Wednesday 28 October 2015

ኢየሱስን የሚጋርዱ - ባህላዊ “ሰባኪ” ዎቻችን



       
                                                 Please read in PDF

     የክርስቶስ አገልጋይ ትጥቁ አጭር (ማቴ.10፥5-11) ፤ ዕለት ዕለት መስቀሉን ተሸክሞ በመከተል የሚኖር (ማር.8፥34) ፤በቁም ሳለ ከሚገድል ቅምጥልነት የራቀና “ወደዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።” የሚል ቅዱስ አቋም ያለው (1ጢሞ.5፥6 ፤ 6፥7-8) ፤ በሕይወቱ (ሮሜ.12፥2) ፣ በንግግሩ (ቈላ.4፥6) ፣ በመንገዱ ሁሉ የአምላኩን ስም የሚያስመሠግንና ከማስነቀፍ ፈጽሞ የራቀ ፤ ለሁልጊዜ ለፈጣሪው የሚያደላና የሚኖር ፤ ለሕይወቱ ምሳሌና መርሕ የሚሆነውን ነገር ለመፈለግ ሁልጊዜ እግረ ልቡን ወደ ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ የሚያቀና ሊሆን ይገባዋል፡፡ (ሐዋ.17፥10 ፤ 1ዮሐ.4፥1)
እንዲህ ስል አገልጋይ ባዕለ ጠጋ መሆን የለበትም የሚል አቋም የለኝም ፤ ዳሩ ግን አማኝም ሆነ አገልጋይ መሠረታዊ የሆነውን ነገር፥ ማለትም ምግብን ፣ ልብስንና መጠለያ በማግኘቱ ፣ እርካታ ይኖረው ዘንድ አስፈላጊ ፤ የተገባም ነው፡፡ ይህ ማለት አገልጋይ እንደሚሠራው ሁሉ አገባብ ያለው ደመወዙ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ እንዲሁ ገንዘብ የሚጠይቅ የተለየ ነገ ርቢከሰት ፣ በልግስና በመስጠት እግዚአብሔርን እያገለገለ (2ቆሮ.8፥3 ፤ 9፥6) “በመከራ ቀን ጥራኝ፥ አድንህማለሁ አንተም ታከብረኛለህ።” እንዲል፥ እግዚአብሔር እንዲሰጠው ወደእርሱ መመልከት ይኖርበታል፡፡ (መዝ.50፣15) ይህንን የምንለው ሁልጊዜ መንግሥቱንና ጽድቁን መቅደምና ማስከተል ከሌለብን ብቻ ነው፡፡ (ማቴ.6፥33)

    አንድና ሊታወቅ የሚገባው ነገር ግን፥ እኛ አማኞች ወይም አገልጋዮች የሆንን ሃብታም ለመሆን መፈለግ የለብንም፡፡“ …ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።” (1ጢሞ.6፥9)እንዲል፥ ራሳችንን “የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል የምሰማውን ቅዱስ ቃል እንዳያንቀው፥ የማያፈራም እንዳይሆን ከሚያደርግ መንፈስና ልማድ መራቅ አለብን፡፡ (ማቴ.13፥22)
ልከኛው አገልጋይ ቅዱስ ጳውሎስ በልክ ስለመኖርና በእግዚአብሔር መንግሥት ያገኘውን ክብርና መወደድ ፤ ሞገስና ተቀባይነት ለሌላ ለምንም ነገር ሳያውል ሲቀርና፥ ከእግዚአብሔር ያገኘውን ለእግዚአብሔር ብቻ ሲያውለው እናያለን፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር የባረካቸው እውነተኛ ሃብታሞች እግዚአብሔር ለዘወትር ስለማይጥላቸው (2ቆሮ.9፥8 ፤ ፊል.4፥19 ፤ዕብ.13፥6) በሃብታቸው ላይ እግዚአብሔርን ብቻ ያዙበታል ፤ ይሾሙበታልም፡፡ እግዚአብሔር ለሎጥ ሃብትን እጅግ አብዝቶ ሰጥቶታል ፤ ሰዶም በኃጢአት በተበላሸች ጊዜ ግን ከከተማይቱ አንዳች ሳይወስድ ነፍሱን ብቻ አድኗል፡፡ ሚስቱ ግን የከተማ ፍቅር ስላልተዋትና በልቧ ተሰንቅሮ ስለቀረ፥ ዘወር ብትል የጨው ሃውልት ሆና ቀርታለች፡፡ (ዘፍ.13፥5 ፤ 19፥26)ይህ እኛን ምን ያስተምረናል?
ከሁሉ ይልቅ ደግሞ አገልጋዮች ልንጠነቀቅ የሚገባን ብርቱ ነገር አለ ፤ ይኸውም በእግዚአብሔር አደባባዮች ላይ “እግዚአብሔርን በማገልገል ያገኘነውን ዝና ፣ ክብር ፣ መወደድ ፣ ሃብትና ንብረት ለመቀማጠያነት ፤ ለውዳሴ ከንቱና “ለክብራችን መከበርያ” መጠቀም ፈጽሞ አይገባንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በጻፋቸው መልዕክቶቹ ውስጥ ስናጠናው፥ በዚያ ዘመን የነበሩትና ከዚያም በፊት የነበሩትን ፈላስፎችን የሚያስንቅ ድንቅ ፍልስፍና ፣ የታወቀ የንግድ ችሎታ ፣ ብዙ ዶክትሬት መውጣት የሚችለው ዕውቀትና ችሎታ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለ ቅዱስ ቢሆንም ፤ ይህንን ሁሉ በመዘንጋት ራሱን “ … አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለክርስቶስ ኢየሱስ ስለጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ ፤ ስለእርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደጕድፍ እቈጥራለሁ … ” (ፊልጵ.3፥8-9) በማለት ራሱን ለክርስቶስ የተሰጠ ባርያ መሆኑንና ራሱን ሲያዋርድ እናገኘዋለን፡፡ በችሎታው ፣ በእውቀቱ ፣ በፍልስፍናው ፣ በማስተማር ችሎታው ፣ ለክርስቶስ ባገለገለው ሕይወቱ የመጣውን ክብርና ሽልማት ፤ … ሃብትና መመስገን ፈጽሞ አልተቀበለውም ፤ ቢቀበልም እንኳ ከጌታ በቀር ለማንም እንዲውል አላደረገውም፡፡ (ሐዋ.14፥11-18 ፤ 16፥17 ፤ )በእርግጥም፦ “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፦ አንተን የነቀፉበት ነቀፋ ወደቀብኝ ተብሎ እንደተጻፈ ሆነበት።” (ሮሜ.15፥3) እንደተባለ እንደክርስቶስ በትክክል ሕይወቱን በሕይወታቸው በመኖር አሳይተዋል፡፡
አንድ ነገር እንድናስተውል እወዳለሁ፥ ለእኛ ክርስቲያኖች ባዕለጠግነት በእግዚአብሔር መባረክ ፤ መወደዳችንና መከበራችን የሚያሳይ፥ ድህነት ደግሞ አለማግኘት እግዚአብሔርን ባለማመን ፤ ባለማክበርና ከእምነት ቢስንት እንደሚመጣ ከሚያስቡ ከአይሁድ ወገን አይደለንም፡፡(ምሳ.10፣15) ይህን ድሃን የማግለልና ፤ ባዕለጠጋን የመቀበልን ንግግር፥ ጌታ በተደጋጋሚ ቢሰማም ፈጽሞ አልተቀበለውም፡፡ (ሉቃ.16፣13-15 ፤ 18፣24)የጌታ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሃሳብ በግልጥ ተቃውመዋል፡፡ (ያዕ.2፥1-7) መሥራትን ባለመውደድ የሚመጣውን ድህነት ግን ስንፍናን ያጸድቃልና አንቀበለውም፡፡
አሁን አሁን ፥ አንድ ክፉ ልማድ በመካከላችን አቆጥቁጦ ፍሬ እያፈራነው ፤ “አገልጋዮቻችን” “የቅምጥልነትን ሕይወት ካልኖርን ፤ አንደነገሥታት ልማድ ካልተከበርን ፤ በብዕል የበለጠግን መሆናችንን ሰዎች ካላዩልን” የሚል ክፉ ልማድን በተደጋጋሚ እያየንነው ፤ ግና ወንጌል ከገባንና ገብቶናል ካልን፥ ቅዱሱን ጋብቻችንን በቤተ ክርስቲያን ፊት ከፈጸምን በኋላ “አለማውያንም ካላዩልን የሚል ሙግትና ክርክር ፤ በ“እግዚአብሔር አገልግሎትና ከእግዚአብሔር ሕዝብ” የሰበሰብነውን ገንዘብ ለቅምጥልነት ጋብቻና ፤ ዝናን ማድመቂያ ማድረጉ ፤ በጌታ አገልግሎት ያገኘነውን ነገር ለግል ማድመቂያ ማዋሉ ለምን አስፈለገ?
አሁን በአገራችን ላይ ያለው የድህነትና የረሃብ ገጽታ እጅግ አስፈሪ ነው ፤ ይህን ከጆሮ ያልተሰወረ እውነት ማሰብና ማሰላሰል ፤ እንዲሁም እንደእግዚአብሔር አገልጋይነታችን ለተራበ ሕዝብ መመገብና መራራት ሲገባ ፤ የተራበ ሕዝብ እንኳ ባይኖር፥ እልፍ የተቸገሩ ድሆች ባሉባት ድሃ አገር ላይ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” የሚል ስም ተሸክሞ “እንደንጉሥ ሥርዓት ለመቀማጠል መከጀል” አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ይህን እንድል ያስባለኝ በጥቅምት 14 ቀን 2008 በተደረገ አንድ የጋብቻ ሥርዓት ላይ “የንጉሥን ሥርዓት በመናፈቅ ስለተቀማጠሉ ሠርገኞችና አገልጋዮች” መናገርን ፈልጌ ነው፡፡ በእውኑ የሚገባ ነበርን? በሠርጉ ላይ የተገኘ አንድ ቀልደኛ “ንጉሥ ሲያበላ እንጂ ለራሱ ሲበላ አላየንም” ማለቱም፥ የምንሆነውና የምናደርገው የተዛመደ እንዳልሆነ ኰናኝ ነበር፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ ቃሉ ሥራችንን ይኰንነዋል፡፡
መሪዎችና አገልጋዮች ሕዝብን የማሳት አቅማቸው ትልቅ ነው ፤ እናም የእግዚአብሔር ከሆንን ሽታችን ፤ መዓዛችን ፤ ኑሮአችን ፤ ንግግራችን ፤ ሁለንተናችን ቃሉን፥ ቃሉን የሚሸትት መሆን አለበት፡፡ በተለይም የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆንን፥ ባለን ነገራችን ሁሉ ላይ እግዚአብሔርን መሾም እንጂ ፈቃዳችንን ማሰልጠን አይገባንም፡፡ በድሃው ሕዝብ ጫንቃ ላይ እየሰባን ይህን ድሃ ሕዝብ ብናስርብ“ … ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ በጎቹን ግን አታሰማሩም።” (ሕዝ.34፥3)የሚለው ብርቱ ወቀሳ እኛንም ይዘልፈናል፡፡ ክርስቲያን ሆነን ባህላዊውን መንገድ በመናፈቅ የምናስተምር ከሆንን የክርስቶስ አገልጋዮች አይደለንም ብቻ ሳይሆን፥ እንዲህ ባለ ቦታ የምንሰብከው ወንጌልና የምናቀርበው መዝሙር የታይታ እንጂ ለጌታ ፍቅር በመሸነፍና ክብሩን ሁሉ እርሱ እንዲወስደው ከማድረግ ልብ የመነጨ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡
ስለዚህ እንደጌታ አገልጋይ ለጌታ ደስታ ብቻ መጨነቁ መልካምና በፍጻሜው ታላቅ ሽልማት ያለው ነው፡፡ ይህን በማስተዋል ብናደርገው የከበረ ዋጋ አለንና ጌታ ማስተዋሉን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

6 comments:

  1. DEFAR WENDEME NEHE LGETA KIBRE MEKNATEHE YASDESETAL TEBAREK

    ReplyDelete
  2. ብስለት የጎደለው ጽሑፍ

    ReplyDelete
    Replies
    1. በመረጃ ጉድለቱን አሳየን እሥቲ

      Delete