Friday, 8 November 2024

“መናፍቅ በመባሌ እጅግ ደስ ይለኛል”

 Please read in PDF

“… በሥጋ ካየነው ያናድዳል፤ የሞተልንን አምላክ በመከተል፣ ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔም ምሰሉ” ባለው መንገድ ከሄድን ያስደስታል፡፡ ምክንያቱም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ … በአባቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተዋርዶአል፡፡ … ርሱ ምን የልተባለው ነገር አለ? ዋናው ክሱ እኮ በሃይማኖት ነው፤ በሃይማኖት መከሰስ ማለት መናፍቅ ነው ተብሎ ነው፡፡ … ሰንበትን ሻረ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ አለ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ ብለው ነው፤ ያ ለነርሱ መናፍቅነት ነበረ … ርሱ ያልተባለው ምን አለ? … ቅዱስ ጳውሎስ ምን ያልተባለው አለ? አስቀድሞ የብሉይ ኪዳን ዋና ጠበቃ ነበረ … ኋላ መንፈስ ቅዱስ አገኘውና ቀየረው፣ ጌታም ምርጥ ዕቃዬ አለው፡፡ እነዚያ ግን መናፍቅ ነው ያሉት … በተለይ በነገረ ድኅነት እንዲህ መባሌ እጅግ ደስ ይለኛል፡፡”

 (ብጹዕ አቡነ በርናባስ ከመለሱት ቃለ መጠይቅ የተወሰደ)

ብጹዕ አቡነ በርናባስ ወንጌል በትክክል ከተረዱ ጳጳሳት መካከል አንዱ ናቸው። በርግጥ "የእግረኛ ሚዲያ" ጠያቂው እንደ ተናገረውም፣ ጳጳሱ "መ*ና*ፍ*ቅ- ነ*ፈ*ቀ" ተብለዋል፤ የተባሉትና በዚህ ስም የተነቀፉት፣ መ*ና*ፍ*ቅ ኾነው ወይም የኑ*ፋ*ቄ ትምህርት ተገኝቶባቸው አይደለም። እንዲህ የሚሉአቸውም ሰዎች ለከርስቶስ ወንጌል ቀንተው ወይም ወንጌልን በትክክል ተረድተው አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፣ “... በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤”(ሐ.ሥ. 24፥14) ብሎ እንደ ተናገረው፣ ጳጳሱን የሚከስሱት ጳውሎስን እንደ ከሰሱት ያሉ ሰዎች ናቸው።

አዎን፤ እንደ ተናገሩትም በዚያ በስድብ ስም መጠራታቸው ያስደስታቸዋል፤ ያስደስታልም። የደስታቸውንም አብነት "ጌታችን ኢየሱስና ቅዱስ ጳውሎስ ምን ያልተባሉት ነገር አለ?" በማለት ቆፍጠን ብለው ይመልሳሉ። የጌታ ኢየሱስ ክስና ወቀሳም ሃይማኖታዊ ይዘቱ ሲገመገም፣ በዚያ ዘመን ከሳሾች ዘንድ "መ*ና*ፍ*ቅ" እንደሚያስብል ጠቅሰውም በሙግት ያስረዳሉ። በክርስቶስ ኢየሱስ ስምና ወንጌል የሚመጣ ስድብና ነቀፋን መቀበል እጅግ ብጽዕናና መታደል ነው። ጌታችን ኢየሱስ እንዳስተማረው፣

“ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።”(ማቴ. 5፥11-12)።

በሌላም ስፍራ እንዲህ ብሎአል፣

“ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።” (ሉቃ. 6፥22-23)

ቅዱስ ጳውሎስም ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንዲህ መክሮታል፣

“በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ።”(2ጢሞ. 3፥12)።

በርግጥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም (ዮሐ. 15፥20) እንዲል፣ አባ በርናባስ ከኢየሱስ ስለማይበልጡ በኢየሱስ የኾነው ኹሉ ቢደርስባቸው ይህ እጅግ ታላቅ ሽልማት አለው። ቅዱስ ጳውሎስ የመጀመሪያው ሰማዕት ሲገደል ቆሞ ያይ፣ የገዳዮችን ልብስ ጠባቂ ነበር፤ በኋላ ግን ላሳደደው ክርስትና ተሰድዶለት ርሱም በሰማዕትነት ዐለፈ!

መነቀፍና መተቸት፣ በስሙና በወንጌሉ መሰደብና መዋረድ ክርስትና ፋሽን ብቻ እንዳይኾን ያደርገዋል፤ ቤተ ክርስቲያ “በሰላም ጊዜዋ” ለውርደትና ለአስቀያሚ የስህተት ትምህርቶች ተጋልጣለች፤ በመከራ ውስጥና በነቀፋና በትችት ረመጥ ውስጥ ባለፈችባቸው ዘመኖችዋ ግን አብባና ፈክታለች፤ ተውባና አጊጣለች! እናም በስሙ መነቀፍና መተቸት፤ መዋረድና ዝቅ ዝቅ ማለት መታደልና ታላቅ ብጽዕና ነው! 

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንዲህ ያሉ ጳጳሳትን አክብራ መያዝ፤ ከዚህ አባት በተቃራኒ ማርያምን ወይም ሌሎች ፍጡራንን ያከበሩ እየመሠላቸው፣ ነገረ ድኅነትን በማዋረድና የክርስቶስን የመስቀል ሥራ የሚያክፋፉትን መውቀስና ወደ እውነት መመለስ ይጠበቅባታል።

 

በርግጥ ዛሬም የወንጌል ብርሃን ጨርሶ እንዳልተዳፈነ ተስፋ አለ! እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው፤ ለርሱ ክብር የማይንበረከክ አይኖርም!

2 comments:

  1. አመሰግናለሁ ትልቅ ትምህርት

    ReplyDelete
  2. ጌታ ኢየሱስ ዘላለምhin እየባረከ ይባርክ።

    ReplyDelete