Wednesday, 27 August 2025

“ሄደህ …ስበክ”! (ዮና. 1፥1)

 Please read in PDF

እግዚአብሔር አምላክ የተልእኮ አምላክ ነው። አስቀድሞ ሰው በኀጢአቱ በወደቀ ጊዜ ለማንሳት ወደ ወደቀበት ስፍራ፣ “ወዴት ነህ?” (ዘፍ. 3፥10) እያለ ፍለጋ የመጣው ያህዌ ኤሎሂም ነው። እግዚአብሔር ፍጥረት በወደቀ ጊዜ በመፈለጉና ፈልጎም በማግኘቱ፣ የተልእኮ አምላክ ነው። ርሱ ፍጥረት በመውደቁ ደስ አይሰኝም፤ “የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” (ሕዝ. 18፥32) እንዲል።

በዮናስ መጽሐፍ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ሉዓላዊ አምላክና ሉዓላዊ አምላክነቱንም፣ በጥበብ፣ በጸጋ፣ በኀይል የሚገልጥ አምላክ ኾኖ ይታያል። የዮናስ ስብከት እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ አጭርና ግልጥ ነው፤ “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” (3፥4) የሚል። ነገር ግን ይህን ስብከት ቢያቀርብም እንኳ፣ ዮናስ በእግዚአብሔር ምሕረት ያልተደሰተና በታዘዘው ትእዛዝ ላይ ያመጸ መኾኑን እንመለከታለን። ከዚህ የተነሣ መልእክቱና ስብከቱ በዮናስ ሕይወት ላይ ደምቆ ይታያል።

እግዚአብሔር ግን ሉዓላዊ ነውና ዮናስን ብዙ ሕዝብ ለነበረባት ነነዌ ነቢይ እንዲኾንና ስብከት እንዲሰብክ ላከው። በተልእኮ ውስጥ ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን አጥብቆ ፈላጊነት እንመለከታለን፤ እግዚአብሔር አይታክትም፤ አይደክምም፤ ፍጥረትን በመፈለግ ውስጥ እንደ ርሱ ኃያልና ጽኑ ፍቅር ያለው ሌላ ማንም የለም።

የዮናስ ልብ የሚያመለክተው የእስራኤልን ልብ ነው፤ እስራኤል በዙሪያዋ ለነበሩት አሕዛብ፣ ልብዋ በንቀትና በጥላቻ የተመላ እንጂ እንዲመለሱና እንዲድኑ የማትሻ ነበረች።

እግዚአብሔር ግን እንደ “ሕዝቡ” ደንታ ቢስ አይደለም፤ ይልቁን ሕዝብ አይደሉም ለተባሉትም የሚጠነቀቅና የሚሳሳ አምላክ ነው። ያልተወደደ የተባለውን የሚወድድ እግዚአብሔር ብቻ ነው!

ይህ አምላካዊ ተልእኮ በአዲስ ኪዳንም ቀጥሎአል፤ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. 28፥19) ጌታችን ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ የትኛውም ትውልድ ውስጥ ለሚገኙ የኢየሱስ ተከታዮች ሁሉ ከክርስቶስ የተሰጡ ታላቅ ተልእኮ ናቸው። ቃላቱ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ሥራ ዐላማ፣ ኀላፊነትና ተልእኮ የሚመለክቱ ናቸው፤ እናም፦ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ትምህርት፣ ሕይወትና ሥራ እንዲኹም የነቢያትና የሐዋርያትን ትምህርት መሠረት በማድረግ ወደ ዓለም ሁሉ በመሄድ ወንጌልን መስበክ አለባት፤ (ኤፌ. 2፥20)። ይህ ተግባር ሚሲዮናውያንን ወደ እያንዳንዱ አገር የመላክን ተቀዳሚ ኀላፊነት ያካትታል (የሐ.ሥ. 13፥1-4)።

በሐዋርያዊ ተልዕኮ ውስጥ መዘንጋት የሌለብንም ታላቁ ጉዳይ ንስሓንና የኀጢአት ስርየትን (ሉቃ. 24፥47)፣ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ” የመቀበል ተስፋን (የሐ.ሥ. 2፥38)፣ የኢየሱስን ከሰማይ መምጣት እየተጠባበቁ ሳለ (የሐ.ሥ. 3፥19-20፤ 1ተሰ. 1፥10) ከዚህ ጠማማ ትውልድ መለየት እንደሚገባ ምክር መስጠትን (የሐ.ሥ. 2፥40) እንዲኹም ዋናው ዐላማ የክርስቶስን ትእዛዞች የሚጠብቁ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ነው።

በዚህ ታላቁ ተልእኮ ውስጥ የሚከናወኑ መንፈሳዊ ተግባራት፣ የቤተ ክርስቲያን አባላትን ቍጥር በማብዛት ላይ ማተኰር የለባትም፤ ማተኰር ያለባት ግን ከዓለም ራሳቸውን የለዩ፣ የክርስቶስን ትእዛዝ የሚጠብቁ እንዲሁም ርሱን በፍጹም ልባቸው፣ ዐሳባቸውና ፈቃዳቸው የሚከተሉትን ደቀ መዛሙርት በማፍራት ላይ ነው። ጌታችን፣ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤”  (ዮሐ. 8፥31)።

እናም አማኞች ዘወትር በጠፉ ወንዶችና ሴቶች ላይ እንድናተኲር ክርስቶስ ያዘዘን መኾኑን ከቶ ቸል ልንል አይገባም። ያመኑ ሁሉ የዓለምን ክፋት በማጋለጥ (ኤፌ. 5፥11)፣ ክፉ ከኾነው ከአሁኑ የዓለም ሥርዐትና ከኢግብረገባዊነቱ ተለይተው መውጣት አለባቸው (ሮሜ 13፥12፤ 2ቆሮ. 6፥14)። በተጨማሪም እንደ ጌታችን ትእዛዝ በክርስቶስና በወንጌሉ የሚያምኑ ሁሉ በውኃ መጠመቅ አለባቸው። ይህም ኢግብረገባዊነትን፣ ዓለምንና የራሳቸውን የኀጢኣታዊ ተፈጥሮ ለማውገዝና ለመተው የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲሁም ለክርስቶስና ለመንግሥቱ ዐላማ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ የሰጡበትን ሁኔታ ይወክላል (የሐ.ሥ. 22፥16)። ከዚህም ታላቅ መታዘዝ በኋላ የመንፈስ ቅዱስ ኀልዎትና ኀይል አማካይነት ክርስቶስ ከታማኝ ተከታዮቹ ጋር ለዘላለም አብሮ ይኾናል። ለዚህም ጌታችን አየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለሕዝብ ሁሉ ለመመስከር መሄድ ያለባቸው ከላይ ኀይልን ከለበሱ በኋላ ብቻ እንደ ኾነ ነገራቸው(ሉቃ. 24፡49፤ የሐ.ሥ. 1፥8)። ኹላችን በዚህ ቃል ለመታዘዝ ጸጋ ይብዛልን፤ አሜን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

No comments:

Post a Comment