Saturday 26 September 2015

መስቀልና ራስን (እኔነትን) መካድ

     
                            Please read in PDF      

   ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ገና ከመሰቀሉ በፊት ስለመስቀሉ፥ “ … መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ.10፥38) በማለት አስተማረ፡፡ በአሁን ጊዜ፥ ይህ የጌታችን ትምህርት ከመሰቀሉ በፊት እንደተናገረውና እንደተጻፈው ሃሳብ ሳይሆን እንደራስ ሃሳብ ከሚተረጎሙ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ በእርግጥም ጌታችን ከመሰቀሉ በፊት ሰሚዎቹ መስቀልን እንዴት ነበር ሲረዱት የነበረው? ጸሐፊው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊስ ሰሚዎቹ እንዴት መረዳታቸውን አስተውሎ ይሆን የጻፈው? “መስቀል” ተብሎ የተነገረው ቃል ጌታ ከመሰቀሉ በፊትና ከተሰቀለ በኋላ ሁለት አይነት መልክ አለው ወይም የቃሉ ሃሳብ አንድና አንድ ነው? ሰሚዎቹ ያስተዋሉት መስቀል ጌታ ወደፊት የተሰቀለበትን መስቀል ነው ወይስ ጌታ የዚያኔ ሊናገር ያሰበውን ነው? እኛስ እንዴት ነው እየተረዳን ያለነው? የሚለውን ሐቲታዊ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ሃሳቡን የጌታን ሃሳብ በአገባቡ ለመረዳት ያግዘናል፡፡
     “ታላላቅ” የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ አንድና ወጥነት ያለው መሆኑን በመስማማት ቃል ይናገራሉ፡፡  ከሁሉም ይልቅ ደግሞ ወንጌላውያን ወንጌልን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወይም ቃኚነት ሲጽፉ ታሪክ ቀመስ እንደመሆኑ መጠን አንዳች በማያቅማማ ሁኔታ የጌታችንን ቀጥተኛ ንግግሮችንና ትምህርቶችን አስፍረውታል፡፡  መንፈስ ቅዱስ፥ ቅዱሳን አባቶችን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲጽፉ ሲነዳቸው ውስብስብና እንዳይገባቸው ወይም እንዳይገባን አድርጎ አልገለጠም ፤ አላጻፈውምም፡፡  በእርግጥም “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ” (ኢሳ.54፥13 ፤ ዮሐ.6፥45) ተብሎ እንደተነገረ፥ የሚድኑትና የዘላለም ሕይወትን የሚያገኙት ስለእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ከራሱ የተማሩት ብቻ ናቸው፡፡

      ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ስለአገልግሎት ጥሪና አገልግሎቱ ስለሚፈልገው ቅድስናና ድንቅ መለኪያ ፤ ስለሚደርስባቸውና ስለሚገጥማቸው መከራና ስደት ሲናገራቸው፥ “ … መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” በማለት ተናገራቸው፡፡ “መስቀል” የሚለው ቃል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሰውና የተነገረው በዚህ ቦታ ነው፡፡ ቃሉ የተጠቀሰበት ዋናው ምክንያት በጥንት ግሪኮች ወንጀል የሠሩ ሰዎች ስለሠሩት ጥፋታቸው እንደመቀጣጫ በዋናነት የሚያገለግለው መሣርያ መስቀል ስለሆነ ፥ መስቀል ሞትን ማመላከቻ ሃሳብ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡
  ስለዚህም “መስቀል” በዚያ ዘመን የሞት ምሳሌነትን መግለጫ ነው ስንል የተመሳቀለን እንጨት ማመላከቻ አይደለም ማለታችን ነው ፤ ምክንያቱም የዚያኔ የነበረው መስቀል ሹል በሆነ ቋሚ እንጨት ሰክቶ (ሰቅሎ) ማዋልን ወይም መግደልን እንጂ እንደዛሬው ወይም እንደጌታችን ዕፀ መስቀል አይደለምና፡፡ ጌታችንም ሊናገር የፈለገው ዋናው ሃሳብ ለወንጌል አገልግሎት የተጠሩት ቅዱሳን ደቀ መዛሙርት በሚያገለግሉት ቅዱስ አገልግሎት ውስጥ ለሚገጥማቸው የትኛውም ተግዳሮት እስከሞት ድረስም ቢሆን ዋጋ መክፈል እንዳለባቸው በአጽንዖት ለማሳሰብ የተናገረው ነው፡፡ መስቀል የሞት ምሳሌነትን ሊያሳይ እንጂ ለሌላ ለምንም ማሳያነት እንዳልተቀመጠ፥ አሁንም ጌታችን “ … በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።” (ማር.8፥34) በማለት በግልጥ አስቀምጦታል፡፡  
    ለተጠራንበት ቅዱስ የአገልግሎት ጥሪ መስቀሉን ለመሸከም ወይም እስከሞት ድረስ የታመንንና ዋጋ ለመክፈል የተዘጋጀን ሆነን ለመገኘት፥ ለክብሩ ተሟጋች የሆነውንና ራሱን በማስቀደም የታወቀውን እኔን ወይም ራስን መግደል ወይም መካድ ያስፈልጋል፡፡ አልሞትኩም የሚል ሰው፥ እኔ እያለ ሲያወራ አይታክተውም ፤ አይደክመውምም፡፡ ለክርስቶስ ሊሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠ ግን እርሱ ራሱን ክዷልና በሚደርስበት ነገር በአንዱም እንኳ አያጉረመርምም ፤ አይዝትምም፡፡ (1ጴጥ.2፥21-24) መስቀል መሸከም ለአገልግሎቱ ባለቤት ለክርስቶስ ኢየሱስ በመታመን ራስን ለሞትም ጭምር ማዘጋጀት ነው፡፡
      ራስን መካድ ለራስ ማስታወቂያ ከመሥራት ፣ ለራስ ከመሟገት ፣ ለመብት ከመከራከር ፣ ለጥቅምና ለይገባኛል ዘብ ከመቆም ፤ እኔ እኔ ነኝ ከማለት ፍጹም መሞትን የሚያሳይ ነው፡፡ እውነተኛ አማኝ ክርስቲያን፥ ዘወትር መስቀል ተሸካሚ ነውና ለራሱ ለሚሆነው ነገር የማይቆም ነው፡፡ የሞተ እሬሳ ለራሱ መከራከር አይችልም ፤ ለክርስቶስ የሞተ ወይም ሊሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠ አማኝም ከክርስቶስ በቀር ሌላ የሚናገረው ፤ ጮኾ የሚያሰማው አንዳች ነገርም የለውም፡፡ ራሱን የካደ ሰው የራሱን ፈቃድና መሻት ማዕከል ካደረገ ነገር የጸዳ ሰው ነው፡፡ ይህም ማለት ፈቃዱና መሻቱ የሞተለት ጌታ መደሰቱና በእርሱ መርካቱ እንጂ የእርሱ ደስታ ትዝም የሚለው አይደለም፡፡
      ባርያ የሁል ጊዜ ደስታው ጌታውን በአገልግሎቱ ማስደሰት ነው ፤ እኛ ለክርስቶስ ፍቅሩንና ማዳኑን ያየን ፤ አይተንም ደስ በመሰኘት የፈቃድ ባርያዎች የሆንን ነን፡፡ ደስታችንና እርካታችን የሞተልንና ያዳነን ጌታ ተደስቶ ማየት ወይም ፈቃዱን ደስ ማሰኘት ነው፡፡  ስለዚህ ራሳችንን ክደናልና የእኛ የምንለው ፍላጎትና መሻት የለንም፡፡ ዛሬ በየመድረኩና አውደ ምህረቱ ላይ ያለው አገልጋይና አማኝ በእውኑ ራሱን የካደና የራሱን መሻት የማያስቀድም ነውን?!
       መስቀሉን ለመሸከም የራስን ፈቃድ መግደል ያስፈልጋል፡፡ ፈቃዱን ያልገደለ ሙሉ ለሙሉ ለክርስቶስ ፈቃድ ራሱን ማስገዛት አይችልም፡፡ “ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን” (ሮሜ.6፥6) እንዲል በአሮጌው ሰው ቁጥጥር ያለ ሰው የአዲሱን ሰው ጠባይ መልበስም ሆነ በእርሱ ቁጥጥር ሥር መሆን አይቻለውም፡፡ አሮጌው ሰው “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።” (ገላ.5፥24) እንዲል፥ መሞት የሚችል ማንነት አለው ፤ በዚህ አገላለጥም “ሰቀሉ” ሲል ለራስ ፈቃድና መሻት አለመኖርንና ለመስቀሉ ባለቤት ፈቃድና ምኞት መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
   እንግዲህ መስቀሉን ስለመሸከም ስናወሳ፥ በዋናነት ወደሕሊናችን ሊመጣ የሚገባው ሁለት ነገር ቢሆን፦ አንዱ ለራስ ፈቃድና መሻት አለመኖርን ሲሆን፥ ሁለተኛው የክርስቶስ ሞት መሆኑን ልናስታውስና ዘወትር ላንዘነጋ ይገባናል፡፡ ሁለተኛውን ሌላ ጊዜ የምመለስበት ቢሆንም፥ ዋናው ሃሳባችን ግን መስቀሉን ሊሸከም የሚገባው ማናቸውም አማኝ ቀድሞ ራሱን ሊክድ ይገባዋል የሚለውን ዳግመኛ መናገር እወዳለሁ፡፡
     ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ያለብን በኋላው ከሆነ፥ ከፊት ከፊት እንድንቀድም የሚያስቸኩለንን ፈቃዳችንን ፈጽሞ መተው አለብን ወይም መግደል አለብን ማለት ነው፡፡ “በኋላ መከተል” ማለት በእርሱ ፈቃድና ቁጥጥር ሥር መሆንን ያመለክታል ፤ ማለትም በእርሱ ፈቃድና ቁጥጥር ሆኖ ለእርሱ መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑለት የወደደው እስከሞት በታመነ ማንነት ውስጥ የአገልግሎት ዘመናቸውን እንዲፈጽሙ ነው፡፡ (ማቴ.10፥22 ፤ 24፥13 ፤ ራዕ.2፥10) እኛም መስቀሉን ተሸከሙ መባላችን እስከሞት ዋጋ የሚያስከፍለውን የወንጌልን አገልግሎት በዘመናችን ተሸክመን መመላለስ እንዳለብን በማስተዋል ሊሆን ይገባዋል፡፡
   እግዚአብሔር አቅማችን ካልተሟጠጠና ካልሞተ በቀር በእኛ አቅም አይሠራም፡፡ እግዚአብሔር ደባልነት አያሻውም ፤ ብቻውን ያለእንከን ሠራተኛ ነው፡፡ መስቀሉን ለመሸከም መሞት ያሻናል ስንል እግዚአብሔር ሕያውና መሥራት እንደሚችል ከሚያስብ ሰው ጋር መሥራት አይፈልግምም ማለታችን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና”  (2ቆሮ.12፥9) እንደተባለው፥ እኛ አለን በምንለው አቅማችን ሳይሆን እግዚአብሔር በድካማችን ብርቱ ሥራ መሥራትን ይወዳልና ፤ መስቀሉን በብርታታችን ለመሸከም አንጣጣር፡፡
     ትላንት ወንጌል በማገልገላችን ስንታማ ፣ ስንነቀፍ ፣ ስንሰደብ ፣ ስንዋረድ ፣ ስማችን ሲጠፋ ፣ ስንዘረጠጥ … በክርስቶስ የሆነውንና የተነገረን ቃሉን ዘንግተን ፤ ከተሸከምነው ወይም ከተሰቀልንበት መስቀል ወርደን ወይም ተንሸራተን በሆነብን ነገር ስንሟገት ዘመናችንን ጨርሰናል፡፡ ግና መስቀሉን ተሸክመናል ብለን ካመንን በነቀፌታ ከሚደርስብን በላይ ገና ልንሞትም እንዳለን ወይም እስከመስቀሉ ድረስ መታገስ እንዳለብን በማስተዋል የሚደርስብንን ሁሉ በጸጋ ልንቀበል ይገባናል፡፡ (ሮሜ.12፥12) መስቀሉን ስናስታውስ በልባችን ዘወትር ትዝ ሊለን የሚገባው እስሞት ድረስ ጌታችንን በመታመን ልናገለግለው እንደሚገባን እንጂ ሜዳዊ ሥርዓቱን ብቻ ማከናወን እንደሌለብን አሁንም ማስታወስ እወዳለሁ፡፡

ጌታ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment