Thursday 17 September 2015

እኔን ዛሬ ማረው!




ጉብዝናዬን ላ’ጢአት ፣ ብርታቴን ለነውር ፤
ውበቴን ለወጥመድ ፣ አውዬ የማድር ፤
እኔ ነኝ ጌታዬ ፣ እኔ ነኝ ፣ እኔ ነኝ፤
በግ ከሚያርዱ ጋራ ፣ እሳት ስሞቅ ’ምገኝ፡፡


ለነፍስ የማልራራ ፣ ውርጃ አስወራጁ፤
ዶሮ ሳይጮኽ ሦስቴ ፣ በሽምጥጫ ካጁ፤
ሸክም የከበደው ፣ ቀንበር ያጎበጠው ፤
እኔ ነኝ ኢየሱስ ፣ እኔን ዛሬ ማረው!!!

ቀኑ ሲቀላላ ፣ ወደወይን ጠጁ፤
ድንግዝግዝ ሲል ደግሞ፣  ከመሸታ ደጁ፤
በስካር በፍትወት ፣ ነድጄ ከስዬ፤
’ምኖር ዕድሜ ልኬን፣ ከፊትህ ኮብልዬ፤
እኔ ነኝ ያ ቃየል ፣ እኔ ነኝ ይሁዳም፤
ወድቀው ከቀሩቱ ፣ ከታሪክ ’ማልማር፡፡

ኃጢአት በአመክንዮ ፣ እየተረጎምኩኝ፤
ከመለየት ይልቅ፣  እየተቋመርኩኝ፤
ጽድቅ በሚመስል ፣ ክፋት ተከብቤ፤
ከመልካም ተራቁቶ ፣ የጠቆረው ልቤ፤
ለእኔ ነው ጌታዬ ፣ መድኃኒት የሚያሻው፤
ኃጢአት ጉንድሽ አ’ርጎ ፣ ጉልበቴን ለነሳው፡፡

የተትረፈረፈ ፣ የበዛ ይቅርታ፤
እኔን ነው ’ሚገባኝ ፣ የሞትክልኝ ጌታ፤
ከኃጢአት ጋር ቁማር ፣ ዕቃቃዬን ትቼ፤
ስመጣ ወ’ዳንተ ፣ እጆቼን ዘርግቼ፤
ትዝብት በማያውቀው ፣ በምህረት ፊትህ፤
ተቀበለኝ ጌታ ፣ በምትወደው ልጅህ ፣ ተቀበለኝ ስልህ፡፡
ተንከባሏል ከ’ኔ ፣ ያ ሁሉ ኃጢአቴ፤

በልጁ ስላየን ፣ ልጁን ውዱ አባቴ፡፡ አሜን፡፡

1 comment: