Tuesday 13 October 2015

አድመኝነት - ከማን የተማርነው ነው?



      
                                   Please read in PDF
            

   ጌታ ኢየሱስ በተያዘባት በሐሙስ ማታው ግርግር፥ ደቀ መዛሙርት አይሁድ ጌታን ቆርጠው ለመግደል በብዙ ጦርና አድማ ተደራጅተው ምክራቸውን እንደጨረሱ ሲያውቁ ፦ “ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት።” (ሉቃ.22፥38) የአይሁድ የካህናት አለቆች ሙሉ ለሙሉ በአድማ ሲነሳሱ ስላዩ፥ ደቀ መዛሙርቱም ምላሽ ለመስጠት በሰይፍ ለሚያስታጥቅ አድማ ለራሳቸው ተዘጋጁ፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንዳያደርጉት በምፀት ቃል “ይበቃል” ቢላቸውም፥ እነርሱ ግን ቃል በቃል ተርጉመው፥ አድማቸውን ወደጥቃት አሸጋግረው የአንዱን ወታደር ጆሮ በመቁረጥ ደመደሙ፡፡ ጌታ ግን “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።” በማለት በተግሳጽ ቃል ተናገረ፡፡ (ማቴ.26፥52)
     ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ከእነርሱ ጋር የተስማማ መስሏቸው ይህን ቢያደርጉም፥ ጌታ ግን ድርጊቱን አብዝቶ ተጠይፏል፡፡ በእርግጥም አድመኝነት የሥጋ ፍሬ ነው ፤ (ገላ.5፥20) ትርጉሙንም ስናሰላስለው ለመለያየት የመጀመርያ ምልክት የሆነ ፤ የግል መሻትና ፍላጎት ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጠር መለያየት ፤ በፍጻሜም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚያጠፋ  ወይም የሚቃወም ድርጊት ነው፡፡ ይህም በአንድ ሃሳብ የሚስማሙና የግል ሃሳባቸውን የሚያስቀድሙ ሰዎች ወገናዊነትን ፤ እኛዊነትን ፤ እኔዊነትን በመፍጠር ፥ በሌላው ላይ በማሾክሾክ ፤ በማማት ፤ በመጥላትም ጭምር ራሳቸውን በማግለል ቡድናዊነትን በመመሥረት በሌላው ላይ የበላይነትን ለማሳየት የሚያደርጉት ድርጊት ነው፡

     በአድመኝነት ኃጢአት ተይዛ ከነበረችው ቤተ ክርስቲያን አንዷ፥ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ (1ቆሮ.1፥11 ፤ 11፥18 ፤ 2ቆሮ.12፥20)  በአድመኝነት መገኘት ማለት እግዚአብሔርና የታመኑ የእግዚአብሔር ቅዱሳን እንደሚፈልጉብን ወይም እንደሚጠብቁን እየኖርን አለመሆናችንን ነው፡፡ እግዚአብሔር ከምንም በላይ ቅዱስ ሕብረትን ይፈልጋል ፤ ከመጀመርያውም፦ “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።” (ዘጸ.25፥8) ፤ “በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ።” (ዘሌዋ.26፥12) ፤ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና” (ሉቃ.17፥21) እንዲል ከመጀመርያው ሕብረትን የፈለገውና ከእኛ ጋር ሊሆን የወደደው እርሱ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
      እርሱ ሕብረት ወዳድ አምላክ ስለሆነም በራሱ መልክና አምሳል ፈጥሮናል፡፡ ሕብረት ማድረግና መገዛት ለሰው ልጆች የተፈጥሮ ባሕርያችን ነው፡፡ የነፍሳችን መልክ ሕብረትን በማድረግ የእግዚአብሔርን መልክ ይመስላልና፥ ከሚያምነው ባልንጀራችን ጋር ቃሉን ለመጨዋወት ፣ አብሮ ለመዘመር ፣ አብሮ ለማምለክ ፣ በቅዳሴና በውዳሴ ለመሳተፍ ፣ በሕብረትም ለመቀመጥ ውበታችን የእግዚአብሔር መልክና ደም ግባት ነው፡፡ (መዝ.133፥1) ሰው ሕብረቱን ከእግዚአብሔር ጋር የማድረግና ፍጹም የመጠማትን ነገር በነፍሱ ሰሌዳ ላይ እግዚአብሔር አትሞበታል ፤ ስለዚህ ሰው ከእግዚአብሔርም ፤ ከሰውም ጋር ሕብረትን ለማድረግ ከጥንቱ የተፈጠረ ነው ማለት ይቻለናል፡፡ ለዚህ ባይገዛ እግዚአብሔር ለማይረባና ለማይታዘዝ አዕምሮ ይተወዋል፡፡ (ሮሜ.1፥28)
      ሰው ለማይረባ አእምሮ ተላልፎ ከተሰጠ ሕብረቱን ከእግዚአብሔር ጋር ሙሉ ለሙሉ በማቋረጥ ወደሥጋ ሥራ ይሰማራል፡፡ እንግዲህ አድመኝነት እንዲህ ካለው መዝገብ የሚወጣ ፤ እንዲህ ካለውም እርሻ የሚበቅል ተክል ነው፡፡ ማደም ራስን ወይም የራስን ቡድን ትክክል ነው በማለት ሌላውን ወገን መኰነን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መገለጫዎቹ እማኝ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መገለጫዎቹ፦
1.     ሾክሾክ ፦ ሐሜትን በግለጥ ከመጀመር በፊት ማሾክሾክ የተለመደ ነገር ነው፡፡ የሚያሾከሽኩ ሰዎች ራሳቸውን ማየት የተሳናቸው ሰዎች ናቸው፡፡ “አቤቱ፥ መርምረኝ ልቤንም እወቅ ፍተነኝ መንገዴንም እወቅ ፤ በደልንም በእኔ ውስጥ ብታገኝ እይ የዘላለምንም መንገድ ምራኝ።” (መዝ.139፥23-24) የሚለውን የመዝሙረኛውን ቃል የዘነጉ ሰዎች ናቸው፡፡ አሮንና ማርያም በአንድ ወቅት በሙሴ ላይ ማንሾካሸካቸውን እግዚአብሔር ሰምቶ ነበር፡፡ ሰምቶ ግን ዝም አላለም ፤ ቀጣቸው እንጂ፡፡ (ዘኊል.12፥1-15)
     በባልንጀራችን ላይ በክፋት የምናሾካሽከውን የቀስታ ሹክሽክታ እግዚአብሔር ይሰማል፡፡ ሰምቶ ግን ዝም የሚል እንዳይመስለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ጊዜ የሚያንሾካሽኩ ሰዎች ስምን በሰገነት ጮኾ የማንሳት ያህል እንደሚሰማ አለማስተዋላቸው ነው፡፡
2.    ሜት ፦ የአድመኞች ልዩና ትልቁ ባሕርያቸው እጅግ የሚጠሉትንና የሚያድሙበትን ቡድን አብዝተው በማማት ይታወቃሉ፡፡ ማሾክሾክም ፤ ማማትም ሁለቱም የአንደበት ኃጢአቶች ናቸው፡፡ ራስን አክብሮ ባልንጀራን ለማዋረድ ፤ ክብሩን ለመንካትና ሞራሉን ለማንቋሸሽ ከሚፈጸሙት ድርጊቶች አንዱ ሐሜት ነው፡፡
    “ሐሜትን የሚገልጥ ሰነፍ ነው።” (ምሳ.10፥18) ሐሜተኞች የሥራ ጊዜያቸውን የማይረባ ወሬ በማውራት ያሳልፋሉና ሰነፎች ናቸው፡፡ በየሆቴሉ ፣ በየካፍቴሪያው ፣ በየመዝናኛ ሥፍራው ፣ በየቤተ ክርስቲያኑ ፣ ለስብከትና ለዝማሬ አውደ ምሕረት ላይ ተቀምጠውም እንኳ ሥራቸው ሐሜት ፤ የባልንጀራቸውን ስም ማጠልሸት ነው፡፡ አይሁድ ክፉ ልብ ስለነበራቸው የጌታን ሥራ በሐሜት ተቃውመው ለሁሉ በጥላቻ አወሩት፡፡ ግና እርሱ ካወሩበት መጠን በላይ በክብር ከፍ ከፍ አለ፡፡
3.   ጣ የተመሉ ናቸው ፦ በባለፈው ሳምንት በሻሸመኔ ከተማ “በአንድ አለቃ እንተዳደር” እና “ልንተዳደር አይገባንም” በሚሉ አድመኞች መካከል በተነሳ ቅራኔ መካከል ብዙዎች የተደበደቡና የቆሰሉ ቢሆኑም፥ አንድ ሰው ግን ክፉኛ ተጎድቶ ሆስፒታል መግባቱን ሰምተናል፡፡ አስተውሉ! የሚደበድቡትም ፤ የሚያቆስሉትም አድመኞች ራሳቸውን እየቆጠሩ ያሉት እንደእግዚአብሔር አገልጋይ ነው ፡፡
    በቅርቡ ደግሞ የተደራጁና ራሳቸውን ለሃይማኖት ቀናተኛ አድርገው ያቀረቡ “ልዩ ወገኖች”፥ የቤተ ክርስቲያንን አገልጋዮችና ዘማሪዎችን ለመደብደብ ፣ ለማቁሰል ፣ ከመድረክ በግድ ለማውረድ ፣ ለመግደልም ጭምር … መሐላ ተግባብተው በአድመኝነት ቁጣ ተመልተው ተነስተዋል፡፡ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ” (ማቴ.5፥44-45) “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” (ሮሜ.12፥21) የሚለው ቃል ፍጹም ተረስቷል፡፡ እንኳን “ለጠላት”፥ እግዚአብሔርን እንደእኛው ለሚያመልክ ወንድም የሚራራ ልብ ማጣታችን እንዴት ያሳዝናል፡፡
    ደቀ መዛሙርቱ ወደተሰሎንቄ መጥተው ወንጌል ሰብከው፥ ብዙዎችን ባሳመኑ ጊዜ “አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥” (ሐዋ.17፥5) ይለናል፡፡ ዲያብሎስም ከሰማያት በተጣለ ጊዜ  እጅግ ተቆጥቷል፡፡ (ራእ.12፥17) በባልንጀራችን ላይ ለመቆጣት የምንነሳ ሰዎች እንደዲያብሎስ ተሸንፈን ላለመሆናችን ምንም እማኝ ማቅረብ አንችልም፡፡ አዎ! የተቆጣነውና ፊታችንን አጥቁረን የቆምነው ተሸንፈንና ተበልጠን ነው እንጂ፥ ባንሸነፍና ባንበለጥ አንዳች የሚያስቀናንም ፤ የሚያስቆጣንም ነገር ባልኖረ ነበር፡፡ በእውኑ በምን መርሕ ይሆን የሌላውን ሰው ደም ለማፍሰስ የምንቆጣው? ወንጌል ትላለችን? ኦሪት እንኳ የበደለህን እንጂ አይንህን ያላወጣውን አይኑን አውጣ አትልም፡፡ ታዲያ ከየት ተማርነው ፤ ከወዴትስ አገኘነው?
4.   ጋዊ ጥቃትን ይፈጽማሉ፦ አድመኞች በቁጣ ከተማ ብቻ አያውኩም ፤ ከመደብደብ ፣ ሥጋን ከመጉዳትና ከመግደልም አይመለሱም፡፡ የትላንት አማኝ ደቀ መዛሙርት ክርስትናን በፍቅርና በመታዘዝ እየሞቱ ፤ በምስክርነትም ሰማዕት ሆኑ ፤ የዛሬዎቹ ግን ከጌታና ከወንጌል መማርን አልፈለጉምና፥ በመግደል “አማኝነታቸውን” ሊያረጋግጡ ወደዱ፡፡ በእርግጥ እኒህ ሰዎች ክፋትና ገንዘብ መውደድ በሌለበት ልብ ለወንጌልና ለቅድስና ብቻ ቀንተው ይህን ቢያደርጉ፥ እንደቅዱስ ጳውሎስ የመመለስ እድል አላቸው ፤ ነገር ግን ይህን የሚያደርጉት ገንዘብን ስለመውደድና ሌላውን ለመጉዳት እጅግ ከማሰብ የተነሳ ነውና ከባድ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡
      ከዚህ የተነሳ ውስጤ የሚመላለስ ጥያቄ አለ ፤ መደብደብ ፤ ባልንጀራን መሳደብ ፤ ማንቋሸሽ ፤ ስም ማጥፋት ፤ መግደል በምን መስፈርት ነው የክርስትና አስተምህሮ ሊሆን የሚችለው? በየትኛው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመን ነው አንድ አገልጋይ በስምምነት ፊርማ እንዲወገዝ የቀረበው? እኛስ ከማን ተምረን ነው “እነእገሌ ይወገዙ ዘንድ” እያልን  ፊርማ የምናሰባስበው? በአለማዊው የመንግሥት ሥርዓት እኰ “ሕዝበ ውሳኔ” የሚያስፈልገው ድንበር ለመከለል ፤ የአንድን ብሔር ሙሉ መብት እስከመገንጠል ለመወሰን ነው፡፡ እኛ ታዲያ ይህን ከየት አመጣነው? በየትኛው የቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ነው በድምጽ ብልጫና በሕዝበ ውሳኔ ለማስወገዝ ፊርማ ለማሰባሰብ የምንቻኮለው?
    ያልተጻፈን ቀኖና እንደተጻፈ አድርጎ ሕዝብን እንደማሳሳት ያለ አስነዋሪ ድርጊትን የመሰለ ኃጢአት በእውኑ አለን? ቤተ ክርስቲያንን ስለናቅን እንጂ ብናከብራት ኖሮ አድመኝነት የመፍትሔ መንገድ አልነበረም፡፡ ይህን የመሰለ ሥርዓት አልበኝነት ሲነግስ ምነው ከመሪዎች የሚቆጣ ጠፋ? ምነው ልክ አይደለም ማለት ተሳነን? አዎ! ያለንበትን እናስተውል! ወንጌሉ ቅዱስ ከሆነ ፤ ልንቀናለት የሚገባን በቅድስናና በቅድስና ብቻ ነው!!!
ጌታ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

2 comments:

  1. ነገሩ ለማን እንደጻፍከው ግልጽ ነው። ኑፋቄ አንፈልግም ነው የእኛ አላማ! እናንተ ከማን እንደተማራችሁ አላማችሁ በስውር እንደሆነ መረጃ በግልጽ ወጥቷል! አሁን ልንደበደብ ነው እያልክ ታወራለህ?

    ReplyDelete