4. በመንፈስ ቅዱስ ደስታ የተመላችም ነበረች ፤
ደስታ ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ነው፡፡ (ገላ.5፥22) ደስታ፥
የመብልና የመጠጥ ፣ በወገን መካከልም የመቀመጥ ፣ በተድላ የመንቀባረር ፣ የመልበስና የማማር ጉዳይም አይደለም ፤ ተድላና ደስታን
ለማየት ለመቅመስም የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ያሻል፡፡ “ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?” (መክ.2፥25)
እንዲል ደስታችንም ፍጹም የሚሆነው በእርሱ ብቻ ነው፡፡ (ዮሐ.15፥11) ዘወትር ለሁልጊዜ በጌታ ልንደሰት እንደሚገባንም ቃሉ ይነግረናል፡፡
(ፊልጵ.4፥4 ፤ 1ተሰ.5፥16)
ድንግል ማርያም ትልቁ ሐሴትና ደስታዋ በእግዚአብሔር መድኃኒትነት ላይ
ያላት መደገፍ ነው፡፡ “መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች” የሚለው መዝሙሯ፥ “እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ አምላኬም
ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።” (መዝ.18፥46) ከሚለው ከዳዊት መዝሙር ጋር ፤ “ … የጽድቅንም መጐናጸፊያ
ደርቦልኛልና በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፥ ነፍሴም በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች።” (ኢሳ.61፥10) ከሚለው ከኢሳይያስ መወድስ
ጋር ፤ “ … እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።” (ዕንባ.3፥18) ከሚለው ከዕንባቆም
የጽናት ዝማሬ ጋር ፍጹም የሚዛመድ ነው፡፡
ቅዱስ አረጋዊ ስምዖን በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት “ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ
ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና” በማለት የረካበትን ደስታ ፤ ቅዱስ አባት አብርሃም በብዙ ናፍቆት ለማየት የጓጓለትንና አይቶም
ሐሴት ያደረገበትን ያንን ደስታ ድንግል ማርያም አስተውላለች፡፡ (ዮሐ.8፥56) ከዚህም ባሻገር እርሱ የፍጥረት ሁሉ ተድላና ሐሴት
፤ ደስታውም የፍጥረት ሁሉ ኃይል ነው፡፡ (1ዜና.16፥27 ፤ ነህ.8፥10 ፤ 12፥43 ፤ አስ.8፥16 ፤ መዝ.21፥6 ፤ 32፥7
፤ ኢሳ.35፥10 ፤ 51፥11 ፤ 66፥14 ፤ ዘካ.10፥7 ፤ ሉቃ.10፥21 ፤ 1ጴጥ.1፥8 ፤ 4፥13) በእርግጥም ጻድቃን በእግዚአብሔር
ፊት ሐሴት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ (መዝ.68፥3 ፤ 70፥4 ፤ ሐዋ.16፥32) ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ስለተሰኙም በወኅኒ በሠንሠለት
ሆነው (ሐዋ.16፥25) ፣ በአንበሳ ጉድጓድ ሆነው (ዳን.6፥22) ፣ እቶኑ እጅግ በሆነ እሳት ውስጥም መካከል ሆነው (ዳን.3፥15
) እንኳ የልባቸው ገጽ አንዴም አልጠቆረም፡፡
የሚያሳዝነኝና የሚገርመኝ በአዲስ ኪዳን ዘመን ውስጥ ሆነን ለራሳችን ደስታ
የምንመኘውን ያህል ለሌላው ደስታ አለመሻታችን ነው፡፡ ደስታ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው ካልን ፥ ፍሬው ጣፋጭ ሆኖ ሌሎች ቢመገቡት
የሚያረካ ሊሆን ይገባል እንጂ፥ መራራና ሆምጣጣ ሊሆን አይገባውም፡፡ እንድንጸልይለትና እንድንወድደው የታዘዝንለትን ጠላታችንንና
ባላጋራችንን (ማቴ.5፥44-45) ብዙዎቻችን ጥላቻችንን በግልጽ ማንጸባረቁ ሳያንሰን፥ በጸሎታችንም የምንረግም ፣ መውደቁንና ሞቱን
የምንመኝለት ከመሆናችንም ባሻገር ቢሞትና ቢወድቅ እንደምንደሰት በጸሎታችን የምንጮህ እንደምን ይሆን የምናሳዝነው?! “ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ
… ” (ምሳ.24፥17) የሚለውን ቃል እንደምንስ አስተውለን ይሆን?
ደስታ ከሌላው ከመቀበል ይልቅ ለሌሎች በሚሆንና በሚደረግ ነገር መርካትና
መደሰትን ያሳያል ፤ ድንግል ማርያም የደስታዋ ምንጭ ለእርሷ ብቻ በሆነው አይደለም ፤ ለፍጥረትም ሁሉ በሆነው ነገር እንጂ፡፡ መላዕክት
ለአለሙ ሁሉ በሆነው መዳንና እርቅ እጅግ ተደስተው ዘምረዋል፡፡ (ሉቃ.2፥9-15) ፤ ለእኛና ለአንድ ኃጢአተኛ ወደእግዚአብሔር
መንግሥት በንስሐ መመለስ እጅግ ይደሰታሉ፡፡ (ሉቃ.15፥7 ፤ 10) ፤ ደቀ መዛሙርት በጌታ በኢየሱስ ስም አስተምረው የተናቁ በመሆናቸው
፥ ፊታቸው እንደጸሐይ እያበራ እጅግ ተደስተው ከሸንጎው ፊት ወጥተዋል፡፡ (ሐዋ.5፥42) ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ከኃጢአታቸው
በመመለሳቸው ምክንያት እጅግ መንፈሳዊ ደስታን ተደስቷል፡፡ (2ቆሮ.7፥4-8)
እውነተኛ ደስታ ለሌሎች በሆነው እጅግ ሲደሰት እንጂ ለእኔ ብቻ በሚል ስግብግብነት
የሚጠመድ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ሌላው በረሃብና በእርዛት ሲሰቃይ ፥ ለራሳቸው “ተመችቷቸውና ደልቷቸው ፤ ተደስተውም” እንደሚኖሩ
የሚያስቡ የአገርና የሃይማኖት መሪዎች በኋላ ጽኑ ሃዘን እንደሚገጥማቸው አስበው፥ ፈጥነው ንስሐ ቢገቡና ቢመለሱ እጅግ መልካም በሆነላቸው
ነበር ፤ ምክንያቱም መንፈሳዊም መሪዎች ሆኑ የዚህም አለም መሪዎች ወደደስታው ግብዣ ለመግባት የሚመዘኑበት የሚዛናቸው ልክ በሥራቸው
በሚያሳዩት ታማኝነት ነው፡፡
አንድ መንግሥት ለአንድ ሠራተኛው ሹመትና ሽልማት የሚሰጠው ፤ ወደደስታውም
የሚያስገባው ለሥራው ባሳየው ታማኝነት ልክ ነው፡፡ ጌታችንም የሰጠንን መክሊት ማለትም ኃላፊነት ፣ ሥልጣን ፣ ሃብት ፣ መንፈሳዊ
ጸጋ … መጥቶ የሚረከብበትና የሚጠይቅበት ጊዜም አለ፡፡ ወደጌታችን ደስታ የምንገባው ወይም የመግባቱን ዕድል የምናገኘው መክሊቱን
ለማትረፍና መክሊቱን በአገባብ ለመጠቀም ባሳየነውና ወደሥራም በተረጎምነው ታማኝነት ልክ ነው፡፡ (ማቴ.25፥23) ታማኝነትን ማጉደል ደስታን ስለመንጠቁ ምንም
ጥርጥር የለውም፡፡ (ማቴ.25፥26-30)
ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ደስታ የበዛላት ናት ስንል፥ ለጌታ ቃል ፍጹም
የታመነችና ፤ ለቃሉ በአክብሮትና በፍርሃት በመታዘዝ ትኖር ነበር ማለታችን ነው፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔርን ቃል በመፍራትና በማክበር
የሚኖሩ ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ደስታ የበዛላቸው ናቸው፡፡ ይህ ደስታ ሁኔታዎች እንኳ ከእኛ ሊወስዱት የማቻላቸው ፍጹም የሆነ ደስታ
ነው፡፡
አቤቱ ጌታችን አብ ሆይ! እንዲህ ያለውን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነውን
ደስታ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ አብዛልን፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment