Tuesday 18 July 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ አራት)

                                                                                   Please read in PDF
2. ዋጉ፦ በክርስቶስ ኢየሱስ ካመንንበት ቀን ጀምሮ ከክፋት ሁሉ አሠራርና ከዲያብሎስ ጋር ውጊያ ለመግጠም ፊት ለፊት ተፋጥጠናል፡፡ ደጋግመን እንዳነሣነው ውጊያችንም ከሥጋ ለባሽ ፍጡር ጋር ሳይሆን፣ ከጀርባው ለራሱ ክብርና አምልኮን ለመቀበል ከሚሠራው[ወንጌል የጨበጡ አገልጋዮችንም ጭምር በመጠቀም] ከክፉ መንፈሳውያን ሠራዊት አለቃ ከሆነው ከዲያብሎስ ጋር ነው፤ (ኤፌ.6፥12)፡፡ ውጊያውን በተመሳሳይ መንገድ በመቆም እንጂ በግል ማንነታችን ብቻ ማሸነፍ እንደማንችል መጽሐፍ ቅዱስ ደጋግሞ ነግሮናል፡፡
     “በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን፤ ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፤” (2ቆሮ.10፥3-5) እንዲል፣ ሰይጣን የሚሰወርበትንና የሚሰውርበትን የክፋትን ምሽግ፣ የስህተትን ትምህርት፣ ርኩሰትና ኃጢአትን ሁሉ ለማፍረስና ለመደምሰስ ፍጹም የሆነ ብቃት ያለውና ጠንካራው መሣርያ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ጦር ዕቃ ብቻ ነው፡፡

    የክፋት የሆነውን የዲያብሎስን የትኛውም መሣርያ፣ መርታትና ድል መንሣት የሚቻለው ጠንካራና ብርቱው፤ መንፈሳዊ የሆነው ቅዱሱ የእግዚአብሔር መሣርያ ብቻ ነው፡፡ ከእኛ በሆነው ጥበብና ማስተዋል የዲያብሎስን ምሽግ ማፍረስም ሆነ መደርመስ አይቻለንም፡፡ ሥጋዊ አቅም፣ ጥሩ የስበከት አቀራረብና የመርሐ ግብሮች ዝግጁነት፣ ማራኪ ድራማና ጭውውቶች፣ ፈገግታ አዘልና አዝናኝ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ሰይጣንን ለመርታት አቅም አይሆኑም፡፡ በመጀመርያዎቹ ረጅም የሰንበት ትምህርት ቤት የአገልግሎት ዘመኔ ብዙ ወጣቶች እንዲመጡና ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሞልቶ እንዲታይ ለማድረግ፣ ትልቁ የዝግጅት ጊዜያችንን ይወስድ የነበረው ድራማ፣ ጭውውት፣ አነቃቂና አዝናኝ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን ከወንድሞች ጋር ያተረፍነው ከድካም በቀር ምንም አልነበረም፡፡
     በኋለኛው ዘመን የአገልግሎት ዘመኔ ግን ያን ሁሉ ከወንድሞቼ ጋር ተማክረን፣ እጅግ በመቀነስ ትኩረታችንን ጸሎትና ቃሉን በአዳር መርሐ ግብሮች[ለበዓላት ንግስ በሄድንባቸውና ራሳችን ባዘጋጀናቸው] ማጥናት ስንጀምር ግን የብዙዎቻችን የሕይወት ለውጥና የመንፈስ ፍሬዎችን ማየት ጀምረን ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ባልጠበቅነው መንገድ ስደትና ተቃውሞን ማስተናገድ ጀምረንም ነበር፡፡ ብዙዎች ወደኋላ ቢያፈገፍጉም ቃሉን አብዝቶ በመመገባችንና በጸሎት መትጋታችን ያንን አስፈሪ ተቃውሞ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ማለፍ ችለናል፡፡
    ከአለም የሚመጣብንን ፈተናና ውጊያ ሁሉ በጥሩ የመርሐ ግብር ዝግጅትና  በጥሩ የስብከት ለዛዎች ማለፍ አይቻልም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችም የክፋትን ጠባያት ከእኛ ማራቅና እኛን ለእግዚአብሔር በትክክል ማቅረብ አይቻላቸውም፡፡ የክፋትንም ኃይላት በትክክል እንድናሸንፍም አይረዱንም፡፡ በጌታ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በትክክልና በእምነት ካልተደገፍን ውጊያውን “እንደወታደር” በመዋጋት የኃጢአትን ኃይል መስበርና ከመገኘቱ መዳን አንችልም፡፡
    “… የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ አፍርሰን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ ለመማረክ”፣ በዝንባሌ፣ በጠባይ፣ በሐሳብ፣ በኑሮ ዘይቤ ጭምር ንጹህና ቅዱስ በመሆን ለጌታችን ኢየሱስ መገዛት ይጠበቅብናል፡፡ በሁለንተናችን ለምናደርገው ማናቸውም ነገር እንጠየቅበታለንና፡፡ ውጊያችን ዝሙትን፣ ስድብን፣ መዳራትን፣ ዘፈንን፣ ስርቆትን … ካለመፈጸም ድርጊታዊ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን፣ “የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥” (መክ.12፥14)፤ “ … መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል …” (2ቆሮ.5፥10)፡፡ ስለዚህም “በመጎምጀት ቆንጆይቱን ከመመልከት” (ኢዮ.31፥1)፤ “የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት” (1ዮሐ.2፥16) ከእኛ ማራቅ ይገባናል፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከባድ ውጊያና “ሂድ፥ አንተ ሰይጣን” ብሎ በግልጥ መቃወምን(ማቴ.4፥10)፤ “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት መካድ” (ቲቶ.2፥12)፤ “በጎ ለማድረግ አውቀን መሥራት” (ያዕ.4፥17) እጅግ ከክፋት ኃይላት ጋር በመዋጋት ልናደርገው ይገባናል፡፡
    በቤታችን፣ በመንገዳችን፣ በተንቀሳቃሽ ስልካችን፣ በምናነባቸው መጻሕፍት ውስጥ ተመሽገውና ተሰድረው የተቀመጡት ምን ይሆኑ? እኛን በቀላሉ የሚያንበረክኩ ወጥመዶች ወይስ ውጊያችንን የሚያስቸኩሉ መልካም ነገሮች ይሆኑ? ብዙዎቻችን በውጊያ አንዲት የቀስት ደጋን ሳንደግን በአውላላ ሜዳ ላይ የምንሸነፈው ከዲያብሎስ በሚነሳብን ጽኑ ውጊያ ሳይሆን በገዛ ፈቃዳችን በፊታችን በምናኖረውና በልባችን በምናመላልሰው ከንቱ ሃሳባችን ነው፡፡ “በጽድቅ መሄድ ቅን ነገርንም መናገር፥ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን መናቅ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጅን ማራገፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮን ማደንቆር፥ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቻችንን መጨፈን”(ኢሳ.33፥14) ከኃጢአት እንደሚቆጠር ገና ከማስተዋል የደነዘዝን ይመስላል፡፡ ሃሳባችን፣ ወደንግግር፣ ንግግራችን ወደተግባር፣ ተግባራችን ወደልምምድ፣ ልምምዳችን ወደባሕርይ ሊለወጥ እንደሚችል ከማስተዋል ችላ ብለናል፤ እንግዲያውስ ውጊያችን እኒህን ሁሉ ነገሮች የሚያካትት፣ የውጪውን ብቻ ሳይሆን በውስጣችንንም ያለውን የክፋት ሃሳብ ድል መንሣትን ያስፈልገናል፡፡
     ቃሉን ባለማጥናትን በጸሎት ካለመትጋት የሚመጣውን ቀላሉን “መንፈሳዊ ልምምድን” ገንዘብ ከማድረግ በእጅጉ መከልከል ይገባናል፡፡ የዚህ ዘመን አገልጋዮች ተስፋችንንና ትምክህታችንን ከጌታ ኢየሱስ ላይ እንድናነሳበት ካደረጉበት መንገድ አንዱ ቁሳዊ ተስፋንና ምድራዊውን መፍትሔ ልክ እንደመንፈሳዊ ትርፍ አድርገው “ወዲያው” በማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት በመዘግየት የሚመጣውን ቅዱስ ሃሳብና መልእክት በመታገስ መቀበልን የመንፈሳዊ ሕይወታችን ልምምድ ማድረግን መውደድ ይገባናል፡፡
      የምንዋጋው ክርስቶስ በሥጋ ሞቱ ባጠናቀቀው ድል ላይ ቆመን ነው፡፡ እርሱ፣ “ኃይለኛውን አስሮ” (ማቴ.12፥29)፣ “ምርኮን ማርኮ ለሰዎችም ስጦታን በመስጠት” (ኤፌ.4፥7)፣   “ … የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመስሶ፤ በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ በማስወገድ፤ አለቅነትንና ሥልጣናትንም ገፎ፥ ድል በመንሣት”(ቈላ.2፥15)፤ “ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንድንል ዓይናችንን ከፍቷል” (ሐዋ.26፥18)፡፡ ስለዚህ እርሱ ያጠናቀቀውን ውጊያ በእርሱ ጉልበት መሮጥ ይገባናል፡፡
     ስለዚህ ተዋጊዎችና በመንፈስ የሰውነትን ሥራ ገዳዮች የኾንነው(ሮሜ.8፥13)፣ በራሳችን ብቃት አይደለም፤ ወይም የዚህ ዘመን አብዛኛዎች አገልጋዮች አድርጉ እንደሚሉን ባለው መንገድ አይደለም፡፡ ቀድመን እንደተናገርነው መሣርያችን ሰማያዊ፤ ከእግዚአብሔር የሆነ ብርቱና ጠንካራ፤ መንፈሳዊም ነው፡፡ በውጊያችንም ውስጥ፦
ü መከራን ሁሉ መታገስ ወይም መቋቋም ይገባናል፤ ቅዱስ ጳውሎስ “በመከራ ታገሡ” ይለናል፤ (ሮሜ.12፥12)፡፡ መከራ ብዙ ጊዜ ለፍላፊ ያደርጋል፤ በምናልፍበት የትኛውም የውጊያ መንገዳችን ግን መከራን መቀበል እንዳለብን ማመንና ዝግጁዎች መሆን መቻል አለብን፤ (ማቴ.5፥10 ፤ ሮሜ.8፥17 ፤ 2ቆሮ.11፥23 ፤ 2ጢሞ.2፥3)፡፡
ü በውጊያው ውስጥ ማናቸውንም የክፋትን ምሽግ ለማፍረስ አቋማችን ግልጥ መሆን ይገባዋል፤ አቋማችን የቅዱስ ቃሉ ሊሆንም ይገባል፡፡ ስህተትን የሚዘሩትንና ቃሉን በማጣመም የሚናገሩትን ሁሉ ደግሞ መቃወምና ለቃሉ ሥልጣናዊ ቃልነት መጋደል ይገባናል፡፡ በዚህም የሚመጣ መከራ ካለ መቀበል፣ “መልካሙን የእምነት ገድል በመጋደል፥ የተጠራንለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንለትንም” ጌታን በመታመን መልካሙን ጦርነት መዋጋት ይገባናል፤ (1ጢሞ.6፥12)፡፡
ü  በፍጻሜውም ማሸነፍና የእምነት አርበኞች መሆናችንን ማሳየት መቻል አለብን፤ (ሮሜ.8፥37 ፤ 1ቆሮ.15፥57 ፤ ዕብ.11፥34)፡፡
    አሸናፊዎች ለመባል ከቃሉ ውጭ የሚነገረውን ብልሃታዊ የሰው መንገድ አንከተልም፡፡ ማሸነፍ ያለብን ቃሉ ባለን መንገድ ላይ እንደቃሉ በመጋደልና በመዋጋት ነው፤ ላብን ጠብ ከሚያደርግ ትጋት እስከ ሰማዕትነት ድረስ ለስሙና ለቅዱስ ወንጌሉ በቅድስና መዋጋት ከእኛ እጅግ ይጠበቃል፡፡ ይህንን ስናደርግም ትኩረታችንን ሁሉ ከሥጋ ለባሽ ላይ በማንሳት ወደዋናችን ጌታ ኢየሱስ ማድረግ ይገባናል፡፡ በዚህም ደስታችን እጅጉን ይበዛል፡፡ አዎን! ታማኝ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን እምነታቸውን ለመጠበቅ በሥጋና በደም አቅም ያይደለ፣ ከመንፈስ ቅዱስ በሆነ መንፈሳዊ አቅምና ጉልበት መዋጋት ይገባቸዋል፡፡
      ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! እንዲህ ባለ ትጋት ባርያዎችህን አበርታን፤ አሜን፡፡

      ይቀጥላል …

1 comment:

  1. bemtlekew melkt betam enwedhalen berta

    ReplyDelete