Tuesday 11 November 2014

የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮች (ክፍል - ሁለት)



3. ደቀ መዛሙርትን ወደኋላ ይስባሉ(ቁ.30)

   ጌታ ኢየሱስ በወንጌል “መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” ብሏል፡፡  (ማቴ.10፥38) እኛ ሁል ጊዜ ከክርስቶስ በኋላ ነን፡፡ ተፎካካሪ ስላልሆንን ከጐኑ ፤ ወይም የተሻልን ሆነን ከኋላችን የምናስከትለው አይደለንም፡፡ እርሱ ሰባሪ ነውና ሁል ጊዜ ከፊት የሚወጣ ነው፡፡ (ሚክ.2፥13) ተመርቆ የተከፈተው አዲስ፤ ህያው መንገድና (ዕብ.10፥19) ቀድሞም በመንገዱ የሄደበት እርሱ ስለሆነ እኛ የእርሱን ፋናና ፍለጋውን የምንከተል ነን፡፡ (1ጴጥ.2፥21) ይህ ጉዞ የዕለት ተዕለትና ያለምንም ማቋረጥ ልናደርገው የሚገባን ነው፡፡(ሉቃ.9፥23)

   የሐሰት መምህራን ግን ይህን መንገድና ጉዞ ፍጹም በመቃረን ይገለጣሉ፡፡ ወደአብ መቅረቢያውንና መግቢያውን በር ክርስቶስን ይዘጉና የራሳቸውን በርነት አጉልተው ያሳያሉ፡፡ መጥምቀ መለኰት ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅ በነበረበት ጊዜ ራሱን ሳይሆን ክርስቶስን አጉልቶ፤ አድምቆ ለሕዝቡ አሳየ፡፡ ነቢዩ ቅዱስ ዮሐንስ በአገልግሎቱ ጌታውን ተከተለ እንጂ “እኔ ልቅደም” አላለም፡፡
  የሐሰት መምህራን ከእውነተኛ አገልጋዮች ጋር ከመስማማት ይልቅ ፈቀቅ ማለትና ወደራሳቸው መንገድ ማዘንበል ይወዳሉ፡፡(2ጢሞ.1፥15) ራሳቸውን እንደዋና ስለሚቆጥሩ የታመኑትን አገልጋዮች መናቅና ዝቅ ማድረግን ይመርጣሉ፡፡(ሐዋ.8፥9 ፤ 3ኛዮሐ.9) በተከታዮቻቸው ፊት እንደዋና የሚታዩትና ሌሎች የታመኑ አገልጋዮችን የሚያናንቁት ተከታዮቻቸውን ይበልጥ ወደኋላቸው ለመሳብ ነው፡፡ ጌታ ራሱን ዝቅ በማድረግና እስከሞት በታዘዘ የአገልግሎት ህይወት ቢመጣም(ፊሊ.2፥8) የሐሰት መምህራን ግን ይህን መንገድ ፈጽሞ አይመርጡም፡፡ “ሊሰርቁና ሊያርዱ” ስለሚመጡ (ዮሐ.10፥10) የትህትና መንገድ ፈጽሞ አይሆንላቸውም፡፡
   ከዚህም ሌላ ደቀ መዛሙርትን ለራሳቸው እንጂ ለክርስቶስ አያበዙም፡፡ ቀድሞ ወደራሳቸው ካመጧቸው በኋላ ወደኋላቸው ይስቧቸዋል፡፡ ክርስቶስን ከመከተል በስውር እየከለከሉ እነርሱን እንዲከተሏቸው ያደርጓቸዋል፡፡ ስለዚህም የሐሰት መምህራን ደቀ መዛሙርትን ለራሳቸው እንጂ ለክርስቶስ አያበዙም፡፡  
4. ጠማማ ነገርን ይናገራሉ፡፡
     ወንጌል ከኃጢአትና  ከጨለማ ፤ ወደጽድቅና ወደሚደነቅ ብርሃን ስለምታመጣ የሰላምና የቀና ጐዳና ተብላለች፡፡ (ሉቃ.1፥79 ፤ ኢሳ.9፥2 ) ጠማማነት ከእውነት ነገር መሳት፤ ሰዎች ወደ እውነት እንዳይደርሱ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሐሰት መምህራን  ሐሳባቸውን  በግድ ወይም በብልሃት ወደ መዕሐፍ ቅዱስ አስርፀው ያስገባሉ፡፡ በሌላ አባባል “የኛ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማ” ይላሉ እንጂ እነርሱ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ፈጽሞ አይሄዱምና የጠማማን ነገር ወይም ጠማማነትን ይናገራሉ፡፡
   እኒህ ሰዎች ጠማማን ነገር የሚናገሩት ከሌለ ነገር ተነስተው ሳይሆን ካለና ክፍተት ሊፈጥር ይችላል ብለው ከሚያስቡት ነገር ተነስተው ነው፡፡ ለምሳሌ ፦
4.1. በገላትያ ቤተ ክርስቲያን የተነሱ የሐሰት መምህራን የትምህርታቸው መነሻ በብሉይ ኪዳን የነበረውን ግዝረትንና ሙሴን ተተግነው ቅዱሱን ወንጌል ልዩ በማድረግ(ገላ.1፥6)  በማጣመም ሲሰብኩ እንመለከታለን፡፡ ግዝረትንና ሙሴን በማንሳት በግልጥ መዳን በህግ እንደሆነ(ገላ 3፥2 ፤ 2፥12) ያስተምሩ ለነበሩ የሐሰት መምህራን “የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።” በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተቃወመ ሲሆን ወግ አጥባቂነትንና የተሻረውን ህግ ከጸጋ ጋር መደባለቅ፤ የጌታን ጸጋ ማቃለልና በመስቀሉ ሥራ ላይ ማፌዝ  እንደሆነ አስረግጦ ይናገራል፡፡  በእርግጥም “ በሐሰት የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው ” (ኢሳ 9፥5 )
     ሁል ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን  የሚጎዱ ሰዎች የስህተት ትምህርታቸውን የሚመሠርቱት በክርስትና ውስጥ ባለ አንድ ነገር ላይ ተተግነው ነው፡፡ ለምሳሌ ፡- መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጻሕፍት እንደ አንዱ መጽሐፍ እንደሆነ እንጂ የሚተካከለው እንደሌለና የሁሉ የበላይ እንደሆነ አያስቀምጡም፡፡ ይህንን ለማጉላት የሌሎች “አባቶችንና መምህራንን” ትምህርት እንደማስደገፊያ ያስገቡበታል ፡፡ ስለዚህም  የሐሰት መምህራን ጠማማ ትምህርታቸውን ከሌላ ነገር ሳይሆን ለማደናገርና ብዙ ደጋፊ ለማግኘት ካለና ከሚታወቅ ነገር ተነስተው የስህተት ትምህርታቸውን ያሠርጻሉ፡፡
4.2. የሐሰት መምህራን ክስ የማቀናበር ልዩ ችሎታ አላቸው፡፡ ናቡቴን(1ነገ.20፥13)፤ ክርስቶስን (ማቴ.26፥59-63)፤ እስጢፋኖስን (ሐዋ.6፥14) ጳውሎስንና (ሐዋ.24፥5-6) … ሌሎችንም የከሰሱት የማንንም ስሜት ሊነካ  በሚችል መልክ ነው፡፡  አንዱን ብናነሳ እስጢፋኖስን  የከሰሱት የትኛውም አይሁዳዊ  “ስሜታዊ” ሊሆን በሚችልበት “ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና” የሚል የክስ አይነት ነው፡፡ ለአንድ አይሁዳዊ ሙሴ ማለት የመጨረሻ መመኪያው ነው፡፡ የሙሴ ህግ ተሻረ ፤ ተለወጠ ቢባልና ይኸው ጉዳይ ለአንድ አይሁዳዊ ቢነገረው የሚታገስበት መንገዱ ትንሽ ነው ፡፡
     ይኸው አሰላል ዛሬ ላይ እግር በእግር ሲፈጸም እናያለን፤ ለወንጌል የጨከኑ አገልጋዮችን ዛሬ ላይ ከስም ማጥፋት በዘለለ ፥ ከባድ የዛቻና የድብደባ ድርጊት የሚፈጸምባቸው የክሱ ምክንያት ማንንም ስሜታዊ በሚያደርገው “ስለማርያም እንዲህ አሉ” ፣ “ስለቅዱሳን እንዲህ ብለዋል” ፣ “ስለታቦት እንዲህ ሲሉ ተሰምተዋል” … በሚል የክስ ዘዬ ነው፡፡ (ወደመናፍቅነት አድልተው ሙሉ ለሙሉ የሚቃወሙትን ግን እዚህ ላይ ማካተት አልፈልግም)፡፡  
     የሚናገሩበት ርዕስ የሰውን ስሜት ለመቀስቀስና የሐሰት ክሳቸውን ሚዛን ለማስደፋት በሚያስችል መንፈሳዊ ለዛ አልብሰው የሐሰት ክሳቸውን ለሚያቆነጁት እንጂ፡፡ እንዲህ ያሉት ነቢያትን ብዙ ህዝብ እንደሚወዳቸው በነቢዩ አንደበት “ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ” (ኤር.5፥31) ተብሎ ተነግሯል፡፡
  ለዚህ ብዙ ማሳያ ማቅረብ ቢቻልም ዛሬ ላይ ከአገልጋዮች እስከሰንበት ትምህርት ቤት የመገለል ፣ የመገፋት ፣ በጠላት አይን የሚታዩት እኒሁ የሐሰት ወንድሞች በሚያቀናብሩት ክስ ምክንያት ነው፡፡ ኤርምያስ ዘመኑ የልቅሶና የሰቆቃ እንዲሆን ያደረገበት አንዱ ነገር ፥ የሕዝቡ የሐሰት ነቢያትን ሙሉ ለሙሉ መቀበልና እርሱን ፍጹም ማግለላቸው ነበር፡፡ የሐሰት መምህራን ሲበዙ ፥ እውነተኛ አገልጋዮች የሕዝቡ መጥፋትና ከአምላክ መለየት እያሰቡ (ኤር.14፥16) ዕጣ ፈንታቸው ሐዘን ፣ እንባና ሰቆቃ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሳይል “ይላል እግዚአብሔር …” እያሉ (ኤር.23፥31) ሕዝቡን የሚያስቱትን የሐሰት መምህራን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር የሚስቱትንም ሕዝቦች ይቀጣል፡፡ (ኤር.23፥34)  
  ጌታ ኢየሱስ በእረኝነቱ ይጠብቀን፡፡

                                 ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment