Wednesday 9 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ስድስት)

                            Please read in PDF
3.    ሠላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፦ የጫማ ዋና ሥራ ከማናቸውም እንቅፋት፣ እሾኽና እግርን ከሚጎዳ አደጋ መከላከልና መደገፍ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ፡፡ ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው” (መዝ.119፥104-105) አለ፤  በጥንት አይሁድ አንድ ሰው የሩቅ መንገድ ሲጓዝ ድንገት ቢጨልምበት፣ በሚሄድበት መንገዱ እንዳይሰናከል በእግሮቹ ላይ መብራትን ያሥራል፡፡ ይህም የሚረግጥበትን በትክክል እንዲያስተውልና ወድቆም ከመሰበር እንዲድን ይረዳዋል፡፡
   ዳዊት በማናቸውም የሕይወት መንገዱ የእግዚአብሔር ሕግ መብራትና ብርሃኑ ነው፤ ስለዚህም በማናቸውም መንገዱ ቢሆን ከሐሰት ጋር አያመቻምችም፣ አይስማማምም፡፡ የሐሰትን መንገድ ከነፍሱ እጅግ ይጠየፋል፡፡ መብራትና ብርሃኑ የሕጉ ቃል ነውና፣ ይህንንም ሕግ በማናቸውም መከራ ውስጥ እንኳ ቢያልፍ ከመጠበቅና በሕጉም ከመጽናናት ቸል አይልም፡፡ በዳዊት ንግግሮች ውስጥ ሁል ጊዜ ዝግጁነትና ፍጹም ታማኝነት አለ፡፡

      ልክ እንዲሁ ቅዱስ ጳውሎስም፣ የሮማዊውን ወታደር የጫማ አለባበስ በማየት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሠላምን ወንጌል በትክክል መጫማት እንዳለብን ይነግረናል፡፡ የሮማ ወታደሮች ያለጫማ ማናቸውንም የውጊያ እንቅስቃሴ አያደርጉም፡፡ ለማናቸውም ሥራ እንኳ ቢሆን ጫማቸውን ተጫምተው ለመንቀሳቀስ ዝግጁዎች ናቸው፡፡ በእርግጥም የወታደር ኑሮ ዘወትር ተጠንቅቆ በዝግጁነት የመኖር ኑሮ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ አማኞች መከራ ለሚያደርሱባቸውና ለሚቃወሟቸው፣ “በእነርሱ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ” ብቻ ያይደለ (2ጴጥ.3፥15)፣ “በሠላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻቸውን ተጫምተው በመቆም” ዲያብሎስን ሊዋጉ፤ በሚያደርስባቸው መከራና  ፈተና ሁሉ ሊቋቋሙት ይገባቸዋል፡፡
    የሠላም ወንጌል ሰውና የተባለው እግዚአብሔር የታረቁበት ነው፡፡ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ጠብ የተቋጨውና የተደመደመው በክርስቶስ በደሙ መካከለኝነትና በወንጌሉ የእርቅ ቃል ነው፡፡ ይህ ቃል ሰዎች ከኃጢአታቸው እንዲድኑበት የምሥራች ብለን የምንናገረው ብቻ አይደለም፤ ደግሞም ክፉውንና ፈጽሞ ሰላምና ፍቅር የማይሻውን ዲያብሎስን፣ የሠላምን ወንጌል ተጫምተን ወይም ፍጹም ለብሰን የምንዋጋበትም ጭምር ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከለበሰው ሥጋ የተነሣ ሊያሳስት የመጣውን ክፉ ጠላት ዲያብሎስን ድል የነሣውና “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን …” (ማቴ.4፥1-10) በማለት ከእርሱ ያራቀው፣ በቅዱስ ቃሉ “መጫሚያት” ነው፡፡ የዲያብሎስን የሐሰት ንግግሮች ማፍረስ የሚቻለንና ማሸነፍ የሚቻለን ክርስቶስ በተናገረው በሠላሙ ወንጌል እውነተኛ ቃሎች ብቻ ነው፡፡
     ከምንም በላይ በዚህ ዘመን ዲያብሎስን ድል መንሣት የማይቻለውን፣ ኃጢአትን የሚያሞጋግሰውን ልዩ ወንጌል የሚናገሩ ብዙ ወገኖች ተነስተዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገር ሁሉ ከእግዚአብሔር ተልኮ ያልመጣ እንዳልሆነ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጠው “የመለያየትና የልዩነት ወንጌል” እያስተማሩ “የሠላም ወንጌል ምስክሮች ነን” የሚሉትን አመቻማቾችን መለየት ይገባናል፡፡ በዚያው ትይዩ ደግሞ ሁል ጊዜ ማስተዋል ያለብን እውነት፣ የሠላምን ወንጌል በቅንነትና በእውነት የሚያገለግሉና ተጫምተው የቆሙ አማኞችም ሆኑ አገልጋዮች ፍጹም የሰይጣን ጠላቶች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ እኒህን አገልጋዮችንና አማኞችን የሰይጣን አገልጋዮች ፈጽመው ስማቸውን በማጥፋት ቢጠመዱ ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይደለም፡፡
4. እምነትን ጋሻ አንሡ፦ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ በመናገር ወይም ቃሉን በማወጅ ብቻ የምንመሰክር አይደለንም፡፡ ልንመሰከር ከተጠራንባቸውና የክርስቶስ ወገኖች መሆናችንን ከምናሳይባቸው  መንገዶች አንዱ፣ ከሰይጣን፣ ከክፋት ኃይላት፣ ከኃጢአትና ርኩሰት ጋር ፍጹም ደምን እስከማፍሰስ ድረስ በመቋቋምና በመዋጋትም ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ወንጌልን መስበክና ማስተማር እጅግ መልካም የሆነውን ያህል ሰይጣንና ሠራዊቱንም በመቃወምና በመዋጋት የምንፈጽመውም ተጋድሎ የምስክርነታችን ዋነኛውና ሊዘነጋ የማይገባው መንገድ ነው፡፡
    ጋሻ፣ ከፊት ለፊት ወጥተው የሚዋጉ ወይም የሚያጠቁ ተዋጊ ወታደሮች በእጅ የሚይዙት፣ ለመከላከያ እጅግ ከሚጠቅሙ የጦር መሣርያዎች አንዱ ነው፤ (ኢሳ.21፥5)፤ የጥንት ጋሻዎች በቈዳ የተለበጡ፣ የእሳት ነበልባል ያለባቸውንና ሲወረወሩ የሚምዘገዘጉ ፍላጻዎችን እንዲያጥፉና የሚንበለበለውንም ነበልባል እንዲያጠፉ በውኃ ውስጥ ተነክረው፣ ለአያያዝ እንዲመቹ፣ ሁለንተናንም መከላከል እንዲያመቹ ሰፊ ሆነው የሚዘጋጁ ናቸው፡፡
     በመጽሐፍ ቅዱስ ጋሻ የእምነትና የእግዚአብሔር ረድኤት ምሳሌ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር በእርሱ ለሚታመኑት ጋሻና ጦርን ያነገበ ተዋጊ መሆኑን፣ “አቤቱ፥ የሚበድሉኝን በድላቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው፡፡ ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ፤ (መዝ.35፥2)ይላል፡፡ ጋሻ የጨበጠና ወደውጊያው የገባ ሰው ድፍረቱና ትምክህቱ ከፊት ለፊቱ የተወደረው ጋሻው ነው፡፡ ጋሻው እስካልተቀደደና እርሱም እስካልሰነፈ ድረስ ውጊያውን በድል የማያጠናቅቅበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በውጊያ ውስጥ ትልቁ ትምክህታችንና የምናነሳው ጋሻችን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ በእርሱ እስከታመንን ድረስና ከእርሱ ውጪ በልባችን ሌላ ትምክህት ከሌለን በቀር በዲያብሎስና ሠራዊቱ ፊት የማንቻል አሸናፊዎች ነን፡፡
    የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር በታመኑና እርሱን ብቻ ትምክህታቸው ብቻ ባደረጉበት ወራታቸው ወቅት አሸናፊዎችና ድል ነሺዎች ነበሩ፤ (1ሳሙ.7፥8 ፤ 13 ፤ መሣ.7፥23)፡፡ ባልታዘዙና በእርሱ ባልታመኑበት ጊዜያቸው ሁሉ ደግሞ ተሸናፊዎችና ድል ተነሺዎች ነበሩ፤ (1ሳሙ.4፥10 ፤ መሣ.6፥1)፡፡ በእግዚአብሔር አለመታመን በአምልኮ የማመንዘር ነው፡፡ እግዚአብሔርም በእርሱ የማይታመኑትን ፈጽሞ ይጥላቸዋል፤ አይራዳቸውምም፡፡ ትምክህታችሁ በማን ነው? ወደውጊያው በማን ተማምናችሁ ወጣችሁ? በጸጋው? በአገልጋዩ? ወይስ ጸጋንና አገልጋይን በሚሰጠው በራሱ በምንጩ በእግዚአብሔር?
    እግዚአብሔር የእርሱ ስለሆኑት እነርሱን ተገብቶ ይዋጋል፡፡ በእርሱ ለሚታመኑት ጥሩርና ጋሻ ለብሶ እንደሚዋጋ ብርቱ ተዋጊ እግዚአብሔርም ለሚታመኑለት ሳይሰለች ይዋጋል፡፡ እግዚአብሔር የእኛን ውጊያ እንዲዋጋ እኛ ሙሉ ለሙሉ በእርሱ መታመን አለብን፡፡ በእርሱ ለታመኑት፣ ከክንዱ በታች ለነበሩት እስራኤል እግዚአብሔር ከጦረኛው ፈርዖንና ሠራዊቱ እንዴት እንዳዳናቸው አስተውሉ! የባሕሩን ግድግዳ ቀጥ አድርጎ እንደጋሻ አቁሞ ማዕበሉና ፈሳሹ እንዳያገኛቸው አደረገ፡፡ አለን ብለን ከምንመካበትና ከምንጠቀመው መሣርያ ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ ያለን መታመን ትልቅና ነገሮችን መለወጥ የሚቻለው ነው፡፡ እንኪያስ አማኞች ሆይ! በእግዚአብሔር ላይ ተደግፋችሁ በጠላታችሁ ላይ የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ እርሱ ድልን ያለብሳልና፡፡
     ከምንም በላይ ለእኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ለምናምን፣ የትምክህታችን ምንጩ የክርስቶስ ጽድቅና ቤዛነት ነው፤ “የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው” እንዲል (1ቆሮ.1፥30-31)፡፡ በእግዚአብሔር ፊት እንደጻድቃን የተቆጠርነው ብቻ ያይደለ፣ በጠላት ፊት ውጊያችንን በድል የምናጠናቅቅበት የእምነታችን ትምክህትና በእምነት የምናነሣው የእምነት ጋሻችን ራሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን  ነው፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይህን ማስተዋል እንድንችል ይርዳን፤ አሜን፡፡

ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment