ የመርገም ጨርቅ ያህል የማይጠቅምና ርኩስ ሆኖ ሳለ በዚያ እንድንመካ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህም በተደረገልንና የኃጢአታችን ክፍያና ቤዛ በሆነልን በክርስቶስ የሥጋ ሞት ልንታመን፣ በመታመንም ከሰይጣንና ሠራዊቱ ጋር ልንዋጋ፤ ድልም እንድንነሣ በርቱ የሚል መለኮታዊ የብርታት ቃል ተነግሮናል፡፡ በእንዲህ መንገድ የሚዋጉትን ሁሉ ዲያብሎስ ይቋቋማቸው ዘንድ ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በዚህ እውነት ያጽናን፤ ለቅድስናም እንድንተጋ ያበርታን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ አሳታሚ የኢትዮጲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ ገጽ.256

No comments:

Post a Comment