Tuesday 29 September 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ክፍል - 4


                             Please read in PDF          

3.  እምነት

      ያለእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም ፤ ያለእምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ካልተቻለ ልናምን የሚገባን እግዚአብሔርን ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ (ዕብ.11፥6) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ላይ ሁለት ጊዜ የተደነቀውና ምስክርነትም የሰጠው ከእስራኤል መካከል ያጣውን እምነት ከአህዛባውያን አማኞች በማግኘቱ ነው፡፡ (ማቴ.15፥28 ፤ ሉቃ.7፥9) ብዙ ቅዱሳንም እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙት “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል” እንዲል በእምነታቸው ነው፡፡ (ዕብ.11፥4 ፤ 5 ፤ 7 ፤ 8 ፤ 17 ፤ 20 ፤ 21 ፤ 22 ፤ 23 ፤ 28-40)

    እምነታችን አጋንንት ከሚያምኑት እምነት ካልበለጠ ምንም ሥራ መሥራት አይቻለውም፡፡ እንዲህ ያለው እምነትም “የሞተ እምነት” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ (ያዕ.2፥26)  በዚህ ርእስ ሥር የምናወራው እምነት የልጅነትን ሥልጣን ስለሚያስገኘው እምነት አይደለም ፤ ልጅነትን ካገኘን በኋላ ስለምናሳድገውና አገልግሎታችንን ስለምንፈጽምበት እምነት እንጂ፡፡ እምነት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነውና ያድጋልም (ገላ.5፥22) ይሞታልም፡፡ ጌታችን እንዲህ ስላለው እምነት “ … እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ” በማለት ገልጦታል፡፡(ማቴ.17፥20)
      አለማመናችን የሚነሳን ፥ ማመናችን የሚሰጠን ትልቅ ጉልበት አለው፡፡ ተራራን ማፍለስ “ለእምነታችን” ከተቻለው፥ አለማመናችን ደግሞ የማይነቀልን ተራራ በልባችን ሊቆልል ይችላል፡፡ (ዘካ.4፥6 ፤ ማቴ.21፥21 ፤ 1ቆሮ.12፥9 ፤ 13፥2 2ቆሮ.12፥8)
       እምነት ሁለንተናን ይገዛል ፤ እምነታችን የልብ መደገፋችንን ፤ አለኝታችን ማን እንደሆነ የመወሰን ብቃት አለው፡፡ ሰዎች ስለእምነታቸው ወይም ስላመኑት ነገር እስከሞት ድረስ ዋጋን ሲከፍሉ እናያለን፡፡ የአይ ኤስ አይ ኤስና መሰል ቡድኖች ከእነርሱ ውጪ ያለውን አለም በማሸበር ፤ በማረድ ፤ በመግደል ፤ በማቃጠል  ሲገልጡት ያመኑት እምነታቸው ትምህርት ውጤት ነው ፤ አልቦ እግዚአብሔር ባዮች የገዛ ህሊናቸውን በመካድ እስከማበድ የሚደርሱት፥ ስለትምህርታቸውና እምነታቸው በሚከፍሉት ዋጋ ነው ፤ አመንዝራዎችም ከአመንዝራነት ውጪ ሌላ የሚያረካ እንደሌለ አምነው በዝሙት የሚሰክሩት፥ “ነው” ብለው ስላመኑ ነው፡፡ ሌሎችም እንዲሁ፡፡
     እምነት “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።” (ዕብ.11፥1) መጽሐፍ ካለን፥ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የምናይበት የጠራ አይን ፣ የዘላለሙን ተስፋችንን የምናሳርፍበት ልብ ፣ ከእግዚአብሔር የልመናችንን ዋጋ የምንቀበልበት እጅ ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምወርስበት ብርቱ ጉልበት ፤ የምድሩን መከራ ሁሉ የምንረሳበት ብርቱ ጽናታችን ነው ማለት ነው፡፡ ይህም በጌታችን ላይ ያለን እምነታችን፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውና ተስፋችንን ከእጁ እንድንቀበል የሚያደርገው ያለግብዝነት ሲሆን ብቻ ማለት ነው፡፡ (1ጢሞ.1፥5 ፤ 2ጢሞ.1፥5)
     ካህኑ ዘካርያስ የሚነገረውን ብሥራት በእምነት ላለመቀበል መልአኩን በአለማመን መንፈስ ይሞግታል፡፡ ስለዚህም መልአኩ በእግዚአብሔር ክንድ አላምን ያለውን ካህን ትናጋውን አሰረው፡፡ ካህኑ ከሚስቱ ጋር ሩካቤ ፈጽሞ ስለሚያገኘው ዘር “እኔ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” (ሉቃ.1፥18) እያለ ምክንያት ይደረድራል፡፡ ድንግሊቱ ግን ያለወንድ ዘር ስለምትወልደው ሕጻን፥ መልአኩ በነገራት ጊዜ በትሁት መንፈስ መልአኩን ትጠይቃለች እንጂ እንደካህኑ ዘካርያስ አትከራከርም ፤ ሙግትም ከመልአኩ ጋር አልጀመረችም፡፡ መልአኩ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና” ባላት ጊዜ “ይሁንልኝ” አለች እንጂ ምንም ነገር አልተናገረችም፡፡
     ዛሬ ከዚህ የከፋ ነገር እናያለን፡፡ የአገልግሎቱን አውደ ምህረት የወረሩት ብዙዎች የሚናገሩትንና የሚሰብኩትን ፣ የሚቀድሱትናን የሚያዜሙትን አያምኑትም ፤ ሰሚዎቹ አማንያን ግን የሰሙትን አምነው ይቀደሳሉ፡፡ አገልጋይ ዝሎ ዓለማዊነትን ፣ ዝሙትን ፣ ግብረ ሰዶምንና ሴሰኝነትን በአለማመን ልብ እየጐመጀ ለመፈጸም ሰውነቱን ያቃጥላል፡፡ አማንያኑ ግን በእምነት ጉልበት ወደእግዚአብሔር አደባባይ ይወጣሉ ፤ ካህኑ ባለማመን ይሞግታል ፤ አማኙ ግን በትሁት ልብ በማመን ይመልሳል፡፡
     ድንግል ማርያም የአዲስ ኪዳን የመጀመርያይቱ አማኝ ናት፡፡ “ይሁንልኝ ፤ ይደረገልኝ” ብላ በመናገር፡፡ በዘመኑ የነበሩ የሕጉ ሊቃውንትና ካህናት ሄሮድስን በክፉ ለመምከር እንጂ (ማቴ.2፥4-6)፥ ለራሳቸው ከቤተ መቅደሱ ርቃ በናዝሬት ገሊላ የነበረችው እናት ግን በእግዚአብሔር ለመታመን እንጂ ለመጠራጠርም ፤ ለመሞገትም ፤ በክፉ ለመምከርም አንዳች ነገር አልነበራትም፡፡
      የባርያነት ውርደቷን የተመለከተ ጌታ በእርሷ ድንቅን ነገር እንደሚያደርግ በትህትና ተናገረች፡፡ እውነት ነው! ድንግል ማርያም የተመረጠችበትና እግዚአብሔር በእርሷ ያደረገው ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ በሥጋ ከእርሷ ተወልዷልና ፤ ይህ በማንም ያልተደረገ የማይደረግም ነው፡፡ እግዚአብሔር ድንግሊቱን መረጠ ፤ ድንግሊቱም “ይሁንልኝ” ብላ በእምነት ልብ ዝቅ ብላ ተቀበለች፡፡
     እግዚአብሔር ከሁኔታ በላይ ፣ ከተፈጥሮ በላይ ፣ ከሕግ በላይ ፣ ከፍጡር ክንድ በላይ ፣ ከነገሥታትና ከገዢዎች በላይ እንደሚሠራና እጁን የምትከለክል ጣቱን የምትጋርድ ነገር እንደሌለ በፍጹም ልብ የምናምን ስንቶች ነን?

ጌታ ልባችንን ለእምነት ያዘንብልልን፡፡ አሜን፡፡


ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment