Friday 7 July 2017

ዘፈን - የወደቀው መልአክ እንጉርጉሮ (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF
እግዚአብሔር ዘፈንን አይባርክም!

    ከዘፋኞች በተደጋጋሚ የምናደምጠው፣ “እግዚአብሔር ዘፈናቸውን እንደሚባርክ፣ ለዘፈን የሚኾን ድምጽ እንደሰጣቸው፣ በመዝፈናቸው እግዚአብሔርም ጭምር ሊደሰት እንደሚችል፣ እንዲያውም ለመዝፈናቸውና ካሴት ለማሳተማቸው ጭምር እግዚአብሔር እንደረዳቸውና እንደባረከላቸው” ሳያፍሩ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እኔን ብዙ ጊዜ እንደገባኝ ግን፣ “እግዚአብሔር” ሲሉ፣ ቅዱሱንና ለኃጢአት ልጁን አሳልፎ የሰጠውን እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔር ብለው እንደማይጠሩ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ዘመን ቅዱሱ እግዚአብሔር ከኃጢአት ጋር የተደራረደረበትና “ኃጢአትን የባረከበትን ሂደት” ሰምተንም፤ አይተንም አናውቅምና፤ ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዲህ ያለውን ምስክርነት ፈጽመው አላስቀመጡልንም፡፡
     እግዚአብሔር ዘፈንን የሚባርክ ከሆነ፣ ከዘፈን ጋር የተጠቀሱትንም የሥጋ ፍሬዎች “ዝሙትን፥ ርኵሰትን፥ መዳራትን፥ ጣዖትን ማምለክን፥ ምዋርትን፥ ጥልን፥ ክርክርን፥ ቅንዓትን፥ ቁጣን፥ አድመኛነትን፥ መለያየትን፥ መናፍቅነትን፥ ምቀኝነትን፥ መግደልን፥ ስካርን፥ … ይህንም የሚመስለውን ሁሉ” መባረክ አለበት እያልን ነው፡፡ ሌላውን ሁሉ ጥሎ፣ ነጥሎ ዘፈንን ይባርካል ማለት፣ እግዚአብሔርን የስንፍና ሃሳባቸው ደጋፊ ለማድረግ ከማሰብ የመነጨ ተላላነት ነው፡፡ እንጂማ ዘፈን ከምንና ከማን ጋር እንደተጠቀሰ በትክክል ቢያነቡት፣ “እግዚአብሔር ዘፈንንም ይባርካል” በማለት እግዚአብሔር ላይ ለመሳለቅ ባልደፈሩ ነበር፡፡

   ዘፈን ኃጢአት አይደለም የሚሉት አካላት፣ አይደለም ካሉ በኋላ የሥጋት ቃጭላቸውን ያሰማሉ፤ እንዲህ ዓይነቱን ዘፈን እንጂ እንደዚያ ዓይነቱን ዘፈንን “ቅዱስ ነው አላልንም” የሚል “የተላላ ሃዘኔታ”፡፡ “ዘፈንን ኃጢአት ነው” የሚሉ ግን ምንም የሚያሰጋቸው ነገር የለም፡፡ ለአንዱ ጌታ ለእስራኤል ቅዱስ ብቻ ቀንተዋልና፡፡ ሁለቱን ተቃራኒ “ጌቶች“ና መንግሥታት [ማለትም እግዚአብሔርንና ሰይጣንን ወይም መዝሙርንና ዘፈንን] ለማስታረቅ ከመሞከር ለአንዱ ብቻ መገዛት የተሻለ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ለሆነው  መዝሙር መሸነፍና መሰጠት ግን ልባቸው ለቀና ብቻ ነው!!!    
     እንደድንበር ከተማ ነዋሪዎች መንታ ባህልና መንታ ቋንቋን መያዝ፣ “ለሥጋ ፍሬ” ማደለቢያ ራስን አሳልፎ ለመስጠት ካልሆነ በቀር፣ “መንፈሳዊ ቤት ሆኖ” ለመሠራት አይጠቅምም፡፡ በእውነት በክርስቶስ በደሙ ኃይል፣ በሞቱና በትንሣኤው ጉልበት ከዚህ ከጠማማና ከማያምን ዓለም አምልጠን ከዳንን፣ ሊያረካንም ሊያሳርፈንም የሚችለው የእርሱ ድምጽ ብቻ ነው፤ እኛም የሚናፍቀን የእርሱ ድምጽ ብቻ ነው፤ የክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ድምጽ፡፡ በክርስቶስ ትምህርትና ድምጽ እንዳለመርካት ያለ አለመባረክ ፈጽሞ አይኖርም፡፡ እርሱ ደግሞ ከእርሱ በሆነ ቅዱስ ነገር እንጂ ከሥጋ ፍሬዎች በአንዱ ፈጽሞ አይባርከንም፤ የቅዱስ ባሕርይውም ፈቃድ አይደለም፡፡
    በዚህ ርእስ ከሚነሱ ክርክሮች መካከል፣ “በመልካም ቃላት የተሽሞንሞኑና ጥሩ ምክር ያለባቸውን ዘፈኖች ብናደምጥ ምን አለበት?” የሚል አንድ ሙግት አለ፡፡ በክርስቶስ ለሚያምኑ የምለው ነገር አለኝ፤ ክርስቶስ ከሰባኪነትና ከተናጋሪነት በፊት የተለወጠ ማንነትን ይሻል፤ በዜማ፣ በግጥም … ከማገልገል በፊት ራስንና ሁለንተናን ለእግዚአብሔር መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር ከአገልግሎት፣ ከመሥዋዕት… በፊት የተለወጠና በልጁ ደም የታጠበ ቅዱስ ሕይወትን ይሻል፡፡ ይህንን ሳናደርግ ግን ደርሰን “በዜማና በድምጽ፣ በግጥም ብገለግልስ?” ብንል፣ የማያመቻምቸው ቃሉ በግልጥ፣ “በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል፡፡ የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ፤” (ማቴ.7፥22-23) ይላል፡፡
     በእውነት፣ እግዚአብሔር የሚወደውን ግብረ ገብነት ያለበትን ዜማና ግጥም “በዘፈን” ማገልገል የምንፈልግ ሁላችንም፣ የግብረ ገብነት መለኪያው ክርስቶስ እጅ እንጂ እኛ ዘንድ አይደለምና፣ ለመገፋፋትና ለመሰባበር ካልሆነ በቀር ጋሪና ፈረሱን ማቀዳዱ አይረባንም፡፡

የወደቀው መልአክ የነበረውን ጸጋ ለክፉ አዋለው!

     ሰይጣን በፍጥረቱ ከጥንት ቅዱስ ነበር፤ በኢሳ.14፥12 ላይ “የአጥቢያ ኮከብ” የሚለው ቃል፣ ከዕብራይስጥ ወደሮማይስጥ ሲመለስ “ሉሲፈር” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ይህም የነበረውንና በፍጥረት መጀመርያ በክብሩ ታላቅ መሆኑን ያሳያል፡፡ ነገር ግን በትዕቢቱ ተነፍቶ በራሱ ወደቀ፤ (1ጢሞ.3፥6)፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ በመቃወም የራሱን መንግሥት ለማጽናትና ለማቋቋም ይታትራል፡፡
    ስለዚህም የተሰጠውን መልካሙን ክብርና ጸጋ ሙሉ ለሙሉ ለክፋት አውሎታል ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ከሌሎች መላዕክት ጋር በመሆን ለእግዚአብሔር ፈጣሪው ምስጋናን አቅራቢና አምልኮ አምጪ የነበረው ፍጡር፣ አሁን ግን “ልክ እንደእግዚአብሔር” አምልኮንና ውዳሴን መቀበልና መመለክን ይፈልጋል፡፡ አምልኮን ለመቀበልና ውዳሴን ለራሱ ሊጠቀልል ከሚፈልግበት መንገድ አንዱ ደግሞ ዘፈን ነው፡፡
    በዘፈን ምን ያህል ስውርና ውስብስብ ነገሮች እንደሚሠሩበት የምናስተውለው፣ ለእያንዳንዱ የክፋት መገለጫ ዜማዎችና ድምጸቶች ተሠርተው መታየታቸውን ስናስተውል ነው፡፡ ሰይጣን የተሰጠውን ክብርና ጥበብ ሙሉ ለሙሉ ለክፋት ስላዋለው ከሁሉም ኮሞሳዊ ዘፈኖች ጀርባ ሆኖ፣ ራሱን ሰውሮ  ክብርና ምስጋናን ይቀበላል፡፡ ስለጾታዊ ፍቅር፣ ስለምድራዊው ባለጠግነት፣ ስለመልክና ቁመና፣ … በሩዋንዳ እንደተፈጸመው አይነት ደግሞ ሰዎች ሰዎችን በጭካኔ መልኩ እንዲገድሉ ለሚያደርግ ሥራ ዘፈን የጎላ ሚናና ሰይጣናዊ ሥራን ከማስቸኮሉም ባሻገር በግፍ ደም ያጨቀያል፡፡
   መቼም ሁላችን ከክርስቶስ ጋር በትክክል ቆመን ቢሆን ኖሮ፣ ራሱ ክርስቶስ እንጂ ሌላ የሚያረካንን ፍለጋ ባልተንከራተትን ነበር፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ የረካ እርሱ፣ በጸጋው እንኳ አይረካም፡፡ ጸጋው እንኳ ከሠጪው ከራሱ ፍጹም ያንሳልና፡፡ ሰይጣን ይህን መንገድ በሚገባ ያውቀዋል፤ ስለዚህም ከክርስቶስ ዓይናችንን ዘወር በማድረግ በሰው ጥበብና ድምጸት ላይ በማተኮር እንድንከፋፈል ትልቅ የቤት ሥራን ሰጥቶናል፡፡ ብናስተውል፣ መዝሙርን እንኳ ለጌታ ክብር በመሰጠት ልንዘምር እንጂ፣ የዘማሪውን ቅላጼና የዜማ ስልት፣ አሸባሸቡን … በማየት በማድነቅ ልባችንን ከግርማው ዙፋን ፊት እንዳናርቅ እጅግ መጠንቀቅ ይገባን ነበር፡፡
      ዘፈንን እየሰሙ የሚያለቅሱ፣ በዘፈን ኮንሰርቶች ላይ ከዘፈን የተነሳ ራሳቸውን ስተው በቃሬዛ ተጭነው የሚወጡ፣ ከፈንጠዝያው የተነሳ ለያዥ ለገላጋይ የሚያስቸግሩትን … ስናይ ሰይጣን በዘፈን ውስጥ የሰወረው የክፋት ስንግ አደገኛነቱ ጎልቶ መታየት ካልቻለን በእርግጥ በፈቃዳችን ራሳችንን አሳውረናል ማለት ነው፡፡ ሁሉም ዘፋኞች ብሎ መድፈር በሚያስችል አቋም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባልነበሩበት ወይም መሆን ባልፈለጉበት ጊዜ ዘፈንን ዘፍነዋል፣ እየዘፈኑም ነው፤ እያዘፈኑም ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ካልነበሩ ደግሞ ከማን ጋር እንደነበሩ ግልጥና ሦስተኛ ምርጫ የሌለበት እውነት ነው፡፡ ከሰይጣን ጋር ነበሩ!!!
ማጠቃለያ
      በሦስቱም ጥቅሶች ውስጥ ዘፈን የተጠቀሰው ከሌሎች ርኩሰቶች ጋር በዝርዝር ነው፡፡ ይህ በግልጥ የሚነግረን ዘፈን አድራሻው ወይም መገኛው ከኃጢአት መንደር እንደሆነ ነው፡፡ በግልጥ ቃል ዘፈንን ከጽድቅ ጋር ለማዋደድ ማሰብ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅን እንደማኖር ያለ ከንቱ ጥረት ነው፤ በፍጹም መጋጠም አይቻላቸውምና፡፡
    በዘመናት ታሪክ፣ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ሃሳብ ስትጥል፣ አንድ “የማይጠቅም” እና ታናሽ ነገር እንደምታነሳ አስተውለናል፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ያው ነው፤ በኃጢአት ለረከሰው ዓለም ከክርስቶስ ደምና ከመንፈስ ቅዱስ ብርሃንነት የተነሳ በትክክል ማብራት ቢሳነን፣ “አሮጌውን ዘፈንን በአዲሱ የጽድቅ አቁማዳ” ላይ ልንለጥፍ ተነሳን፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ያውቃል፤ ስለዚህም ዘፈንን ኃጢአት ለማለት ምስክርነታችን ልምሾ አይሁን፡፡ ዘፈን ከነማን ጋር መጠቀሱን ካስተዋልን፣ መንደሩንም በትክክል ከለየን፣ …. አዲስ ጎጆ ቀልሰን ከቅዱሱ መዝሙር ጋር ልናጎራብተው አንዳዳ፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፤ አሜን፡፡

ተፈጸመ፡፡ 

2 comments:

  1. መቼም ሁላችን ከክርስቶስ ጋር በትክክል ቆመን ቢሆን ኖሮ፣ ራሱ ክርስቶስ እንጂ ሌላ የሚያረካንን ፍለጋ ባልተንከራተትን ነበር፡፡ smart article berta wendme Geta tsegwn yabzlh ... kale hiwot yasemah

    ReplyDelete
  2. Hi there i am kavin, its my first occasion to commenting anyplace, when i read this article i thought i could
    also make comment due to this sensible post.

    ReplyDelete