Friday 7 November 2014

የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮች(ክፍል - አንድ)


                                          Please read in PDF
    
     የመከራው አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ ክርስትና ያለመከራ የኖረበት ዘመን የለም፡፡ የትላንት ቄሳሮች ክርስቲያኖችን በማረድ ፤ የኋላ መናፍቃን የእውነትን ወንጌል በማጣመም፤ ፖለቲከኞችም ድርሳኖቻቸውን አግዝፈው መጽሐፍ ቅዱስን “ሊያንኳስሱ” ፤ ህሊናቸውን የሳቱ ፈላስፎች በወንጌሉ ቃል ሊሳለቁ ፤ ሳይንሳዊ ምርምር (ሁሉም አይደለም) ሐለወተ እግዚአብሔርን ሊቃረን … መልከ ብዙ ስህተቶችንና መከራዎችን በክርስትና ውስጥና ላይ ተስተናግዷል፡፡ ይህ ግን ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን የተቃወሙትን አደከመ እንጂ፤ ቤተ ክርስቲያንን እንደትክል ድንጋይ በሙሽራዋ ጽናት ዛሬም ህያው ምስክር ሆና አለች፡፡
    ከዚህ የሚከፋው ነገር ግን፥ ከውጪ ሆኖ በግልጥ የሚዋጋው የጠላት አሠራር ሳይሆን በስውር “ሌላ ወንጌል ሳይይዙ”(ገላ.1፥7) እንደብርሃን መልአክ (2ቆሮ.11፥14) ተገልጠው ሊያናውጡ የሚወዱቱ ናቸው፡፡ በዘመናት የሰይጣን ውጊያ ልዩ ልዩ ነው፡፡ ትላንት ጣዖት አቁሞ ያሰግድ የነበረው፤ ዛሬ ያንን ስልት ትቶ ጣዖትን የብርሃን መልአክ አልብሶ በእያንዳንዱ ልብ አቁሟል፡፡ ሰው ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ላለመገናኘት የራሱ “የብርሃን ምክንያት” አለው፡፡ ያንን “ብርሃናዊ ምክንያት” በጸሎትና በመንፈስ ቅዱስ ሃሳብ ብንመረምረው ግን ጣዖት እንጂ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ምንም ነገር ቢሆን ለእግዚአብሔር የሆነውን ነገር እንዲሰርቅብን አልተፈቀደለትምና፡፡(ማቴ.10፥37)

    የሰይጣን አገልጋዮች ራሳቸውን ገልጠው ሰይጣን በሚገለገልበት ሥፍራና ቃል አያገለግሉም፡፡ ብዙ ጊዜ የሰይጣን አገልጋዮች የሚያገለግሉት የእግዚአብሔር መመለኪያ በሆነበት ሥፍራና ከእግዚአብሔር ቃል በመጥቀስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የእነዚህን ሐሰተኛ መምህራን ጠባይ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እኒህም፦
1.    ሐሰተኛ መምህራን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ባሉበት ሥፍራ አይኖሩም፡፡
   ቅዱስ ጳውሎስ “ከሔድሁም በኋላ …” የሚለው እኒህን መምህራን ነው፡፡(ሐዋ.20፥29) እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ባሉበት የሐሰት መምህራን ትምህርት ይራቆታል፡፡ ስለዚህ “ሊሰርቁና ሊያርዱ ሊያጠፉም የሚመጡበት፤ ሌቦችና ወንበዴዎች የተባሉት የሐሰት መምህራን በበር ሳይሆን በሌላ መንገድ ነው የሚገቡት፡፡(ዮሐ.10፥1 ፤ 10) ደቀ መዛሙርት የሚያስተምሩትን እውነተኛ ትምህርት እያስተማሩ አይመጡምና ትምህርታቸው ሌላ መንገድ፤ ሌላ በር ተብሏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በሚገቡበት በር አይገቡም፡፡ ደቀ መዛሙርት በማይገቡበት በሌላ በር (የክህደት ትምህርት) እውነተኞቹ አገልጋዮች በሌሉበት ሰዓት ይገባሉ እንጂ፡፡
   መንጋውን የሚጠብቅ እውነተኛ አገልጋይ ሲጠፋ ሐሰተኛ አገልጋዮች በቦታው ይተካሉ ወይም ቦታውን ይይዛሉ፡፡ በሌላ አገላለጥ እውነትን ከመናገር ፤ ወንጌልን በግልጥ ለመስበክ የጨከኑ ሲያጠፉና ወንጌሉን የሚያመቻምቹ አገልጋዮች ሲበዙ ተረታ ተረትን የሚተርቱ ፤ ፌዝና ቧልትን የሚያወሩ በየአውደ ምህረቱ ይፈላሉ፡፡ እውነተኛ አገልጋይ ደግሞ መንጋው አደጋ እንዳይገጥመው ፈጽሞ  ይተጋል፡፡ አስከፊው የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ትልቁ ገጽታ በወንጌል ላይ የሚደራደሩና የሚያመቻምቹ አገልጋዮች መፍላታቸው ነው፡፡
   እውነተኛው አገልጋይ ተውጦ(ተሰዶ) የሐሰት አገልጋይ የሚናገረው ቃል ፍጹም የታመነው፤ የሐሰት አገልጋዮች ነገራቸውን ደጋግመው ፍጹም ሕዝቡን በሐሰት ወጥመድ ስላጠመዱት ነው፡፡
2.   የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች ናቸው፡፡
    ዲያብሎስ እኛ ወደ ገሃነመ እሳት ብንገባ የማይራራልን ስላልፈጠረንና ገንዘቦቹ ስላልሆን ነው፡፡ ገንዘቦቹ የሆንለት እግዚአብሔር ውድና አንድ ልጁን ልኰ አድኖናል፡፡ የሐሰት መምህራን ልዩ ጠባያቸው እነርሱ በሐሰት ትምህርት ተጠላልፈው ወድቀው ፤ ለሌላውም ሳይራሩ በዚያው የክፋት ትምህርት በጭካኔ ይመራሉ(ያሠማራሉ)፡፡
   የተኩላ ልዩ ባህርይው በበጐች መካከል በግ መስሎ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ በግ መስሎ በበጐች መካከል መገኘቱ በማይራራ ጭካኔው በጐችን በህይወት ሳሉ እየነጠቀ ሊበላ እንጂ አብሮ ሊያድር አይደለም፡፡ የሐሰት መምህራን እንዲህ ያለ ነገር ልዩ “ክህነታቸው” ነው፡፡ ትምህርቶቻቸው ፣ ጽሁፎቻቸው ፣ መዝሙራቸው ፣ ስብከቶቻቸው ፣ ወግና ትውፊታቸው … ከእውነተኛው መለየት እስኪቸግር የሚመሳሰል የበግና የተኩላ ያህል ቅርርብ አለው፡፡ ነገር ግን እንደተነገረው በፍጻሜ “ከፍሬያቸው ይታወቃሉ”፡፡(ማቴ.7፥16)
   የሐሰት መምህራን ለራሳቸው አላማ ማግደው እስከተጠቀሙብን ድረስ፥ የእኛ መዳንና አለመዳን ግድ የማይሰጣቸው ጨካኞች ናቸው፡፡ “ጥሬ ዘይት” ከኢየሩሳሌም ነው የመጣው “የተዘጋ ማህጸን ይከፍታልና፤ በማህጸን ጨምሩ ፣ በጆሮ ጠብ አድርጉ … ” ከሚሉት ወሮበላ የከተማ ባህታውያን እስከ እስረኞች ፣ ጥቂት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽተኞችን ፣ አካል ጉዳተኞችን … አሰባስበው በስማቸው ከውጪ ዕርዳታን ፤ ከሐገር ቤት ሥጦታን ካሰባሰቡ በኋላ ዘወር ብለው እስከማያዩቱ ድረስ የሐሰት መምህራን የመጨረሻ ሃሳባቸውን ማወቅ ያስቸግር ይሆናል፡፡ በዙርያቸው የተሰበሰቡትን አማኞችና ተከታዮች ከአስገድዶ መድፈር እስከ የግብረ ሰዶም ጥቃት ፈጻሚ የሆኑቱ የእኛው ዘመን ሐሰተኞች መምህራን መገለጫቸው ነው፡፡
    በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሰጠው ትልቁ ምስክርነት “ቴዎዳስ፦ እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ።”(ሐዋ.5፥36) የሚል ነው፡፡ “ልትጠፋ ያለች ከተማ ነጋሪት ቢጐሰምባት አትሰማም” እንዲባል ብዙዎቻችን የሐሰት ትምህርት ከሚያስተምሩ አገልጋዮች እንድንርቅ ሲነገረን በአገልጋዩ ተቀንቶ ወይም ስም ማጥፋት ነው( ግን እንዲህ የሚያደርጉ የሉም ማለታችን አይደለም) ብለን ነው የሙጥኝ የምንለው፡፡ ነገር ግን በፍጻሜ እንደምናምን መሆንም አለና ፍጻሜው ዕረፍት የሆነውን ጌታ ብንከተል ፍጹም ይረባናል፡፡ አዎ! እርሱን ብንከተለውና ብንሰማው “ሰላማችን እንደወንዝ ጽድቃችንም እንደባህር ሞገድ ይሆንልናል”(ኢሳ.48፥18)
አሜን፡፡ በስሙ ሥልጣን ይሁንልን፡፡   

    ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment