Friday 23 October 2015

የፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ንግግር ሳጤነው ምጥ አለበት!!!


ብዙዎች ያልጨከንለትና ያልደፈርንለት እውነት!!!

      በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተካሄደው 34  መደበኛ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ፥ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥቅምት 8 ቀን  2008 ዓ.ም ካስተላለፉት አባታዊ መልዕክት የሚከተለው መልዕክት ላይ ማተኮር ፈለግሁ፡፡
 
“ … የምዕመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምስጢር ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ልታጤነው ይገባል ፤ በዚህ ዙርያ የሚታየው ክፍተት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መግቻ ካላበጀንለት ነገ ከባድ የሃይማኖትና የታሪክ ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ልብ እንበል፡፡
     ለመሆኑ ምዕመናን ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ  ወደሌላ ካምብ ለመግባት ለምን መረጡ?
-       የሚያስተምራቸውን ካህን አጥተው ነውን?
-       የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት ነው?
-       የቤተ ክርስቲያችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነውን?
-       የካህን እጥረት ስላለ ነውን?
-       ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው፤?
የዚህ ሁሉ መልስ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ቁልጭ ብሎ ስለሚታወቅ የጥያቄው መልስ ለእናንተው ሰጥተናል፡፡  … ”

     ደግሞም ልቀጥል፦ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መጀመርን አስመልክቶ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም  ቅዱስነታቸው በሰጡትም መግለጫም እንዲህ አሉ፦


        “ … ለሰብዑ አብያተ ክርስቲያናት ዘእስያና ለአለቆቻቸው የተነገረው ሁሉ ዛሬ ያለችው  ቤተ ክርስቲያንና አለቆቿን ጭምር በቀጥታ የሚመለከት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከአለቆች መካከል የተመሰገኑም ፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙም ፣ እንደዚሁም ጠንከር ያለ ተግሣጽ የደረሰባቸው እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ በየትኛውም ዘመን  ፣ በየትኛውም ቦታ ፣ ክፍተት አይፈጠርም ብሎ በሙሉ ኃላፊነት መውሰድ የሚችል ይገኛል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን የከፋና የባሰ ክፍተት እንዳይፈጠር የተናጠከረ ሥራ በመሥራት መከላከል የሚችሉ በየጊዜው ሁሉ የተነሡ ታላላቅ አበው እንዳሉ እናስተውላለን፡፡ በዚህ ዘመን የምንገኝ ኖሎትም ምንም ቢሆን ከዚህ እውነታ ውጭ መሆን አንችልም ፤ …”


         ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ልብ ውስጥ ያለች የዘላለም ሃሳቡና ዕቅዱ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለእግዚአብሔር ሕልው ሆና በሕያውነት መኖር አትችልም ፤ ለዘወትርም “ … እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ” የዕለት የዕለት በጐ መሻቱ ነው፡፡(ኤፌ.5፥27) ስለዚህም ከእርሱ የተነሳ ሕያው ናትና ፤ ታድጋለች ፤ ትለመልማለች ፤ ሕያዋን የሆኑ ነፍሳትንም ትጨምራለች፡፡ (ሐዋ.2፥41 ፤  4፥4 ፤ 6፥1 ፤ 7 ፤ 9፥31 ፤ 42 ፤ 12፥24) 
     
 
     የቅዱስ ፓትርያርኩ ንግግር ይህን በማሰብና በመናፈቅ ይመስል ነበርና ፥ ከልብ ለሰማው እጅግ ልብ የሚነካ ፤ ጩኸቱ ከሩቅ የሚሰማ ምጠት አለው፡፡ ለእውነተኛ እረኛ በጐቹ ሲቅበዘበዙ ፤ ተበትነው በዱርና በምድረ በዳ ፤ በፍርክታና በዋሻ ተበታትነው ሲርመሰመሱ ፤ “ሙሉ ነገራቸው” ለጠላት ተላልፎ እንደመሰጠት ያለ ልብን የሚሰብር ፤ አቅልን የሚበትን ብርቱ ነገር የለም፡፡ ለዘመናት  ቤተ ክርስቲያን በጐቿን በገዛ እጇ መበተኗን ላለማመን፥ ብዙ ምክንያቶችን ስትደረድር ኖራለች ወይም ደግሞ “ከጐጆ ላይ አንዲት ሳር ብትመዘዝ ጐጆ አያፈስም” በሚል “ከንቱ ትምክህት” ፤ በሰነፍ ልጆቿ “መዝሙር” ተከባ ኖራለች፡፡ ይህንን መዝሙር  ሲዘምሩ የነበሩቱ ዛሬ ማፈር ያለባቸው ጊዜ ነው ብንል ግነት አለበት አያስብልም፡፡
     በጐች ማሪፊያ አጥተው ሲንከራተቱ ፤ ተርበው አንጀታቸው ሲታጠፍ ፤ ተጠምተው አፋቸው ሲደርቅ ፤ መንፈሳቸው ጭው ባለ የክህደት ምድረ በዳ ላይ ሲንቀዋለል፥ ሰባኪዎቻችንና ዘማሪዎቻችን ፤ እንዲሁም የሚበዙቱ የአድባራትና የገዳም አስተዳዳሪዎቻችን እንደጐበዝ አለቃ በቡድን ተከፋፍለው በአድመኝነት መንፈስ መገፋፋቱን እንደሥራ ፤ ሃብት ማጋበስንና ቅምጥለትን እንደጀብዱነት ተያይዘውት፥ የአንዲቱ ሳር መመዘዝ ሳያሳስባቸው ኖረዋል ፤ አሁንም አሉ፡፡ በዚህ ሳያበቃ በሚያማምሩ የመጻህፍትና የአማርኛ ቅንብሮች ጀርባ ማጭበርበርና ዘረፋ ፤ ከጉባኤያትና ከአገልግሎት ጀርባ ግብረ ሰዶማዊነት ፤ ከጠበልና ከቤት ለቤት አገልግሎት ጀርባ ጥንቆላና አይን ያወጣ ሴሰኝነትና አመንዝራትን እንጂ ማን ይሆን ስለቤተ ክርስቲያን ማደግና መለምለም እጅግ እየተጨነቀ ያለው? የሚል ቱባ ጥያቄ ያነሳ ሲወገዝና ሲገፋም እያየን ነው፡፡
  
  
  አንድ ነገር ግን እናስተውል፦ ከአንዲት ጐጆ ላይ የተመዘዙት ሳሮች፥ ዛሬ አንዲት ሳር የሚባሉ አይደሉም ፤ እኒያ እልፍ ሳሮች ዛሬ ገመናችንን አሳይተዋል ፤ ድካማችንን ገልጠዋል ፤ ብዙ አንድ አማኞች ለብዙ ሕዝብ ምንም ግድ እንደሌለን በትክክል አሳብቀዋል ፤ ብዙ ያለን እየመሰለን ስንመካ ብዙ ከሚባለው በላይ አጥተናል ፤ ካተረፍነው ይልቅ ስለከሰርነው ከልብ ላለመነጋገር ብንደባበቅም፥ እውነታውን ግን ወዴትም መገፍተር አልተቻለንም ፤ ሚሊየኖች የት ናቸው? እኒያ እንደዋዛ የታዩት ትናንሽ አንድ አንድ ሳሮች የት ናቸው? ምክንያትና ሰበብ ይኖረን ይሆን?  የእግዚአብሔር ይቆየን … በታሪክ ፊት ከመጠየቅ ያድነን ይሆን? ነው ወይስ ዛሬም “አብ ያልተከለው ተክል ይነቀላል” እያልን ከአውዱ ጋር የማገጥም ጥቅስ በማስጨነቅ እየተረጐምን ነው?!
     ለዘመናት ዕድሜያችንን ያነቀዘውና ያቀጨጨን ነገር፥ ሁለንተናዊ ችግር አለብን ለማለት አለመቻላችን ነው፡፡ “ሙሉ ነን ፣ አልተሳሳትንም ፤ ልንሳሳትም አንችልም ፣ ቀደምት ጥንታውያን ነን ፣ ብቸኞች ነን ፣ እኛን የሚመስል የሚተካከለንም የለም” እያልን ለዘመናት ኖረናል ፤ እውነታው ግን ይህን አያሳይም ፤ በብዙ ነገር የአለሙም የክርስትናውም ጅራት ሆነናል ፤ ለዚህም ነው፦  እንኳን በቤተ መንግሥቱ፥ በቤተ ክህነቱ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ያልቻልነው! ለዚህም ነው፦ እንኳን ከመንግሥታዊ ቢሮዎች ስግብግብነትንና ጉበኝነትን ልናስወጣ፥ ከመንፈሳውያን አደባባዮቻችን በድፍረት “ነውር ነው” ማለት የተሳነን! ለዚህም ነው፦ የሌላውን ድካምና ኃጢአት ቀኑን ሙሉ በማውራት ሳንሰለች ለቅጽበት ግን “እኔም ትውልዴም ፤ የአባቴም ቤት ጭምር በድለናል ፤ ኃጢአትንም ሠርተናል” በማለት ከንስሐ የዘገየን ትምክህተኞች የሆንነው! ለዚህም ነው፦ በገጠርና በከተማ አፋፍ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉና ምዕመናን ወደሌሎች አብያተ ክርስቲያናትና ወደአህዛብ መንደር እየፈለሱ ፤ ጀርባቸውንም ለቤተ ከርስቲያን ሰጥተው ወደዓለማዊነት ሲጐርፉ እኛ ግን “በአልሞትንምና በአንሞትም” ሽለላና ቀረርቶ ላይ ያለነው! 
   ብጹዕ አባታችን እንዳሉት፦ አዎ! በብዙ አድባራትና ገዳማት ላይ ወንጌል የታጠቁ ፥ በሕይወትም ጭምር የሚሰብኩ ካህናት የሉንም፡፡  የእልፍ አዕላፍ ካህናት ገመና ለማወቅ ብዙም ጥናታዊ ጽሁፍ ሳያስፈልግ ዙርያችንን ማየትና ማስተዋል በቂ ነው፡፡ አዎ! ትምህርተ ሃይማኖታችንም ክፍተት እንዳለው እያሳየ ነው ፤ ብዙ የሚያስነቅፉ “ድሪቶዎችም” እየተለጣጠፉበት ነው፡፡  “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም!” ፤ “ክርስቶስ የተዋሃደው ሥጋ፥ ድንግል ማርያም የፈጠረችውን ሥጋ ነው” ፤ “እንደክርስቶስ፥ ቅዱሳንም የአለም ቤዛ መባል(መሆን) ይችላሉ” ፤ “ምድር ገና ስትፈጠር(እንደተፈጠረች) እርሷም እንደሰው ጥምቀትን ተጠምቃለች” … የሚሉና ሌሎች አስነዋሪ ትምህርቶች በአውደ ምህረቶቻችን ማስተጋባት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አዎ! ትምህርተ ሃይማኖታችን ክፍተት ማሳየቱን ልንክድ አንችልም፡፡
    አዎ! የቤተ ክርስቲያችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነው! ለመሆኑ አስተዳደራችን የበጐ ምላሽ ምች መትቶት ከቆሰለ አልሰነበተምን ፤ ቁስሉስ አልሸተተምን?! በዚህ ጉዳይ አለማውያን መሪዎችና ጸሐፍት ጭምር አልታዘቡንምን? አንድ ዲያቆን ቢበደል ሊቀ ጳጳሱን ሊያገኝ ምን ያህል ጊዜ ይወስድበታል? የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በተለያየ ጊዜ እንዲህ ያሉ ገጠመኞችን አስተናግዷል፡፡ ወደሊቀ ጳጳሱ የሚያስገቡ “እልፍኝ አስከልካዮች” ከሌሉ በቀር፥ የጳጳስን ፊት ማየት ሕልም ነው! እንኪያስ መልካም አስተዳደራችን ወዴት ነው?
      የካህን እጥረት ግን አለ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ ፤ በአዲስ አበባና በታላላቅ አድባራትና ገዳማት ያሉት ካህናትና መነኰሳት የተቀማጠለ ኑሮአቸውን ተወት አድርገው ፤ እንደጌታ ደቀ መዛሙርት በአጭር ታጥቀው ፤ ወንጌሉን ከልብ ሊመሰክሩ ቢነሱ፥ ለምሥራቅ አፍሪካ የማይትረፈረፉበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ መናገሩንና መተንነተኑን ፈርተን እንጂ ችግራችን ምንና ማን ዘንድ እንዳለ በሚገባ እናውቃለን ፤ ዳሩ ግን ከለመድነው ልማድ ለመውጣት በመጀመርያ የምንፈራው፥ ልማድ እንደባርያ እየገዛው ያለውን ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ደፍረን ብንናገር ሊሆን ያለውንና ሊመጣ ያለውን መከራ ፈርተን ዝም ብለናል፡፡ ዋዘኞችና ወንጌልን ሳይሆን የአሮጊትን ተረት በመተረት በከንቱ የሚለፈልፉቱ ግን እንደአዝማሪ የሕዝቡን ስሜት እየኰረኰሩ ሲላቸው ያስቁታል ፤ ሲብስ ያስለቅሱታል፡፡
     እውነት ለመናገር ብዙዎቻችን በየመድረኩና በየአውደ ምሕረቱ የምናስተምረውን ከልባችን አናምነውም ፤ አንዳንዶች ወንጌልን እንደሥራ የያዝነው ለሆዳችን ነውና፥ ከደመወዝ ላለመፈናቀል እንደሰው ልማድ ያለውን እንጂ ወንጌልን አንሰብክም ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለዝና ለክብራችን እንጂ ለወንጌሉ ግድም የለን ፤ እጅግ የምንበዛው ደግሞ ከቤተ ሰብ ፣ ከማህበራዊ ሕይወት ፣ ከማህበረሰቡ ፣ ከምንወዳቸው ወንድሞችና ባልንጀሮቻችን ፣ በትዳራችን ላይ ይደቀናል ብለን ከምንፈራው ብርቱ ፍርሃት የተነሳ ወንጌልን ለመስበክ መንቀጥቀጥ የያዘን ነን፡፡
      እንግዲህ ብጹዕነታቸው የተናገሩት ይህን ነው ፤ በልባችን የተገለጠውን ያንን እውነት ለመናገር አለመድፈራችን፡፡ ለመሸነጋገልና ለመደባበቅ ፤ በከንቱ ትዕቢት ለመታጀል ካልፈለግን በቀር ችግሩን አለማወቃችንና ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናችን ብቻ ሳይሆን ፥ ችግሩን አውቀን መፍትሔውን ለመናገር አለመቻላችን ዋና ችግራችንም ነው፡፡
      እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ለሚወዱ የሥራው ጊዜ ፤ የተወደደውም ሰዓት አሁን ነው፡፡ አባታችን እንዳሉት፦ የዚህ ሁሉ ችግር የመጀመርያውም የመጨረሻውም ድንቅ መፍትሔ “ምዕመናንን የመጠበቅ ተልዕኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሳ” እጅግ የተወደደ ነው፡፡ አልያ ግን “የጥንት ነን ፤ ፊተኞች ነን ፤ ከእኛም ወዲያ ላሣር” የሚለው ባዶ ትምክህት ባዶአችንን እንዳያስቀረን ለራሳችን መፍራት ይገባናል፡፡ በየጓዲያው እየተብሰከሰክን ማውራት ፤ ችግሩን እያወቁ፥ መፍትሔውንም እያስተዋሉ ዝም ብሎ መቀመጥ ጊዜው አይደለም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ትውፊትና ለዛ ላይ ቆመን ለመነጋገር መወሰን ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ አልያ ግን ይህን ባናደርግ ኃጢአትንና ቅድስናን ፤ ቅዱስ ጋብቻንና ግብረ ሰዶማዊነትን ለሚያዳቅል እንግዳ ትውልድ አስረክበን እንዳንዋረድ፥ በሰማይም በምድርም ፊት ንስሐ ገብተን መመለስ ይገባናል፡፡
     ቅዱስ ወንጌል መሠረት ነው! ወንጌል የቅድስና ሁሉ ምንጭ ነው ! ወንጌል አደላዳይ ነው! ወንጌል ያለንበትን ፤ የኖርንበትን ፤ እንኖርበት ዘንድ የሚገባንን እውነተኛውን ነገር የሚነግረን ቅዱስና ፍጹም ባልንጀራ ነው!!! እንኪያስ! ይህ ወንጌል ባለበት አርነት አለ፡፡ ወንጌል በመካከላችን ከሰለጠነ ትምህርተ ሃይማኖታችን ከዚያ ይቀዳል ፤ መልካም አስተዳደራችን ከዚያ ይመነጫል ፤ በጥቂት ሠራዊት እልፉን ድል ማድረግ የዚያኔ በአምላካችን ፊት ቀላል እንደሆነች፥ በእኛም ዘንድ እጅግ ትቀላለች፡፡
     አዎ! ወንጌላውያን አማርኛ ትተን ወንጌሉን አጥርተን እንስበክ ፤ ምዕመናንም ቅዱሱን ወንጌል ከልብ በመጠማት እንስማ፡፡ ጌታ ይህን ልብ ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

6 comments:

  1. አታጭበርብር
    "...አዎ! ትምህርተ ሃይማኖታችንም ክፍተት እንዳለው እያሳየ ነው ፤ ብዙ የሚያስነቅፉ “ድሪቶዎችም” እየተለጣጠፉበት ነው፡፡ “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም!” ፤ “ክርስቶስ የተዋሃደው ሥጋ፥ ድንግል ማርያም የፈጠረችውን ሥጋ ነው” ፤ “እንደክርስቶስ፥ ቅዱሳንም የአለም ቤዛ መባል(መሆን) ይችላሉ” ፤ “ምድር ገና ስትፈጠር(እንደተፈጠረች) እርሷም እንደሰው ጥምቀትን ተጠምቃለች” … " ደግሞ ብላችሁ በዚህ መጣችሁ የቤተክርስቲያንን ምዕመናን ቁጥር ካሳነሱት መካከል የአንተ አይነቱ ተሃድሶ ምንደኞች የዋህ ምዕመናንን በማስኮብለላቸውና ምዕመኑ ትምህርተ ሃይማኖትን ረስቶ በጥራዝ ነጠቅ ስብከት በማደንቆራችሁ መሆኑን አትዘንጋ ኦርቶዶክስ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ሰጥታለች! አታጭበርብር ቤ/ክ የአስተምህሮ ክፍተት የለባትም!!!

    ReplyDelete
  2. አጭበርባሪ መናፍቅ ጅብ የማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንዳለው ነህ ሁሉም ፕሮፋይልህን ያውቀዋል በደ/ል/ቅ/ጊዮርጊስ ሰ/ትቤትና ቅ/ኪዳነ መህረት ት/ቤት ወጣቶችን ለመናፍቃን ስትመለምል እንደነበረ እናውቃለን ስለዚህ ረፍዶብሃል ወደ ላኩህ ዘንድ ተመለስ

    ReplyDelete
  3. ምንድነው ተሀድሶ የወሬ ማጣፈጫ ፣ ማስደንበሪያ፣ማሸማቀቂያ ራስህ በፈጠርከው ባልተባለ ነገር ትደብናለህ ያልተባለና በምናብህ በፈጠርከው ተሀድሶ ወሬው ሁሉ ተሀድሶ እንዲሆን ትፈልጋለህ አሁን ምን አመጣው ተሀድሶን እዚህ ውስጥ የአድመኝነት መንፈስ ሲለሚጋልብህ ቅዠት ይሁንብህ እግዚብሄር ሆይ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ሀይማኖትን ጠብቅልን ከአድመኛና ከፋፋይን አስተግስልን አሜን!!!!!!

    ReplyDelete